የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች

ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፍ የመጨረሻው ክለብ የሚለይ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

የከፍተኛ ሊጉ መሪ አርባምንጭ እና ሀዋሳ ከተማ የሚያደርጉት የሩብ ፍፃሜው የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች


በሁለተኛው ዙር ኦሮምያ ፖሊስን በመለያ ምት፤ በሦስተኛው ዙር ደግሞ በአሕመድ ሑሴን ብቸኛ ግብ ባህርዳር ከተማን አሸንፈው ወደ ሩብ ፍፃሜው የበቁት አርባምንጭ ከተማዎች የከፍተኛ ሊጉ ብቸኛ ተወካይ ናቸው። አዞዎቹ ከወራት በፊት ባህርዳር ከተማን በገጠሙበት ወቅት በከፍተኛ ሊጉ ከመሪው በሁለት ነጥብ ርቀው በሁለተኛ ደረጃነት ተቀምጠው ነበር፤ አሁን ግን ከተከታያቸው በአምስት ነጥብ ልቀው የሊጉን አናት ተቆናጠዋል። አርባምንጮች በመጀመርያው ዙር መገባደጃ ጨዋታ ላይ ካፋ ቡናን አራት ለአንድ ካሸነፉ በኋላ ላለፉት ሰላሣ ሦስት ቀናት በዝግጅት ቆይተዋል። ቡድኑ አራት ቀናት ካረፈው ተጋጣሚው ሀዋሳ ከተማ የተሻለ የመዘጋጃና የዕረፍት ጊዜ ነበረው። ይህም በብዙ ረገድ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ተብሎ ይታመናል። በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ ግስጋሴ በማድረግ ላይ የሚገኙት አርባምንጮች ባለፈው የውድድር ዓመት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠማቸውም።

ቤንች ማጂ ቡና እና መቻልን አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያሻገራቸውን ውጤት ያስመዘገቡት ሀዋሳ ከተማዎች በፕሪምየር ሊጉ የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ወደ ጥሩ ብቃት ተመልሰዋል። በሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ባስቆጠረው ኤርትራዊው ፈጣን አጥቂ ዐሊ ሱሌማን በተገኙ ግቦች ወደዚህ ዘር የበቁት ሀይቆቹ በመጨረሻዎቹ አምስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ዘጠኝ ግቦች በማስቆጠር በጥሩ ብቃት የሚገኝ የፈት መስመር አላቸው። በነገው ዕለትም በኢትዮጵያ ዋንጫ ላይ አንድ ግብ ብቻ ካስተናገደው የአርባምንጭ የተከላካይ መስመር የሚያደርጉት ፍልምያ ተጠባቂ ነው።