ሙጅብ ቃሲም የጣና ሞገዶቹን ተቀላቅሏል

በአጋማሹ የዝውውር መስኮት በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች አጥቂ አስፈርመዋል።

ከፋሲል ከነማ ጋር ከተለያየ በኋላ ላለፉት ዓመት ከመንፈቅ ጊዜያት ወደ ሀዋሳ ከተማ አምርቶ በመጫዎት ያሳለፈው አጥቂው ሙጅብ ቃሲም በዘንድሮ ቆይታው ከክለቡ ጋር በተፈጠረ ሰጣ ገባ ከቡድኑ ጋር አብሮ  መቆየት ባለመቻሉ በተከታታይ ጨዋታዎች ለቡድኑ ግልጋሎት መስጠት ሳይችል ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ቀሪ የስድስት ወር ውል እያለው በስምምነት ከክለቡ ጋር ተለያይቷል።

ሆኖም ከፊት መስመር ያለባቸውን መሳሳት አስመልክቶ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ ጸጋዬ አበራን ከሲዳማ ቡና ካስፈረሙ በኋላ የሀዋሳውን ሙጅብ ቃሲም ሁለተኛ ፈራሚያቸው አድርገውታል።