ሪፖርት | ሠራተኞቹ ሰባተኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደዋል

በምሽቱ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና ወልቂጤ ከተማን 4ለ0 በማሸነፍ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

በምሽቱ መርሐግብር ወልቂጤዎች በ26ኛው ሳምንት በድሬዳዋ 3ለ0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ በርካታ ተጫዋቾችን በ “የ5 ወር ደመወዝ ይከፈለን” ጥያቄ በማጣታቸው ምክንያት መሳይ ጳውሎስ ፣ መድን ተክሉ እና ወንድማገኝ ማዕረግን ብቻ አስቀጥለዋል። ቡናማዎቹ በአንጻሩ ሀምበርቾን 6ለ1 ካሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አብዱልከሪም ወርቁ እና አንተነህ ተፈራ ወጥተው ስንታየሁ ወለጬ እና ጫላ ተሺታ ገብተዋል።


12፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የወሰዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ገና በ7ኛው ደቂቃ ነበር ለግብ የቀረበውን ጥቃት የሰነዘሩት ፣ በዚህም አማኑኤል አድማሱ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ቡናማዎቹ በከፍተኛ የራስ መተማመን ጨዋታውን በመቆጣጠር 16ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በዚህም ከራሳቸው የግብ ክልል በፍቃዱ ዓለማየሁ ለስንታየሁ ወለጬ ያቀበለውን ኳስ አማካዩ ወደፊት ሲሰነጥቀው አማኑኤል አድማሱም የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረገበት ቦታ ላይ በጥሩ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

ወልቂጤ ከተማዎች ደካማ በሆነው አቀራረባቸው በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመጠጋት መጫወትን ሲመርጡ በዚህም 26ኛው ደቂቃ ላይ ተቀጥተዋል። አማኑኤል ዮሐንስ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ ከተከላካዮች ሾልኮ በመውጣት ያገኘው መሐመድኑር ናስር ኳሱን ሳይነካ ግብ ጠባቂውን ካታለለው በኋላ ኳሱን በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በሁለት ግቦች መመራት ከጀመሩ በኋላ በመጠኑ የተነቃቁት ሠራተኞቹ የመጀመሪያ ሙከራቸውን 32ኛ ደቂቃ ላይ አድርገው ፉዓድ አብደላ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ሲያስወጣበት 43ኛው ደቂቃ ላይም አድናን ፈይሰል ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 48ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ጫላ ተሺታ ከበፍቃዱ ዓለማየሁ ተቀብሎ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ቀጥሎ 62ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል አድማሱ የአጋማሹን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ናትናኤል ጃምቦ አግዶበታል።

በሁለቱም በኩል ጨዋታው ለመጠናቀቅ የተቃረበ በሚመስል ሁኔታ እጅግ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ ሠራተኞቹ ወደራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በሰፊ የግብ ልዩነት ላለመረታት መከላከልን ሲመርጡ 78ኛው ደቂቃ ላይ መድን ተክሉ ያለቀለት የግብ ዕድል አግኝቶ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

ቡናማዎቹ የጨዋታ ደቂቃ ተነፍገው ለነበሩት ተጫዋቾቻቸው ዕድል በመስጠት በኳስ ቁጥጥሩ ያላቸውን ብልጫ አስቀጥለው 87ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ኃይለሚካኤል አደፍርስ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው አንተነህ ተፈራ በቀላሉ ግብ ማስቆጠር ችሏል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴዎች ሳይደረጉ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሴኮንዶች ሲቀሩ 90+6ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ ወለጬ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 4ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ከቡድኖቹ ወቅታዊ ሁኔታ እና ከጨዋታው አንጻር ውጤቱ የተጠበቀ እንደሆነ ጠቁመው ክለቡ በሊጉ መቆየት የሚፈልግ ከሆነ ተጫዋቾቹ ላይ ያለውን ጥያቄ እንዲፈታ አበክረው በመግለጽ ዓመቱን ሙሉ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ እያለፉ ደጋፊዎቻቸው እና አመራሮቻቸው ችላ ያሉበት ምክንያት ሊገባቸው እንዳልቻለ ሀሳባቸውን ሲሰጡ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ ጨዋታውን ቀድመው እንደተዘጋጁበት እንዳገኙት እና በጨዋታው ቀድመው ጎል ማስቆጠራቸው የተጋጣሚያቸውን ስነልቦና በማውረዱ በኩል እንደጠቀማቸው በምክትል አሰልጣኝነት ያገለገሉበት ወልቂጤ ከተማ ያለበት ችግር አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው መፍትሔ እንዲፈለግጉት በመጠቆም እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው በማጠናቀቅ የኢትዮጵያ ዋንጫን ካነሱ ትልቅ ስኬት እንደሚሆንላቸው ተናግረዋል።