ኢትዮጵያ በፊፋ የሃገራት ደረጃ አሽቆልቁላለች

ፊፋ በየወሩ በሚያወጣው የኮካኮላ ፊፋ የሃገራት ደረጃ ኢትዮጵያ 11 ደረጃዎችን አሽቁልቁላለች፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኩማሲ ላይ 5-0 የተሸነፉት ዋሊያዎቹ በሰኔ ወር ያደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሲሆን ከዩጋንዳ ጋር የተደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ በፊፋ የታወቀ ባለመሆኑ በነጥብ አያያዙ ላይ አልተካተተም፡፡

ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ወር 125ኛ የነበረች ቢሆንም በአሁኑ ወር 11 ደረጃዎችን ወደ ኃላ ተጉዞ 136ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ ከ265 ነጥብም ወደ 215 ነጥብ ወርዳለች፡፡ ኢትዮጵያ በ2009 በፊፋ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ኃላ መጓዟን ቀጥላለች፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለረጅም ግዜ የፊፋ ፕሮግራምን በተከተለ መልኩ ያለደረገ ከመሆኑ ባሻገር በማጣሪያ ጨዋታዎችም ውጤት ከራቀው ሰነባብቷል፡፡ ዋሊያዎቹ ላይ አምስት ግብ ያዘነበችው ጋና ከአለም 50ኛ ስትሆን፣ በምድቡ የሚገኙት ሴራሊዮን እና ኬንያ 83 እና 84ኛ ናቸው፡፡ ኬንያ 10 ደረጃዎችን ስትቀንስ የሃራምቤ ከዋክብቶቹን ፍሪታውን ላይ ማሸነፍ የቻለችው ሴራሊዮን 30 ደረጃዎችን ከፍ ብላለች፡፡

በቻን ማጣሪያ ኢትዮጵያን የምትገጥመው ጅቡቲ ከ206 ሃገራት በ64 ነጥብ 185ኛ ላይ ትገኛለች፡፡ የአፍሪካ የበላይነቱን አሁንም ግብፅ ስትይዝ ሴኔጋል፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ፣ ቱኒዚያ እና በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ከምደብ የዘለለ ተሳትፎ ያላደረገችው ካሜሮን ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ናይጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ አልጄሪያ፣ ጋና እና ኮትዲቯር ከ6-10 ያሉት ደረጃዎች መያዝ የቻሉ የአፍሪካ ሃገራት ናቸው፡፡ የአለም እና የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመን አንደኛ ስትሆን ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ፖርቹጋል፣ ስዊዘርላንድ፣ ፖላንድ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ፈረንሳይ እና ቤልጂየም እስከ10 ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *