ሪፖርት | እጅግ ወሳኙ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል

በሰንጠረዡ ሁለት ዕንፎት ትልቅ ዋጋ የነበረው እና ማራኪ ፉክክር የተደረገበት የመቻል እና የሻሸመኔ ከተማ ጨዋታ 2ለ2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

መቻሎች በ25ኛው ሳምንት ሀዋሳን 3ለ2 ካሸነፉበት አሰላለፍ ነስረዲን ኃይሉ ፣ ግሩም ሀጎስ እና ዮሐንስ መንግሥቱን አስወጥተው አስቻለው ታመነ ፣ ግርማ ዲሳሳ እና ሳሙኤል ሳሊሶን ሲያስገቡ ሻሸመኔዎች በአንጻሩ በ25ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 የተሸነፉበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ቀርበዋል።

09፡00 ሲል በፌደራል ዳኛ ዓባይነህ ሙላት ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ መቻሎች በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው መጫወት ቢጀምሩም እጅግ የተደራጀው የሻሸመኔ ከተማ የመከላከል መዋቅር በተደጋጋሚ የመቻል ተጫዋቾችን ከጨዋታ ውጪ ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ያፈራበት ነበር።

በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ ፍላጎት እየታየበት በቀጠለው ጨዋታ መቻሎች የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድል ፈጥረው ግርማ ዲሳሳ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ከነዓን ማርክነህ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጨዋታው 30ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ በግሩም ዕይታ ያመቻቸለትን ኳስ በሳጥኑ የግራ ክፍል በመግባት ያገኘው አብዱልቃድር ናስር በጥሩ አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፏት ሻሸመኔን መሪ አድርጓል።

መቻሎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር መታተር ሲችሉ 40ኛው ደቂቃ ላይም በረከት ደስታ በጥሩ ሁኔታ ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ለሽመልስ በቀለ አመቻችቶለት ሽመልስም ያደረገው ሙከራም ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

እጅግ ምርጥ የሆነውን እንቅስቃሴያቸውን ያሳዩት ሻሸመኔዎች 43ኛው ደቂቃ ላይ ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረው እዮብ ገብረማርያም ካባከነው በኋላ የመስመር አጥቂው ከአንድ ደቂቃ በኋላ ከጨዋታ ውጪ በሚመስል እንቅስቃሴ የወሰደውን ኳስ ወደ ሳጥን መሬት ለመሬት አሻግሮት ኳሱን ያገኘው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ኳሱን ተቆጣጥሮ ዳዊት ማሞን በመሸወድ በአስደናቂ መረጋጋት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከተገመተው ተቃራኒ በነበረው አጋማሽ መቻሎች ሁለተኛ ግብ አስተናግደው ኳሱን ከመሃል ሜዳ በጀመሩበት ቅፅበት ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ጎል አግኝተዋል። በዚህም 45+1ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተከላካዮች በደንብ ሳያፀዱት ቀርተው በረከት ደስታ ግብ አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ቀጥሎ ሻሸመኔ ከተማዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ካደረጉ በኋላ 51ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው የነበረ ሲሆን እዮብ ገብረማርያም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አብዱልቃድር ናስር ካመቻቸው በኋላ ማይክል ኔልሰን ወደ ግብ ሞክሮት አስቻለው ታመነ ተደርቦ አውጥበታል።

መቻሎች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ማሻሻል ሲችሉ 57ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። አብዱ ሙታላቡ ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ ሽመልስ በቀለ ለምንይሉ ወንድሙ አመቻችቶለት አጥቂው ከሳጥን ጠርዝ ላይ የመታው ኳስ የግብ ጠባቂውን ኬን ሳይዲን እጅ ጥሶ ግብ ሆኗል።

ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ መቻሎች 58ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ እየገፋ ወስዶ ሞክሮት በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት በወጣበት ኳስ የተጋጣሚን ሳጥን ማስጨነቅ ቢቀጥሉም የሻሸመኔ የኋላ መስመር ርብርብ ሲመክታቸው ውሏል።

በመቻሎች በኩል 82ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ በሳጥኑ የግራ ክፍል ገብቶ ሙከራ ካደረገ በኋላ 88ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ ግብ ቢያስቆጥሩም ግብ ጠባቂው ላይ ጥፋት ተሠርቷል በሚል ግቡ በአወዛጋቢ ሁኔታ ሳይፀድቅ ቀርቷል። ጨዋታውም 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡት አስተያየቶች አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በጨዋታው በሁሉም መመዘኛዎች የተሻሉ እንደነበሩ ተናግረው በጨዋታው በእጃቸው የገባውን ውጤት ማስጠበቅ አለመቻላቸው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ የተቆጠረባቸው ግብ እንዳስቆጫቸው ሲገልጹ በአንጻሩ የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በጨዋታው ዙርያ ቅር የተሰኙበትን ሀሳብ ቢገልፁ ለቅጣት እንደሚዳረጉ ተናግረው ሀሳባቸውን እንደማይሰጡ የገለፁ ሲሆን ቀሪ አራት ጨዋታዎች ስላሉ እስከ መጨረሻው ለመታገል ዝግጁ ስለመሆናቸው ገልፀዋል።