የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ተጠባቂው ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ8 ሳምንት የመጨረሻ ቀን መርሃግብር ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው የሳምንቱ ተጠባቂውን ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሀዋሳ ከተማ በግብ ተንበሽብሾ እንዲሁም ሀምበርቾም አሸንፈዋል።

ረፋድ ሶስት ሰዓት ላይ ይርጋጨፌ ቡናን ከሀዋሳ ከተማ ያገነኘው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ በላይነት ተጠናቋል። ደረጃቸውን ለማስጠበቅ ሰፊ ግብ ማስቆጠር ግዴታ የሆነባቸው ሀዋሳ ከተማዎች ገና ጨዋታ ከመጀመሩ ነበር ተጋጣሚያቸውን በግብ ሙከራ ማጨናነቅ የጀመሩት።

ከብዙ ግብ ሙከራ በኋላ በ24ኛው ደቂቃ ቱሪስት ለማ ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ሀዋሳ ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች። ግብ አስቆጥረው ወደጨዋታ የገቡት ሀዋሳዎች ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር አራት ደቂቃ ብቻ ነበር የጠበቁት።በ28ኛው ደቂቃ እሙሽ ዳንኤል በአንድ ለአንድ ቅብብል ያገኘችውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝታ ግባቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች።

በዚህ ብቻ ያላበቁት ሀዋሳዎች 8 ደቂቃ ብቻ በመጠበቅ በ36ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ እሙሽ ዳንኤል ከመስመር የተሻገረው ኳስ አስቆጥራ መሪነታቸው ወደ ሶስት አድርሰዋል።የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት በ42ኛው ደቂቃ ረዲኤት አስረሳኸኝ ከግብ ክልል ውጪ ሆና መትታ በማስቆጠር 4ለ0 እየመሩ እረፍት እንዲወጡ ሆኗል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ሀዋሳ ከተማ በመጀመሪያ አጋማሽ ያሳዩትን እንቅስቃሴ ዳግም አስመልክተዋል። ዛሬ ጥሩ ያልነበሩት ይርጋጨፌዎች በሁለቱም አጋማሽ ደካማ እንቅሰቃሴ አስመልክተዋል።በመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ብቻ ያላበቁት ሀዋሳዎች በ62ኛው ደቂቃ በይርጋጨፌ ግብ ውስጥ በተደረግ የእጅ ንክክ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት እሙሽ ዳንኤል አስቆጥራ 5ለ0 እንዲመሩ አድርጋለች።

እንዲሁም በ72ኛው ደቂቃ ረዲኤት አስረሳኸኝ ከመስመር አካባቢ አክርራ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥራ ጨዋታው 6ለ0 እንዲሆን አድርጋለች።ሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን አግንተው መጠቀም አልቻሉም።ይርጋጨፌ ቡና በአንፃሩ በፍፁም ጨዋታ በላይነት ተበልጠው ጨዋታውን ለመጨረስ ተገደዋል።በዚህም ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ 6ለ0 አሸናፊነት ተገባዷል።

ቀን ስምንት ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው  የሳምንቱ ተጠባቂው ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፍነት ተጠናቋል።

የሳምንቱ ትልቁ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከአርባምንጭ ያገናኘ መርሃ ግብር ሲሆን ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴም ለተመልካች አስመልከተዋል።ጥሩ ፉክክር እና ተመጣጣኝ የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴ በታየው በመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያለ የግብ መለከራዎች በሁለቱም ቡድኖች መካከል ተደርጓል።

ሁለቱም ቡድኖች በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት ሲያድርጉ ተስተውለዋል። አርባምንጭ ከተማ በኳስ ቁጥጥር ተሽሎ የተገኘበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ሲያሳልፉ ደካማ አጨራረስ አሳዩ እንጂ ከኤልፖዎች የተሻለ ግብ የሚሆኑ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያድርግም በኳስ ቁጥጥር የተበለጡበትን አጋማሽ አሳልፈዋል።በመሆኑም በሁለቱም ቡድኖች መካከል ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ አርባምንጭ ከተማዎች ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር ግን በጣሙን ተቸግረው ተመልከትናል።ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአንፃሩ በረጃጅም ኳሶች በመጠቀም የተጋጣሚን ሳጥን ለመጎብኘት ጥረት አድርገዋል።በ56ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው እና ከሰሞኑ ብዙዎችን እያስደመመች የምትገኘው ሽታዬ ሲሳይ ከርቀት አክርራ በመምታት ባስቆጠረችው ግብ ኢትዮ ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ ችላለች።

ከግቧ በኃላ አርባምንጭ ከተማዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው ለመጫወት ሲጥሩ በአንፃሩ ኤሌክትሪኮች ይበልጥ ጥንቃቄን ጨምረው ለመጫወት ሞክረዋል ይህም የሳምንቱ ተጠባቂው ጨዋታ በሽታዬ ሲሳይ ብቸኛ ግብ በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

የሳምንቱ ማሳረጊያ በነበረው መርሃግብር ድሬዳዋ ከተማን ከሀምበርቾ ያገናኘ ሲሆን ጨዋታውም በሀምበርቾ ከተማ ድል አድራጊነት ተደምድሟል።

10 ሰዓት ላይ የተደረገው ይህ መርሃግብር እምብዛም በግብ ሙከራዎች የተሞላ አልነበረም። ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ነበሩ።ሀምበርቾዎችም ደግሞ መጠነኛ ብልጫ ቢወሰድባቸውም አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ግን አስፈሪ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተመልክተናል።

ከቀዝቃዛው የመጀመሪያ አጋማሽ መልስ በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር በተሻለ መነቃቃት የተጫወቱበት ነበር።

በ76ኛው ደቂቃ ብርሃን ሀይለስላሴ ከርቀት አክርራ የመታችውን ኳስ የድሬዳዋዋ ግብ ጠባቂ ለመቆጣጠር ጥረት ብታደርግም ኳሷ ሀይል ስለነበራት በእጆቿ መሀል ሾልኮ ከመረብ ጋር መገናኘቷን ተከትሎ ሀምበርቾ ከተማን ከጨዋታው ወሳኙን ሶስት ነጥብ እንዲያሳኩ አስችሏቸዋል።