መረጃዎች| 76ኛ የጨዋታ ቀን

የአስራ ዘጠነኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን ነገ በአንድ ጨዋታ ቀጥሎ የሚውል ሲሆን እኛም ጨዋታውን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፋችን አቅርበናል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ሀዋሳ ከተማ

ከአደጋው ክልል ለመራቅ የሚልመው ኢትዮጵያ መድን ተከታታይ ድሎች ካስመዘገቡት ሀዋሳ ከተማዎች የሚያደርጉት ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

በርከት ያሉ ዝውውሮች ፈፅመው ከአደገኛው ቀጠና ለመውጣት በጥረት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች ለአስር ሳምንታት ከናፈቃቸው ድል ለመታረቅ ሀዋሳ ከተማን ይገጥማሉ። መድኖች በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መሻሻል አሳይተው ከተከታታይ ሽንፈቶች ቢርቁም ጨዋታዎች አሸንፈው ደረጃቸው ማሻሻል አልቻሉም። በፊት መስመር ያላቸው ክፍተት ለመሙላት በርከት ያሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ያስፈረሙት መድኖች በቀጣይ ጨዋታዎች ከዚ ቀደም ዋነኛ የቡድኑ ችግር የነበረው የአፈፃፀም ችግራቸው ሙሉ ለሙሉ ፈተው መቅረብ ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ አራት የአቻና አንድ የሽንፈት ውጤቶች ባስመዘገበባቸው ጨዋታዎች አራት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በሦስቱ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖታል። በነገው ዕለትም ቡድኑ የተሻለ የመዘጋጃ ጊዜ አግኝቶ የሚያካሂደው ጨዋታ እንደመሆኑ በአጨዋወትም ሆነ በቋሚ አሰላለፍ ለውጦች የሚያደርግበት ዕድል የሰፋ ነው።

ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገቡት መድኖች ከሽንፈት መራቃቸው ከከባዱ ጨዋታ በፊት በሥነ ልቦናው ጠንክረው እንዲቀርቡ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ነው። ከነገው ጨዋታ ውጤት ማግኘት መቻል ደግሞ በዚህ ረገድ ለቡድኑ ከውጤትም በላይ ፋይዳው ትልቅ ነው።

ከአስከፊው ጉዞ ተላቀው ደረጃቸውን ማሻሻል የቻሉት ሀይቆቹ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በመሀል በፋሲል ከነማ ከገጠማቸው ሽንፈት ውጭ ተከታታይ ድሎች ያስመዘገበው ቡድኑ ከሰንጠረዡ አጋማሽ ይበልጥ ከፍ ብሎ ለመፎካከር ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ መሰብሰብ አስፈላጊው ነው። ሀይቆቹ በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሻሸመኔ ከተማና በጥሩ የመሻሻል ሂደት ላይ ያለው ድሬዳዋ ከተማን አሸንፈዋል፤ ከድሉም በተጨማሪ በሁለቱ ጨዋታዎች ስድስት ግቦች አስቆጥረዋል። በነገው ጨዋታም ካልተዛነፈው ፈጣን የማጥቃት ችግግራቸው ባለፈ በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኙት አጥቂዎቸቸው ለተጋጣሚ ትልቅ ፈተና እንደሚሆኑ ለመገመት አያዳግትም።


ወረቀት ላይ ሲታይ ጨዋታው ለሀዋሳ ከተማ ፈታኝ መስሎ ላይታይ ይችላል። ነገር ግን በዝውውሮች ራሱን ያጠናከረው፤ ከተከታታይ ሽንፈቶች የራቀውና ከአደጋው ክልል ለመራቅ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ የሚጠበቅበት ቡድን ያለብዙ ፈተና ማሸነፍ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

በኢትዮጵያ መድን በኩል አማካዮቹ ሀይደር ሸረፋ እና ንጋቱ ገብረስላሴ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ አብዲሳ ጀማል በቅጣት እንዲሁም አዲስ ፈራሚው አለን ካይዋ የወረቀት ስራዎች ባለማለቃቸው የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል። በሀዋሳ ከተማ በኩልም በተመሳሳይ በመጨረሻው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣው እንየው ካሳሁን በቅጣት ምክንያት በዚ ጨዋታ ተሳትፎ አይኖረውም።

ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ 28 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ 13 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ሲኖረው የመጨረሻ አምስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ጨምሮ በ11 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተው መድን 4 ጨዋታ አሸንፏል። ሀዋሳ ከተማ 36 ፣ መድን 26 አስቆጥረዋል።