የሞሮኮው ኢቲሃድ ታንገ ለኢትዮጵያዊው ተከላካይ የሙከራ ጊዜ ሰጥቷል

በሞሮኮ ቦቶላ ፕሮ ሊግ የሚሳተፈው ኢቲሃድ ታንገ ለኢትዮጵያዊው ተከላካይ ሙጂብ ቃሲም የሙከራ ጊዜ ሰጥቷል፡፡ የብሔራዊ ቡድን እና የአዳማ ከተማው ተጫዋች ሙጂብ ወደ ስፍራው ለሙከራ ዛሬ ምሽት 5፡00 ሰዓት ወደ ስፍራው ያመራል፡፡

በሞሮኮው ክለብ የሙከራ ጊዜን በማግኘቱ ምክንያት ሙጂብ በቻን ማጣሪያ ላይ ከሚገኘው የዋሊያዎቹ ስብስብ ውጪ የሆነ ሲሆን በኢቲሃድ ታንገ የ20 ቀናት የሙከራ ግዜን ያሳልፋል፡፡ ከአዳማ ጋር የአንድ አመች ኮንትራት ያለው ሙጂብ በተሰጠው ቀናት ክለቡን ማሳመን ከቻለ የውል ስምምነት ይፈርማል፡፡

ከአዳማ ከተማ በፊት በሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የተሳካ ቆይታ የነበረው ሙጂብ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዳማ ከተማ ከተከላካይነት እስከ አጥቂነት በተለያዩ ሚናዎች የተጫወተ ሲሆን በውድድር ዘመኑ በአጥቂነት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ወሳኝ ግቦችን ለአዳማ ከተማ አስቆጥሯል፡፡ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ብሄራዊ ቡድን ውስጥም ቋሚ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ በጋና 5-0 ስትሸነፍ እና በቻን ማጣሪያ ጅቡቲን 5-1 ስትረታ ተጫዋቹ በቋሚነት መሰለፍም ችሏል፡፡

በታንገ ከተማ መቀመጫወን ያደረገው በሙሉ ስሙ ኢትሃድ ሪያዲ ታንገ (ዩኒየን ስፖርቲቭ ኦፍ ታንገ) የተመሰረተው በ1983 በሁለተኛው የሞሮኮ እግርኳስ ዲቪዚዮን በሚወዳደሩ ክለቦች ውህደት ነው፡፡ በሰሜን ሞሮኮ በተለይም ታንገ-ትቷዋን አከባቢ በከፍተኛ ሁኔታ የሚደገፈው ክለቡ በውጤት ረገድ በ2015/16 የውድድር ዘመን ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ከማጠናቀቁ በቀር በሊጉ ሌላ የሚጠቀስ ድል የለውም፡፡

የሞሮኮ የክለብ እግርኳስን በተለይ የካዛብላንካ ባላንጣዎቹ ዋይዳድ እና ራጃ እንዲሁም የመዲናዋ ራባት ክለብ የሆኑት ፉስ እና ኤኤስ ፋር ቢቆጣጠሩትም በ2014/15 ወደ ዋናው ሊግ ያደገው ኢትሃድ ታንገ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ በ2017ም በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል፡፡

ኢትሃድ ታንገ የ2016/17 የውድድር ዓመትን በአልጄሪያዊው አሰልጣኝ አብደላክ ቤንቺካ እየተመራ በ5ኝነት የጨረሰ ሲሆን ለአዲሱ የውድድር ዘመን የቀድሞ የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ኮከብን ዛኪ ባዱን ቀጥሯል፡፡ የቀድሞ የዋይዳድ ካዛብላንካ፣ ፉስ ራባት እና ማዮርካ ግብ ጠባቂ ባዱ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የአልጀርሱን ክለብ ሲአር ቤሎዝዳድን ለአልጄሪያ ዋንጫ ቻምፒዮንነት አብቅቷል፡፡

ባለፉት ወራት ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በተለያዩ ክለቦች የሙከራ እድል አግኝተዋል፡፡ ከሙጂብ ወደ ሞሮኮ መጓዝ አስቀድሞ አማካዩ ጋቶች ፓኖም በሩሲያ የነበረውን የሙከራ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ አጠናቆ ለአንዚ ማካቻካላ ሲፈርም ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አማካይ ቢኒያም በላይ በጀርመን (ዳይናሞ ድረስደን እና ኤዘንበርገር አዎ) እና ኦስትሪያ ተስፋ ሰጪ የሙከራ ግዜ አሳይቶ አሁን ላይ በአርሜኒያ በሌላ የሙከራ ግዜ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *