የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድኑን ማፍረሱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር ዛሬ ከጠዋቱ በ 5፡00 በኢትዮጵያ ሆቴል በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንትና የስፖርት ማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ሰይፉ ቦጋለ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ17 ዓመት በታች፣ ከ20 ዓመት በታች እና የዋናው የእግር ኳስ ቡድኖች መፍረሳቸውን እንዲሁም የሴቶች የእግር ኳስ ቡድንና የአትሌቲክስ ቡድኖቹ ግን ለጊዜው እንደማይፈርሱ ነገር ግን ውጤታቸው እየታየ ወደፊት ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

ውሳኔው የክለቡን ውጤት ብቻ መሰረት አድርጎ የተወሰነ ሲሆን የስፖርት ማኅበሩ የእግር ኳስ ክለቡን ያለፉትን ስድስት ዓመታት ውጤቶች በሚገባ ከመረመረ በኋላ ውሳኔውን እንዳስተላለፈ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የሴቶቹ የእግር ኳስ ክለብ ከወንዶች የተሻለ ውጤት ቢኖረውም ላለፉት ሁለት ዓመታት ሻምፒዮን መሆን አልቻለም፤ ይሁን እንጂ የስፖርት ማኅበሩ ለሴቶቹ የእግር ኳስ ቡድን አንድ ተጨማሪ ዓመት እድል እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡

የስፖርት ማኅበሩ እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በሚገባ የክለቡን አሰራር እንዳጠና ያስታወቁት ኃላፊው ባንኩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት በማሰብ እንዲሁም ክለቡ ለወጣትና ኣዳዲስ ተጫዋቾች እድል በመስጠት የሃገሪቱን እግር ኳስ ለመደገፍ በሚል ክለቡን ይዞ ቢቆይም ይህ ግን በፍጹም ሊሆን አልቻለም፤ አሁን በሃገቱ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ኣንጻርም ሊሆን የሚችል አይመስልም በሚል ክለቡን ለማፍረስ መገደዱን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

የአትሌቲክስ ቡድኑን በሚመለከት ምንም መናገር ኣንፈልግም ያሉት ኃላፊው ለጊዜው ከወንዶች የእግር ኳስ ቡድኑ በስተቀር በስፖርት ማኅበሩ ስር ያሉ የአትሌቲክሱም ሆነ የሴቶቹ ቡድን ይቀጥላሉ፡፡ ባንኩ ሲገነባቸው የነበሩ የስፖርት መሰረተ ልማት ስራዎች በሙሉ እንደሚቀጥሉና ባንኩ እነዚህን ሥራዎች የመገንባት የመጠበቅና የመንከባከብ ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡

የስፖርት ማኅበሩ ለ2010 ዓ.ም. ለክለቡ ይዞት ከነበረው 85 ሚሊዮን ብር ከሃምሳ በመቶ በላይ በመቀነስ በ30 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደሚንቀሳቀስ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

የባንኮች የእግር ኳስ ክለብ በ1975 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን በ1992 የግል ባንኮችን አባል አድርጎ የኢትዮጵያ ባንኮች ስፖርት ማህበር በሚል በአዲስ አደረጃጀት ሲመጣ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስር በመሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ማኅበር ተብሎ በሃገሪቱ እግርኳስ ላይ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ እስከተጠናቀወው የውድድር አመት ድረስ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲወዳደር ቆይቶ ዐደ ከፍተኛ ሊጉ የወረደ ሲሆን በ1996 በክለቡ ታሪክ ብቸኛው የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አንስቷል፡፡ በ1997 እና በ2002 የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር ላይም ተሳትፏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *