ዋሊድ አታ ወደ ሳውዲ አረቢያ ተመልሷል

ያለፉትን አራት ወራት በውሰት ለኖርዌው ሶግናድል ክለብ ሲጫወት የቆየው ዋሊድ አታ ወደ ሳውዲ አረቢያ ተመልሶ የአንደኛ ዲቪዚዮን ክለብ የሆነውን ናጅራን ተቀላቅሏል፡፡ በጉዳት ምክንያት በኖርዌይ የሚጠበቀውን ያህል ሶግንዳልን ያላገለገለው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዋሊድ ከናጅራን ጋር የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅቱን መጀመሩም ታውቋል፡፡

የቀድሞ የኤአይኬ እና ቢኬ ሃከን የመሃል ተከላካይ ናጅራንን ለቆ ሶግንዳልን በአጭር ግዜ የውል ስምምነት የተቀላቀለው ከወራት በፊት ነበር፡፡ ቢሆንም የኖርዌይ ቆይታ በጉዳት መታመሱን ተከትሎ በአብዛኛው የሊግ ጨዋታ ላይ መሰለፍ አልቻለም ነበር፡፡

ዋሊድ ወደ ኖርዌይ በውሰት ያቀናው በሳውዲ አረቢያ አንደኛ ዲቪዚዮን ክለቡ ናጅራን ሊያስመዝገበው አለመቻሉን ተክተሎ መሆኑን ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ በተለይ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “አዎ በውሰጥ ኖርዌ አምርቼ ነበር፡፡ ምክንያቱም ናጅራን በሊጉ ሊያስመዝገቡኝ ስላልቻሉ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ከጉዳት ተመልሼ ለአዲሱ የውድድር ዓመት ከናጅራን ጋር ዝግጅት ማድረግ ጀምሪያለሁ፡፡ አሁን ላይ በልምምድ እና የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ላይ እየተሳተፍኩ እገኛለው፡፡”

ናጅራን በ2015/16 ከሳውዲ ዋናው ሊግ መውረዱን ተከትሎ በ2016/17 የውድድር ዘመን ወደ ነበረበት ሊግ ለመመለስ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ናጅራን ለመለያ ጨዋታዎች ቢደርስም ወደ ሊጉ የሚያሳድገውን ውጤት ግን አላገኘም፡፡ አዲሱ የሳውዲ አንደኛ ዲቪዚዮን የውድድር ዘመን በመስረም ወር ይጀመራል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *