ሪፖርት | አራት ግቦችን እና ሁለት ቀይ ካርዶችን ያስመለከተን ድራማዊው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል

በሁለተኛው አጋማሽ ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን የወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ በርካታ ክስተቶችን ታጅቦ በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወላይታ ድቻ ከአዳማው የአቻ ውጤት የአራት ተጫዋቾችን ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም መልካሙ ቦጋለ ፣ አናጋው ባደግ ፣ መሳይ ኒኮል እና ቢኒያም ፍቅሬ አስወጥተው በምትካቸው አንነተህ ጉግሳ ፣ ፍፁም ግርማ ፣ አብነት ደምሴ እና ባዬ ገዛኸኝ በቋሚነት ሲያስገቡ በፋሲል ከነማ ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት መድኖች በኩላቸው አምስት ተጫዋቾች ቅያሪ አድረገዋል በዚህም ያሬድ ካሳዬ ፣ ሙሴ ካባላ ፣ መሐመድ አበራ ፣ ያሬድ ዳርዛ እና አቡበከር ወንድሙን በአብዱልከሪም መሐመድ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ አሚር ሙደሲር እንዲሁም የክለቡ አዲስ ፈራሚዎች አብዲሳ ጀማል እና አቡበከር ሳኒ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ በመተካት የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል።

የምሽቱ የሁለቱ ቡድኖች መርሃግብር በመጀመሪያው አርባ አምስት ደቂቃ ከሁነቶች መበራከት ውጪ እምብዛም ዕድሎች ተፈጥረው ያልተመለከትን ነበር። ጨዋታውን በተወሰነ መልኩ መቆጣጠር ችለው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ረጃጅም ኳሶችን ወደ ግራ መስመር በመጣል በብስራት በቀለ አማካኝነት የጥቃት መነሻቸውን አድርገው መንቀሳቀስ ሲችሉ በአንፃሩ መድኖች ደግሞ አቡበከር ሳኒን በመጠቀም ከቀኝ ወደ ውስጥ በጥልቀት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሲጫወቱ ተመልክተናል።

የጨዋታውን ቀዳሚ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች በ8ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ተከላካዩ አንተነህ ቢጨርፋትም ከጀርባው ሆኖ ኳሷን ያገኛት አብዲሳ ጀማል ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥታለች።

በጨዋታው የተሻሉ ይመስሉ የነበሩት በመድን ተከላካዮች የተፈተኑት የጦና ንቦቹ በተለይ ከተከላካይ ጀርባ እና ወደ መስመር በሚጣሉ ኳሶች ጫናዎች ለማሳደር ትጋቶች ቢታይባቸውም የመድንን ተከላካዮች ለማለፍ ግን ከብዷቸው ተስተውሏል። ብዙም ልዩነት መፈጠር ባልቻሉበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጨዋታው 34ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ የመድኑ አዲስ ፈራሚ አብዲሳ ጀማል ናትናኤል ናሲሩን በክርን ደረቱ ላይ በመማታቱ በዕለቱ ዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

የተጋጣሚያቸውን የተጫዋች መጉደልን ተከትሎ በይበልጥ መነቃቃት የታየባቸው ድቻዎች 39ኛው ደቂቃ ጥራት ያላትን ዕድል ከመፍጠራቸው ውጪ አባካኞች የነበሩ ሲሆን በተጠቀሰው ደቂቃም ዘላለም ከግራ መስመር እየነዳ የሄደው ኳስ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ ወደ ግብ መቶ የግብ ዘቡ አቡበከር በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶበታል።በ41ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች ቢጫ ተመልክቶ በነበረው ፍፁም ግርማ ምትክ እዮብ ተስፋዬን ከተኩ በኋላ ጨዋታው ያለ ጎል ተጋምሷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ መድኖች ከፍ ባለ ተነሳሽነት የጀመሩ ሲሆን አጥቂዎቻቸውን ያማከሉ ረጃጅም ኳስ በመጠቀም በሁለት አጋጣሚዎች በወላይታ ድቻ የግብ ክልል ደርሰው የነበሩ ቢሆንም ለማጥቃት ትተውት የሚሄዱትን ቦታ ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱት ድቻዎች ግን ሳይጠበቁ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

53ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች ወደፊት የላኩትን ኳስ ሰይድ ሐሰን ለማውጣት በሚያደርገው ጥረት ተንሸራቶ በስህተት ያቀበለውን ኳስ ብስራት በቀለ ግብ ጠባቂው አቡበከርን በማለፍ መረቡ ላይ ኳሷን አሳርፏታል።

በጎዶሎ ተጫዋቾች ረጅሙን ደቂቃ ለመጫወት የተገደዱትን መድኖች 63ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ሀይደርን በአጥቂው መሐመድ አበራ ተክተው ካስገቡ በኋላ ጨዋታውን ወደ መቆጣጠር መምጣት የቻሉ ሲሆን መሐመድ አበራም ተቀይሮ በገባ በሰከንዶች ውስጥ ከአቡበከር ሳኒ ያገኘውን ግልፅ አጋጣሚ ወደ ውጪ የሰደዳት ቢሆንም በደቂቃዎች ልዩነት በ72ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነቷን ግብ ማግኘት ችለዋል።

እዮብ ተስፋዬ በሳጥን ውስጥ ብሩክ ሙሉጌታ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘችዋን የፍፁም ቅጣት ምት አሚር ሙደሲር አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ 1ለ1 ተሸጋግሯል።

ፋታ የለሽ ጫናን ማሳደራቸውን የቀጠሉት መድኖች 74ኛው ደቂቃ ላይ መልካም አጋጣሚን አግኝተዋል። ብሩክ ሙሉጌታ ኳስን ይዞ ወደ ድቻ የግብ ክልል ለመግባት ጥረት ሲያደርግ በአንተነህ ጉግሳ በእጅ በመጎተቱ የተነሳ በቀጥታ ቀይ ካርድ ለመሰናበት ተገዷል። የቁጥር መመጣጠኑ ከተፈጠረ ወዲህ መድኖች ፍፁም የሆነ ብልጫን ወስደው ተጨማሪ ግብን ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ሳይጠበቅ ግብ አስተናግደዋል።

81ኛው ደቂቃ ዘላለም ኢሳያስ ከተከላካይ ጀርባ አመቻችቶ ያቀበለውነሰ ኳስ ብስራት በቀለ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎልን ከመረብ አዋህዷል።

ወደ አቻነት ለመሸጋገር በብርቱ መትጋታቸው የጀመሩት መድኖች በተጨማሪ ደቂቃ ወገኔ ገዛኸኝ በድቻ ተከላካይ መሐል ያሾለከለትን አስደናቃ ኳስ ተጠቅሞ መሐመድ አበራ የቡድኑን የአቻነት ግብ ሲያስገኝ በመጨረሻዎቹ ቅፅበቶችም መድኖች በያሬድ ዳርዛ አማካኝነት የምታስቆጭ ግልፅ ዕድልን አግኝተው የነበረ ቢሆን በቢኒያም ገነቱ ጥረት ግብ ከመሆን በመዳኗ ጨዋታው 2ለ2 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ጠንካራ ጨዋታ እንደነበር ጠቅሰው ነጥቡን ለመያዝ ፈልገው የነበረ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት የሰሯቸውን ስህተቶች በተመሳሳይ ዛሬም መድገማቸው ለውጤቱ መበላሸት ምክንያት መሆኑን እንዲሁም በጨዋታው የተቆጠረችባቸው ሁለተኛ ግብ ከጨዋታ ውጪ መሆናቸውን ሲገልፁ በአንፃሩ የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ በበኩላቸው ጨዋታው መጥፎ አለመሆኑን ጠቁመው በጎዶሎ ተጫዋች ረጅም ደቂቃን ተጫውተው ወደ አቻነት መምጣታቸው የቡድኑን አልሸነፍ ባይነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።