የጣና ሞገዶቹ ፍጹም ፍትዓለውና አንተነህ ተፈራ ባስቆጠሯቸው ግቦች ድሬድዋ ከተማን 2 ለ 0 አሸነፉ

በድሬዳዋ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሙከራዎች ያልታዩበትና ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ነበር። አስራት ቱንጆ ለድሬዳዋ ከተማ መሬት ለመሬት መትቶ ለጥቂት ከወጣችው ኳስ ውጭ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ተቸግረው ቆይተዋል። ሆኖም አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩ ፍጹም ፍትዓለው ከቅጣት ምት በመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ አስቆጥሮ ባህር ዳርን መሪ አድርጓል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር የጣና ሞገዶቹ ውጤቱን ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት ቀጥለዋል። በ59ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሰን በለጠ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አንተነህ ተፈራ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ በመጠቅለል አስደናቂ ግብ አስቆጥሯል። ይህች ግብ የባህር ዳርን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ በማሳደግ የጨዋታውን ሂደት እንዲቆጣጠሩ ረድታቸዋለች።
ድሬዳዋ ከተማዎች በሁለት ግብ ከተመሩ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ወደፊት ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል። አቤል ነጋሽ በግንባር እንዲሁም ሙሀመድኑር ናስር በቅጣት ምት ተስፋ ሰጪ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በቁጥር በዝተውና ተደራጅተው መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉትን የባህር ዳር ተጫዋቾች አልፎ ግብ ማስቆጠር ግን አልተሳካላቸውም። በመጨረሻም ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል::

