የውድድር ዘመኑ ምርጥ 10 የውጭ ዜጋ ተጫዋቾች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ጨምሮ የሀገር ውስጥ ውድድሮች እና ክለቦቻችን የሚሳተፉባቸው የአፍሪካ ውድድሮች በአመዛኙ ተገባደዋል፡፡ በዚህ የዘንድሮው የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ክለቦች ከ40 በላይ የውጪ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን የተጠቀሙ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም በዛሬው ምርጥ 10 ዝግጅቷ በ2009 የውድድር አመት ምርጥ አቋማቸውን ያሳዩ 10 የውጪ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን ተመልክታለች፡፡

1 አብዱልከሪም ኒኪማ

የቅዱስ ጊዮርጊስን የዘንድሮውን የአማካይ ክፍል ከኒኪማ ውጪ ብናስበው እጅግ በጣም ደካማ ሆኖ እናገኘዋለን። ወትሮም ቢሆን ጥያቄ የሚነሳበት የቻምፒዮኖቹ የመሀል ክፍል የድክመቱን ያህል እንዳይጋለጥ ምክንያት የሆነው ቡርኪናፋሷዊው አብዱልከሪም ኒኪማ ነው። በታታሪነቱና አብዛኛውን የሜዳ ክፍል አካሎ በመጫወት በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ጊዜ ያልወሰደበት ኒኪማ ቅርፁን በሚቀያይረው የቡድኑ የአማካይ ክፍል ውስጥ የመጀመሪያ ተመራጭ ነበር። በሁለተኛው ዙር የተወሰኑ ጨዋታዎች ላይም በመስመር አጥቂነት የተጫወተው ኒኪማ ከቡድኑ ተሰላፊዎች መካከል ከኳስ ጋር ምቾት የሚሰማው እና ጥሩ እይታ ያለው ተጨዋች ከመሆኑ ባሻገር ለቡድኑ የተለየ ሚናን በመወጣት አማራጭ የሚፈጥር ተጨዋች መሆኑን አሳይቷል ።

2 ጃኮ አራፋት

በተለያዩ ሀገራት የመጫወት ልምድ ያለው ጃኮ በመጀመርያ አመት የሀዋሳ ከተማ ቆይታው ምርጥ አቋሙን አሳይቷል፡፡ በባህርዩ የሳጥን አጥቂ ባይሆንም 13 ጎሎች በማስቆጠር ከውጪ ተጫዋቾች ከፍተኛውን ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡

እስከ መሀለኛው የሜዳ ክፍል በጥልቀት በመሳብ ቡድኑ የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ጥረት ሲያደርግ የሚስተዋለው ጃኮ በዚህ ሒደትም በርካታ ኳሶችን ለግብ አመቻችቶ እንዲያቀብል አስችሎታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለሌሎች የቡድኑ ተጫዋቾች (ጋዲሳ መብራቴ ፣ ፍሬው ሰለሞን እና ታፈሰ ሰለሞን) የማጥቃት ቀዳዳ በመፍጠር የግብ እድል ከመፍጠር አልፈው በርካታ ጎሎች እንዲያስቆጥሩ ወሳኝ ሚና መጫወት ችሏል፡፡

ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ዝውውር ጋር እየተያያዘ የሚገኘው ጃኮ አራፋት ምናልባትም ከኢትዮጵያ ውጪ በሚገኙ ክለቦች ልንመለከተው የምንችለው ተጫዋች ነው፡፡

3 አዳሙ መሀመድ

በ2003 ወደ ኢትዮጵያ የመጣው አዳሙ መሀመድ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ሰፊ ልምድ አለው፡፡ በደደቢት መልካም ጊዜያት አሳልፎ በ2007 የውድድር ዘመን መቀዛቀዝ ቢያሳይም ወደ ወልድያ ካመራ ወዲህ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት ምርጥ አቋሙን አሳይቷል፡፡ በተለይ ዘንድሮ በመከላከል አጨዋወቱ ከሊጉ ክለቦች የተሻለ በነበረው ወልድያ የተከላካይ መስመርን በመምራት ምርጥ አቋሙን አበርክቷል፡፡ አመዛኝ ጨዋታዎችን በአንድ ግብ ልዩነት የሚያሸንፈው ወልድያ አዳሙን ባይዝ ምናልባትም ዘንድሮ ያሳካውን ነጥብ ላይሰበስብ ይችል ነበር ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

4 ክሪዚስቶም ንታንቢ

ጅማ አባ ቡና በመጀመሪያ ተሳትፎው ብዙ ጥሩ ነገሮችን አሳይቶ በሊጉ መቆየት ያልቻለ ክለብ ነው። ዩጋንዳዊው አማካይም በዚህ መልኩ ሊጠቀስ የሚችል ነው ። በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ክለቡን ከተቀላቀለ በኃላ በአዲስ አበባ ዋንጫ ውድድር ላይ ባሳየው ደካማ አቋም በብዙዎች ተተችቶ የነበረው ንታንቢ ሊጉ ከጀመረ በኋላ ግን ይህን ሀሳብ ፉርሽ ያደረገ የውድድር አመት አሳልፏል ። በመጀመሪያው ዙር ሁሉንም ጨዋታዎች መሰለፍ የቻለው ንታንቢ በተከላካይ አማካይነት ወጥ የሆነ ብቃት በማሳየት በሊጉ ካሉ ተጨዋቾች መሀከል በቦታው ዋና ተጠቃሽ ያደረገውን አቋም አሳይቷል። አባ ቡና አሰልጣኝ ደረጄ በላይን በ አሰልጣኝ ገ/መድህን ሀይሌ ከተካ በኃላም ተጨዋቹ ከ አዲስ ፈራሚው ኄኖክ ካሳሁን ጋር ለመጣመር ጊዜ አልፈጀበትም። በሁለተኛው ዙር ከዚህ ሚናው በተጨማሪም በአስር ቁጥር ቦታ ላይ እንዲጫወት መደረጉ ቢያስገርምም ተጨዋቹ ይሄኛውንም ሚና በጥሩ ብቃት በመወጣት ለቡድኑ አዲስ አይነት አማራጭን ሰጥቷል። ከክለቡ ጅማ አባ ቡና ባለፈ ንታንቢ ባሳለፈው ጥሩ የውድድር አመት በሁለት አጋጣሚዎች በአሰልጣኝ ሚቾ የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ መካተት ችሏል ።

5 ኤሚክሪል ቤሊንጌ

በሊጉ ከሚገኙ እና የጨዋታ አቀራረባቸው በግልፅ ከሚታወቁ ጥቂት ክለቦች ውስጥ ወልድያ አንዱ ነው ። ክለቡ በተለይም ከሜዳ ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ለሚከተለው ጥብቅ መከላከል ውጤታማነት ከተከላካይ ክፍሉ ጋር አብሮ ሚነሳው ግብ ጠባቂው ኤሚክሪል ቤሊንጌ ነው። በሊጉ በተደረጉ ሁሉም ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈው ቤሊንጌ ለወልድያ በሊጉ መቆየት ጉልህ ሚና ነበረው። ጠንካራ ግብ ጠባቂ መሆኑ ከፊቱ ለሚሰለፉት አራት ተከላካዮች በራስ መተማመን መጨመር እና በእርጋታ መጫወት ምክንያት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ቤሊንጌ ያዳናቸው  ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኳሶችም እንደተጨዋቹ መልካም ብቃት ባይሆን ኖሮ የቡድኑን ውጤት ችግር ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ነበሩ ። በዚህም ረገድ ለወልድያ ዘንድሮ በሊጉ መቆየት የግዙፉ ግብ ጠባቂን ሚና ከፍተኛ መሆኑን መናገር ይቻላል ።

6 ካድር ኩሊባሊ

ብዙዎች በአካላዊ ጥንካሬው እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት በሜዳ ላይ በሚወስናቸው ኃይል የተቀላቀለባቸው ውሳኔዎች ለይተው ያውቁታል። በእርግጥም ድንቅ የሆነ ኳስ የማስጣል ብቃት አለው ። የኮትዲቫር ተወላጁ ኩሊባሊ ደደቢትን በዘንድሮው የውድድር አመት ከተቀላቀለ በኃላ በአመዛኙ በመሀል ተከላካይነት የውድድር አመቱን የጀመረ ሲሆን ቀስ በቀስ ግን በዋነኝነት በተከላካይ አማካይነት ሚና ላይ በመጫወት አመቱን አሳልፏል።

ኩሊባሊ በተለይ ከተከላካዮች ፊት በተለይም በሜዳው መሀል ለመሀል የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን እና የአየር ላይ ኳሶችን በማክሸፍ ወሳኝ ሚና ተወጥቷል። ቡድኑ በብዛት ሁለት አማካዮችን ከተከላካዮች ፊት በሚያጣምርባቸው አጋጣሚዎች ከአስራት መገርሳ ፣ ኤቤል እንዳለ እና ሳምሶን ጥላሁን ጋር በመጣመር ያሳለፈው ኩሊባሊ አብረውት ለሚጣመሩ ተጨዋቾች የጨዋታ ነፃነትም የጎላ ሚና ነበረው ።

7 ሰንደይ ሙቱኩ

ኬንያዊው ሰንደይ በአመቱ መጀመርያ ሰዳማ ቡናን ከተቀላቀለ ወዲህ አቋሙ ሳይዋዥቅ የውድድር ዘመኑን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ የሰነደይ ከሌሎች የሚለየው ደግሞ በአመቱ በተለያዩ ሚናዎች እና የመጫወቻ ቦታዎች ላይ ተሰልፎ ተመሳሳይ ግልጋሎት ማበርከቱ ነው፡፡

በተከላካይ አማካይነት ፣ በመሀል ተከላካይነት እንዲሁም በመስመር ተከላካይነት ድንቅ አመት ሲያሳልፍ እስከ አመቱ መጨረሻ ጨዋታዎች ድረስ ድነንቅ ጉዞ አድርጎ በነበረው ሲዳማ ቡና ጠንካራ የተከላካይ መስመር ጥምረት ላይ ወሳኝ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል፡፡

8 ሀሪሰን ሄሱ

አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ ሲል የውድድር ዘመኑን በጨረሰው ኢትዮጵያ ቡና ወጥ አቋሙን ማሳየት የቻለው ሀሪሰን ሄሱ ብቻ ነው፡፡ ቡድኑ በተለይ በጥሩ አቋም በተገኘበት የጥር ወር በ6 ጨዋታ አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ በሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጥ ቡድን ውስጥ ሲካተት በአመቱ መጨረሻ ጨዋታዎች የቡድኑ ተጫዋቾች ከደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ በአንጻሩ ሙገሳ ሲቸረው መሰማቱ ምን ያህል በደጋፊዎች እንደሚወደድ ማሳያ ሆኗል፡፡

ሁለተኛ የውድድር ዘመኑን ያሳለፈው ሄሱ እንደ ድክመት ይቆጠሩበት የነበረውን የትኩረት እና በጨዋታ እንቅስቃሴ በመሳብ የሚፈጥረው የቦታ አጠባበቅ ችግርን መቅረፍ ችሏል፡፡

9 መሃመድ ሲይላ

ሀዋሳ ከተማ በመጀመሪያው ዙር በማጥቃት እና ግቦችን በማስቆጠር መጥፎ አልነበረም። ሆኖም ቡድኑ በየጨዋታው ያስተናግድ የነበረው የግብ መጠን በ13ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦት ነበር። በሁለተኛው ዙር መጀመሪያ ላይ ኮትዲቯራዊው የመሀል ተከላካይ መሀመድ ሲይላን ከሱዳኑ አልሀሊ ሼንዲ በነፃ ዝውውር ካገኘ በኃላ ቡድኑ በመከላከል ረገድ በእጅጉ መሻሻልን አሳይቷል። ሲላም ሊጉን መሀል ላይ ቢቀላቀልም ከወጣቱ ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ ጋር የፈጠረው ጥምረት በተለይም በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ላይ ሀዋሳ በቀላሉ መረቡ እንዳይደፈር እና በቶሎ ነጥቦችን እንዲሰበስብ አግዞታል። ክለቡ በሁለተኛው ዙር ባደረጋቸው የመጀመሪያ ስድስት ጨዋታዎችም አንድ ግብ ብቻ ነበር ያስተናገደው ። ተጨዋቹ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ራሱን ከክለቡ እና ከሊጉ ጋር አላምዶ ወሳኝ ተጨዋች እስከ መሆን መድረሱ ብዙዎች ክለቡ በአመቱ መጀመሪያ ላይ ተጨዋቹን አግኝቶ የነበረ ቢሆን ኖሮ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሊገባ ይችል እንደነበር እንዲያስቡ አድርጓል።


10 ኢብራሂም ፎፋና

የፎፋና አጀማመር በአትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ምርጡ የውጪ ተጫዋች እንደሚሆን ፍንጭ የሰጠ ነበር፡፡ በተለይ በአአ ከተማ ዋንጫ ያሳየው አቋም ለመስመር ተከላካዮች የራስ ምታት ነበር፡፡ ሆኖም የውድድር ዘመኑ እየተጋመሰ ሲመጣ የተጫዋቹ አቋም ቀስ በቀስ እየተቀዛቀዘ መጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እጅግ ደካማ የማጥቃት አጨዋወት አንጻር ፎፋና በግሉ መልካም የውድድር አመት አሳልፏል፡፡

ሊጠቀሱ የሚገባቸው ሌሎች ተጫዋቾች

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሮበርት ኦዶንካራ በጉዳት ምክንያት በርካታ ጨዋታዎች ቢያልፉትም በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ድንቅ አቋሙን አሳይቷል፡፡ የአዳማ ከተማው ጃኮ ፔንዜም ሌላው መልካም አመት ያሳለፈ ግብ ጠባቂ ነው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፕሪንስ እና የሲዳማ ቡናው ላኪ ሳኒ 10 ውስጥ ከተካተቱት አንጻር ጥቂት ጨዋታ ቢያደርጉም በተሰለፉባቸው ጨዋታዎች ምርጥ አቋማቸውን አሳይተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *