ሪፖርት | የኢትዮጵያ መድን እና አሸናፊነት አሁንም መታረቅ አልቻሉም

የዕለቱ ብቸኛ በነበረው መርሃግብር ኢትዮጵያ መድን ተሽለው ባመሹበት ጨዋታ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል።

ኢትዮጵያ መድን በመጨረሻ የሊግ ጨዋታቸው ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ተካልኝ ደጀኔ ፣ ሀይደር ሸረፋ እና አብዲሳ ጀማልን አስወጥተው በምትካቸው ያሬድ ካሳዬ ፣ ዮናስ ገረመው እና ጄሮም ፊሊፕ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ሲያስጀምሩ በአንፃሩ በሀዋሳ ከተማዎች በኩል ድሬዳዋ ከተማን ከረታው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ መድሀኔ ብርሃኔ እንየው ካሳሁን ተክቶ በዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ጀምሯል።

ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን አለልኝ አዘነን በማሰብ የጀመረው ጨዋታ ፈጣን አጀማመርን ያስመለከተን ነበር ፤ በኢትዮጵያ መድን መለያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገው ጄሮም ፊሊፕ ሙከራ በጀመረው ጨዋታው ሀዋሳ ከተማዎች ገና በ3ኛው ደቂቃ ነበር መሪ መሆን የቻሉት።

ዓሊ ሱሌይማን ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ በአቡበከር ኑራ ሲመለስበት በቅርብ ርቀት የነበረው ተባረክ ሄፋሞ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ በቀጥታ በመምታት ከመረብ ባዋሃዳት ኳስ ሀዋሳ ከተማዎች መሪ መሆን ችለዋል።

ግብ ካስተናገዱ በኃላ ኢትዮጵያ መድኖች በትዕግሥት ኳሱን በመቆጣጠር ተጋጣሚያቸውን ለማስከፈት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ሀዋሳ ዓሊ ሱሌይማንን ታሳቢ ባደረጉ በረጃጅም ከሚጣሉ ኳሶች ከሚደረጉ ሙከራዎች በዘለለ በአጋማሹ በብዙ መልኩ ሁለተኛ ሆነው ያሳለፉበት ነበር።

በአጋማሹን ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት መድኖች መሀል ለመሀል ሆነ ከመስመሮች በሚሻገሩ ኳሶች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዋል ፤ በዚህም በ37ኛው ደቂቃም የሚገባቸውን የአቻነት ግብ አግኝተዋል። መሀል ሜዳ ላይ አሚር ሙደሲር ባቋረጣት ኳስ የጀመረው የማጥቃት እንቅስቃሴ ወገኔ ገዛኸኝ ከአዲሱ ፈራሚ ጄሮም ፊሊፕ የደረሰውን ኳስ በቀላሉ በማስቆጠር አጋማሹ በአንድ አቻ ውጤት ወደ ዕረፍት እንዲያመራ ምክንያት ሆኗል።

ሀዋሳ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ እስራኤል እሸቱ እና አቤነዘር ዮሀንስን ተክተው ቢጀምሩም ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ነበር ወደ መመራት የተሸጋገሩት ፤ በ46ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ በሀዋሳ ተከላካዮች ስህተት ታግዞ ከመሀል ሾልኮ በመውጣት ቡድኑን መሪ ያደረገችውን ግብ አስቆጥሯል።

ነገርግን ጥሩ መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት የኢትዮጵያ መድኖች ሳይጠበቅ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል በዚህም በ58ኛው ደቂቃ ሲሳይ ጋቾ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ለመቆጣጠር ግቡን ለቆ የወጣው አቡበከር ኑራ ኳሷን መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ ኳሷን ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን በቀላሉ ኳሷን ከመረብ በማዋሀድ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መመለስ ችሏል።

ምንም እንኳን በድንገት ግብ ቢያስተናግዱም በተረጋጋ ሁኔታ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ መድኖች በ62ኛው ደቂቃ ወገኔ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ያደረጋት እንዲሁም በ70ኛው ደቂቃ ያሬድ ካሳዬ ከቆመ ኳስ ያደረገው ሙከራ በአብዱልባሲጥ ከማል ተጨርፋ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት ሙከራ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ደካማ በነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በኩል በግሉ የተሻለ ጥረት ሲያደርግ ያመሸው ዓሊ ሱሌይማን 72ኛው ደቂቃ ላይ በግሉ ጥረቱ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብ ቢልክም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ለትማ ልትመለስ ችላለች።

በአጋማሹ ቀሪ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ መድኖች በአውንታዊ አጨዋወት አሸናፊ ሊሆኑ የሚችሉባትን ግብ ፍለጋ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሀዋሳ ከተማዎች በጠንካራ መከላከል ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ይዘውት የመጡት የጨዋታ ዕቅድ ውጤታማ እንዳልነበረ ገልፀው በጥቅል የቡድናቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀው በቀጣይ ይህን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ወደ አሸናፊነት በመመንዘር ቡድናቸው ላይ የሚስተዋለውን ጫና ለማስወገድ እንደሚጥሩ ገለፀዋል በአንፃሩ የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ደግሞ ጨዋታው መሀል ክፍላቸው እና የአጥቂ መስመራቸው ቅንጅት ጥሩ እንዳልነበረ አንስተው ከጨዋታ ጨዋታ ቡድናቸው መሻሻል እያሳየ ባለበት ጊዜ ሊጉ መቋረጡ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸውም አንስተዋል።