የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | ሲዳማ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ ግቦች ድል አድርጓል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር 10ኛ ሳምንት በሁለተኛ ቀን ውሎ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ከመመራት ተነስቶ ባለቀ ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ሲያሸንፍ አዲስ አበባ ከተማም ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

03፡00 ሲል የጀመረው ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡናን ከአዲስአበባ ከተማ አገናኝቶ አዲስ አበባ ከተማ በጠባብ ውጤት አሸንፏል። ገና የመጀመሪያ አጋማሽ እንደጀመረ በ6ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቆመ ኳስ በመሠረት ማሞ አማካኝነት ወደግብ የቀየሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል።

ይርጋጨፌ ቡና በበኩላቸው ጥሩ ሆኖ የዋሉበትን ጨዋታ ማስመልከት ችለዋል። ሆኖም ግን ወደፊት ይዘው የሚገቡትን ኳስ ጨራሽ በማጣታቸው ሲያመክኑ ለመመልከት ተችሏል። እንዲሁም ከዚህ በፊት ካደረጓቸው ጨዋታዎች የበለጠ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

አዲስ አበባ ከተማም በአንደኛው አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሳይሳካለቸው ቀርተው ዕረፍት በ1ለ0 መሪነት ለመውጣት ተገደዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ሁለቱም ጥሩ ፉክክር ማሳየት ችለዋል። ይርጋጨፌ ቡና ከጥሩ ኳስ ቅብብል ጋር የግብ ሙከራ ያደረጉበትን ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፈዋል።

አዲስ አበባም በአንፃሩ በርከት ያለ የግብ ሙከራ ያደረገ ሲሆን ወደግብነት መቀየር ግን ተስኗቸዋል። በዚህም ይርጋጨፌ ቡና የአቻነት ግብ ለማስቆጠር እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጥረት ሲያደርግ አዲስ አበባ ከተማም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በሚያደርጉት ድንቅ ጨዋታ ለተመልካች አስመልክተዋል።

ሆኖም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 1ለ0 በሆነ ውጤት በአዲስ አበባ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ከሲዳማ ቡና አገናኝቶ ሲዳማ ቡና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ግቦች ውጤት ቀልብሶ አሸናፊ ሆኗል። በርከት ካለ ደጋፊ ጋር የታጀበው የ10:00 ጨዋታ በአንደኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማ ሙሉ የጨዋታ በላይነት የወሰዱበት አጋማሽ ነበር።

በኳስ ቁጥጥር በልጠው የተገኙትን ድሬዎች በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል። በ19ኛው ደቂቃ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነችዋ ቃልኪዳን ጥላሁን ከግብ ክልል ውጪ ሆና አክርራ የመታችውን ኳስ የሲዳማ ቡናዋ ግብ ጠባቂ ምቱ ጠንካራ ስለነበር  መቆጠጣር ተስኗት በእጆቿ መካከል በመውጣት ከመረብ ጋር ተገናኝቶ ድሬዎቹ መሪ እንዲሆኑ ሆኗል።

ድሬዳዋ ከተማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በሲዳማ ቡና በኩል የሚታዩትን ክፍተቶች በመጠቀም በአንደኛው አጋማሽ ብቻ በርከት ያለ ሙከራ ከጥሩ ኳስ ቁጥጥር ጋር አድርገዋል። ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። የመጀመሪያ አጋማሽም በድሬዳዋ ከተማ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ሲዳማ ቡና የነበራቸውን ክፍተት በመሸፈን በርከት ያለ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጠንከር ብለው ገብተዋል። በዚህም በኳስ ቁጥጥር ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ መሆን ችለዋል። ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ ነጥባቸውን ለማስጠበቅ ወደኋላ አፈግፍገው በመከላከል ሲጫወቱ ተስተውለዋል።

የአቻነት ግብ ፍለጋ ኳስን ወደ ፊት ገፍተው የተጫወቱት ሲዳማ ቡናዎች የድሬን ግብ ሳይደፍሩ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ቢደርስም ተስፋ ያልቆረጡት ሲዳማ ቡናዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት በ89ኛው ደቂቃ የተከላካይ መሰመር ተጫዋች የሆነችዋ ባዩሽ ኪንባ ከመሃል ሜዳ አከባቢ አክርራ የመታችው ኳስ ከመረብ ጋር ተገናኝቶ ጨዋታው 1ለ1 መሆን ችሏል።

የአቻነት ግብ አስቆጥረው በመነቃቃት ወደ ጨዋታ የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው በ90+2′ ላይ የድሬዳዋ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ኳስን በረጅም ለማውጣት ጥረት በምታደርግበት ቅፅበት ተቀይራ የገባችው ሠናይት ኡራጎ ኳሱ ላይ በመደረብ አግኝታ ወደ ግብነት ቀይራ ለሲዳማ ቡና ሶስት ነጥብ አጎናጽፋለች።