የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣አዲስ አበባ ከተማ እና መቻል ድል አድርገዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ በሁለተኛ ቀን ሦስት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፊ ግብ ልዩነት ሲያሸንፉ አዲስ አበባ ከተማ በጠባብ ውጤት አሸንፏል።

ረፋድ ሦስት ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከአዳማ ከተማ ጋር ያገናኘው መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ንግድ አሸናፍነት ተጠናቋል።

የመጀመሪያ ግብ እስከተቆጠረበት ደቂቃ ድረስ በሁለቱም መካከል ጥሩ ፉክክር የታየ ሲሆን የመጀመሪያ ግብ መቆጠሩ ንግድ ባንክ የጨዋታ በላይነት እንዲወስድ ሆኗል። በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉት ንግድ ባንኮች በ30ኛው ደቂቃ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ከመረብ ጋር አገናኝታ የጨዋታ ብልጫ እንዲወስዱ አድርጋለች።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታ መመለስ የዳገታቸው አዳማ ከተማዎች አልፈው አልፈው የሚያገኙትን እድል በደካማ አጨራረስ ሲያበላሹ ተመልክተናል። ንግድ ባንክ ወደ መልበሻ ክፍል ከመመለሳቸው በፊት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሙከራ ሲያድርጉ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ግብ ሳይቆጠር ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተጠናክረው የገቡት ንግድ ባንኮች በነጥብ ከመስተካከላቸው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያላቸውን የግብ ልዩነት አስፍተው ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተጋጣሚያቸው ላይ በጫና ተጫውተዋል።

በ61ኛው ደቂቃ ለግብ የተቃረበ ኳስ ወደ ግብ ክልል ይዘው በመግቡበት ቅፅበት የአዳማ ከተማ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሰጥቷቸዋል። እመቤት አዲሱ አስቆጥራ መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድጋለች።

በዚህ ያላበቁት ንግድ ባንኮች እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ኳስን ወደፊት ገፍተው ተጫውተዋል። በ89ኛው ደቂቃ መዲና አወል በርቀት መትታ ሌላኛውን ግብ አስገኝታለች። በዚህም ንግድ ባንክ 3ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት አዳማ ከተማን አሸንፏል።

ቀን ስምንት ሰዓት ላይ ልደታ ክ/ከተማን ከ አዲስአበባ ከተማ ያገናኘው መርሃግብር በአዲስ አበባ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

እምብዛም የግብ ሙከራዎች ባልታዩበት በዚህ ጨዋታ አልፈው አልፈው በሚያደርጉት ሙከራ ልደታዎች የተሻሉ ነበሩ።እንዲሁም ቀድሞ ግብ በማስቆጠርም ልደታ ቀዳሚ ነበር።ሆኖም ግን እየመሩ መቆየት የቻሉት ለ7 ደቂቃ ብቻ ነበር።

በ40 ደቂቃ የልደታ ክ/ከተማ አምበል እና የፊት መስመር ተጫዋች የሆነችው ህዳት ካሱ በራሱ ጥረት ኳስን ይዛ በመግባት ግሩም ግብ አስቆጥራ ልደታ ክፍለ ከተማን መሪ ማድረግ ችላ ነበር። ሆኖም ግን እየተመሩ ዕረፍት መውጣት ያልፈለጉት አዲስ አበባ ከተማዎች ግብ እንዲተቆጠረባቸው በመለሰው ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረዋል።

መደበኛው አርባ አምስት ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ውስጥ የልደታ ክፍለ ከተማ ተከላካዮች መካከል በተፈጠረው የእጅ ንክኪ ለአዲስ አበባ ከተማ ፍፁም ምት ተሰቷቸዋል። ቤተልሔም መንተሎ ከመረብ ጋር አገናኝታ እረፍት በአቻ ውጤት እንዲወጡ ሆኗል።

በሁለተኛው አጋማሽ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ የግብ ሙከራ መመልከት አልተቻለም። ሆኖም ግን ሁለቱም ቡድኖች በኳስ ቁጥጥር ተመጣጣኝ አጨዋወትን አስመልከተዋል። መከላከል የበዛበት በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውለዋል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቃቁ ደቂቃዎች ሲቀሩ የጥረታቸው ወጤት የሆችዋን ግብ የአዲስ አበባዋ ዳግማዊት ሞገስ በ88ኛው ደቂቃ በርቀት መጥታ በማስቆጠር ለአዲስ አበባ ከተማ 3 ነጥብ አጎናፅፋለች።

የዕለቱ ማሳረጊያ ጨዋታ መቻልን ከቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቷል። መቻልም ከፍፁም ጨዋታ በላይነት ጋር በሰፊ ግብ ልዩነት አሸንፏል።

በዚህ ጨዋታ መቻሎች በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ብቻ በርከት ያለ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል።ሆኖም ግን ግብ አላስቆጠሩም ነበር።ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ጫና ሲያሳድር የነበረውን የመቻልን የፊት መስመር ለማስቆም በመከላከል ሲጫወቱ ተስተውለዋል።

በ37ኛው ደቂቃ ህይወት ረጉ በርቀት መትታ ድንቅ ግብ አስቆጥራ መቻልን መሪ አድርጋለች። ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የቋመጡት መቻሎች የጊዮርጊሶችን አለመረጋገት ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ሳይሳካላቸው እረፍት ለመውጣት ተገደዋል።

በመልበሻ ክፍል መልስ ጠንከር ብለው የገቡት መቻሎች ገና ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሩ በሁለተኛው ደቂቃ በ47ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የተቃረበ ኳስ ይዘው ሲገቡ ጊዮርጊሶች ባደረጉት በእጅ ንክኪ ፍፁም ቅጣት ምት ለመቻሎች ተሰጥቶ ቤተልሔም ታምሩ አስቆጥራ 2ለ0 እንድመሩ አድርጋለች።

ሁለተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ መረጋጋት የተሳናቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ስህተት ሲሰሩ ተስተውለዋል። በዚህም አከታትለው በ49ኛው እና በ55ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ ማስተናገድ ችለዋል። በ49ኛው ደቂቃ ቤተልሔም ታምሩ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ አግንታ በግሩም ሁኔታ አክርራ በመምታት አስቆጥራ በአንድ ጨዋታ ለራሷ ሁለተኛ ግብ ለክለቡ ሦስተኛ ግብ በማስቆጠር ልዩነታቸው አስፍታለች።

እንዲሁም በ55ኛው ደቂቃ ራሷ ቤተልሔም ታምሩ ሶስተኛ ግብ አስቆጥራ ሀትሪክ ሲትሰራ መቻልም 4 ለ0 እንዲመራ ሆኗል። መቻሎች እስከመጨረሻው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ታይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ደካማ የሚባል ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፏል። በዚህም ጨዋታው በመቻሎች 4ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።