ሚሊዮን ሠለሞን ወደ አዲስ ክለብ አመራ

ከስድስት ወራት በፊት ሀዋሳን የተቀላቀለው ተከላካይ ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ወደ አዲስ ክለብ ማምራቱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር አጋማሽ የዝውውር መስኮት ከተከፈተ ቀናት ቢቆጠሩን እንደ ቀደሙት ጊዜያት በርከት ያሉ ዝውውሮች እየተደረጉ አይገኝም። ይህ ቢሆንም ክፍተት አለብኝ የሚሉ ክለቦች በመስኮቱ እያማተቱ ሲሆን ከዓምናው በአንፃራዊነት ደካማ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድንም ወሳኝ ተከላካይ ማስፈረሙን የዝግጅት ክፍላችን አረጋግጣለች።

መድንን የተቀላቀለው ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ነው። የቀድሞ የአዲስ አበባ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ተጫዋች ክረምት ላይ ለአንድ ዓመት በሀዋሳ የሚያቆየውን ውል ቢፈርምም ከሳምንታት በፊት የልቀቁኝ ደብዳቤ ለክለቡ ማስገባቱ ይታወሳል። ተጫዋቹ እና ክለቡም በስምምነት ከተለያዩ በኋላ አሁን ወደ ኢትዮጵያ መድን ማምራቱ እርግጥ ሆኗል።