ሪፖርት| የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ መሪነት የሚመጣበትን ዕድል አምክኗል

የብርቱካናማዎቹ እና የሀምራዊ ለባሾቹ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል።

ንግድ ባንኮች ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አሰላለፍ
እንዳለ ዮሐንስና ሀብታሙ ሽዋለም በካሌብ አማንክዋህና አዲስ ግደይ ተክተው ሲገቡ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ከገጠመው ቋሚ አሰላለፍ ሄኖክ አንጃውና አሜ መሐመድ በአቤል አሰበና ሄኖክ ሀሰን ተክተው ገብተዋል።

እንደተጠበቀው በሙከራዎች ያልታጀበው የመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታ ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖረውም ጨዋታውን በመቆጣጠር ረገድም ይሁን የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ግን ብርቱካናማዎቹ ናቸው። ድሬዳዋ ከተማዎች ሁለቱም የመስመር ተከላካዮች ያሳተፈና ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ስያደርጉ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው በአመዛኙ የተጋጣሚ ተከላካዮች ከጀርባ የሚተውትን ክፍት ቦታ ተጠቅመው በረዣዥም ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፤ ሆኖም ከተደጋጋሚ የጨዋታ ውጭ አቋቋም በዘለለ ይህ ነው የሚባል ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ባሲሩ ዑመር ጨዋታው እንደተጀመረ አዲስ ግደይ በጥሩ ሁኔታ ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት እጅግ ሙከራም ብቸኛዋ ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።

አደገኛው የሜዳው ክፍል ጥቅጥቅ ብለው በመሸፈን ተጋጣሚያቸው የግብ ዕድሎች እንዳይፈጥር ካደረጉት ውጤታማ ስራ በተጨማሪ በመስመር ተከላካዮቻቸው መነሻነት የግብ ዕድሎች የፈጠሩት ብርቱካናማዎቹ በተጠቀሰው አጨዋወት በርከት ያሉ ዕድሎች ፈጥረዋል። በአስራ አራተኛው ደቂቃም ጥረታቸው ሰምሮ በቻርለስ ሙሴጌ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። አጥቂው መሐመድ ዓብዱለጢፍ ከመስመር ያሻገራትን ኳስ ፈቱዲን ጀማል ሳይቆጣጠራት በመቅረቱ በጥሩ አዟዟር ከመረብ ጋር ቀላቅሏታል። ድሬዎች ከግቧም በኋላ በመልሶ ማጥቃት ወርቃማ አጋጣሚ ቢያገኙም በዘርአይ ገብረስላሴ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር በሁሉም ረገድ የወረደ እንቅስቃሴ የታየበት አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ ተስፋ ሰጪ የማጥቃት ሂደት የነበራቸው ብርቱካናማዎቹ ቻርለስ ሙሴጌን በጉዳት ካጡ በኋላ የፊት መስመሩ ጥንካርያቸው አጥተዋል። ከዚ በተጨማሪ የመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ መገደብም የራሱን አስተዋፆ አድርጓል። ሆኖም በአሜ መሐመድ አማካኝነት ባደረጓቸው ሁለት ሙከራዎች መሪነታቸውን ለማስፋት ተቃርበው ነበር። አጥቂው በንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ፍሬው ስህተት አማካኝነት ያገኛትን ኳስ ከኤፍሬም አሻሞ በጥሩ ሁኔታ ተቀባብሎ ያደረጋት ሙከራም የአጋማሹ ወርቃማ ዕድል ነበረች። ከዚ በተጨማሪ በተመሳሳይ መንገድ በተከላካዮች የቅብብል ስህተት አግኝቷት ወደ ግብነት ያልቀየራት ዕድልም ትጠቀሳለች። ያለው ወትሮ የተዳከመ የፊት መስመር የነበራቸው ንግድ ባንኮች ይህ ነው የሚባል የጥራ ዕድል ሳይፈጥሩ ከቆዩ በኋላ በሰማንያኛው ደቂቃ በሲሞን ፒተር አማካኝነት የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል።

ኪቲካ ጅማ ከመስመር ተሻግራ አጥቂዎች ያልተጠቀሟትን ኳስ አግኝቶ ከመታት በኋላ ግብ ጠባቂው ሲተፋት ከግቡ ቅርብ ርቀት የነበረውና ተቀይሮ የገባው ሲሞን ፒተር ከግቡ ጋር አዋህዷት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቧ በኋላም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተደርገዋል። በንግድ ባንክ በኩል ፈቱዲን በረዥሙ አሻግሯት አቤል በግንባሩ ገጭቷት ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና ያዳናት ኳስ፤ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ የጨዋታው መጠናቀቅ የምታበስር ፊሽካ ከመነፋትዋ በፊት ከመአዝን ምት ያደረጓት ሙከራና ካሌን አማንካዋህ እንደምንም ጨርፎ ያወጣት ኳስ ትጠቀሳለች።

ጥቂት የግብ ሙከራዎች ያስመለከተው ጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ መሪነት የሚመጣበትን ዕድል አምክኗል።