መረጃዎች | 66ኛ የጨዋታ ቀን

17ኛ ሳምንት የሊግ መርሃግብር ነገ ጅማሮውን ያደርጋል እኛም በመጀመሪያ የጨዋታ ዕለት የሚከወኑትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከተ መረጃ በተከታዩ መልኩ አቅርበናል።

ሀዋሳ ከተማ ከሻሸመኔ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ መርሃግብር ጎረቤታዎቹን ሀዋሳ ከተማን ከሻሸመኔ ከተማ የሚያገናኝ ይሆናል።

ሁለተኛው ዙርን በተለያየ መንገድ የከፈቱት የነገዎቹ ተጋጣሚዎች ሀዋሳ በፋሲል ሲረታ ሻሸመኔ ደግሞ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድል ወላይታ ድቻ ላይ መቀዳጀት ችለዋል ፤ በዚህም ሀዋሳ ከተማዎች በ19 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ሻሸመኔ ከተማዎች ደግሞ በ12 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ከውጤታማነት ሆነ ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አንፃር ወጥ ለመሆን እየተቸገሩ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች በሰንጠረዡ የተሻለ ቦታን ይዘው ለማጠናቀቅ ብዙ ስራ እንደሚጠብቃቸው በፋሲል ከነማ የተሸነፉበት ጨዋታ ዓይነተኛ ማሳያ ነበር።

ምንም እንኳን አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ቅጣት ላይ ቢገኙም ሻሸመኔ ከተማዎች በጨዋታ ዕለቶች ግን በሚታይ ደረጃ እየተሻሸሉ ይገኛሉ ፤ በተለይም ወላይታ ድቻን በረቱበት ጨዋታ ከወትሮው በተለየ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸውን የሚመጥን ውጤት ይዘው ወደ መውጣት የመሸጋገራቸው ጉዳይ ለቡድኑ ተስፋ የሚፈነጥቅ ሲሆን ይህም በሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ትግልም ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸውም ይጠበቃል።

ሀዋሳ ከተማዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህኛው የውድድር ዘመን በሁለተኛ ሳምንት ያደረጉት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች በእዮብ ዓለማየሁ አስደናቂ ግብ አንድ ለምንም ማሸነፋቸው አይዘነጋም።

ሀዋሳ ከ ሻሸመኔ ከተማ 4 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሀዋሳ 3 ጊዜ ሲያሸንፍ ቀሪዋን ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ 5 ግቦች ሲያስቆጥሩ፣ ሻሸመኔ 2 ጎሎች አስቆጥረዋል። ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህኛው የውድድር ዘመን በሁለተኛ ሳምንት ያደረጉት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች በእዮብ ዓለማየሁ አስደናቂ ግብ አንድ ለምንም ማሸነፋቸው አይዘነጋም።

10 ሰዓት ሲል የሚጀምረውን ጨዋታ አባይነህ ሙላት በመሐል ዳኝነት ለዓለም ዋሲሁን እና ኢያሱ ካሳሁን ረዳቶች ሙሉቀን ያረጋል በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተሰይመዋል።

መቻል ከባህር ዳር ከተማ

ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግ የሚጠበቅበት የምሽቱ መርሃግብር ሁለት ድልን አጥብቀው የሚሹ ቡድኖችን ያገናኛል።

ሁለተኛውን ዙር ባልተጠበቀ ሽንፈት የጀመሩት መቻሎች በጨዋታ ሳምንቱ ማብቂያ የሊጉ መሪነታቸውን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስረክበው አሁን ላይ በ33 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በዓመቱ መጨረሻ በሰንጠረዡ አናት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ሁነኛ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት መቻሎች ከመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት አንስቶ በመጠኑም ቢሆን መቀዛቀዝ ውስጥ የገቡ ይመስላል ፤ በመሆኑም ቡድኑ በዚህ መልኩ በቀጣይ ነጥቦችን የሚጥሉ ከሆነ ተፎካካሪነታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑን ተከትሎ በፍጥነት አካሄዳቸውን ማረም ይኖርባቸዋል።

ብዙ ተስፋ የተደረገባቸው የጣና ሞገዶቹ በአንፃሩ ከገቡበት ሰመመን አሁን ድረስ የነቁ አይመስሉም ፤ የቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ማሳመን ከተሳነው ወራት የተቆጠሩ ሲሆን በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ስብስባቸው ላይ መጠነኛ ጥገና ያደረጉት ባህር ዳር ከተማዎች አሁን ላይ ከመሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ12 ነጥቦች ርቀው በሰንጠረዡ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ታድያ የአሰልጣኝ ደግዓረግ ይግዛውም የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ለእነሱ ከሚኖረው የላቀ ትርጉም መነሻነት የነገውን ጨዋታ በተሻለ ትኩረት እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።

በባህር ዳር ከተማ በኩል አጥቂው ሱሌይማን ትራኦሬ ከቡድኑ ጋር በስምምነት የተለያየ ሲሆን ሌሎች ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በመቻል በኩልም በተመሳሳይ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ሲታወቅ የበኃይሉ ግርማ ከቅጣት መመለስም መልካም ዜና ሆኖላቸዋል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በሊጉ በሰባት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ባህር ዳር ከተማዎች ሁለት ጊዜ እንዲሁም መቻሎች ደግሞ ሶስት ጊዜ ድል ማድረግ ሲችሉ የተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በነጥብ መጋራት የተፈፀሙ ነበሩ።

መቻል ከ ባህርዳር 7 ጊዜ ተገናኝተው መቻል 3 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ባህር ዳር 2 አሸንፎ ሁለቱ አቻ ተጠናቋል። ጦሩ 11፣ ሞገዱ 9 አስቆጥረዋል።

ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ሲመራው ኢንተርናሽናል እንስት ረዳት ዳኛዋ ወይንሸት አበራ እና ኤልያስ መኮንን ረዳቶች እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በበኩሉ አራተኛ ሆኖ ለጨዋታው ተመድቧል።