የቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የ32ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የ32ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ32ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች

መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮጵያ መድን

መቐለ 70 እንደርታ ካለበት አስከፊ ውጤት ማጣት ለመውጣት እና በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን በማሰናበት ቡድኑን በአዲስ መንፈስ ለመገንባት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ሾሟል። ቡድኑ እስካሁን ባደረጋቸው 31 ጨዋታዎች 13 ጊዜ ተሸንፎ 63 ነጥቦችን በመጣሉ በ30 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 34 ጎሎችን ያስተናገደው ተከላካዩና በመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች የሚታይበት የትኩረት ማጣት ዋነኛ ደካማ ጎኖቹ ቢሆኑም በአዲስ አሰልጣኝ ወደ ሜዳ መግባታቸው መነቃቃት እንደሚፈጥርላቸው ተጠብቋል። መቐለ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣትና ባለፈው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ የደረሰበትን የ1 ለ 0 ሽንፈት ለማካካስ በዛሬው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ማግኘት የግድ ይለዋል።

የኢትዮጵያ መድን በአሁኑ ሰዓት እጅግ አስደናቂ በሚባል አቋም ላይ ይገኛል። ቡድኑ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ31 ጨዋታዎች 40 ነጥብ በመሰብሰብና +3 የጎል ክፍያ በመያዝ በ11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ጠንካራውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2 ለ 1 በማሸነፍ ትልቅ ግስጋሴ አሳይቷል። የቡድኑ ጥንካሬ በዋናነት የሚገለጸው ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሶስት ተከታታይ ድሎችን አሳክቶ በሁለቱ አቻ በመውጣት ሽንፈት አለማስተናገዱ ሲሆን ይህም ጥሩ የሚባል የሊግ ግስጋሴ እያደረገ እንየሚገኝ ማሳያ ነው። ጠንካራ ጎኑ በራስ የመተማመን መንፈስና የተከታታይ ድሎች ስነ-ልቦና ሲሆን ደካማ ጎኑ ደግሞ ምንም እንኳን 27 ጎሎችን ቢያገባም 24 ጎሎች ማስተናገዱ በመከላከል ረገድ ጥንቃቄ እንደሚሻ ያሳያል።

ሁለቱ ቡድኖች ሶስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን ሁለት ጊዜ ዶል ሲያደርግ መቐለዎች ደግሞ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል። መድን 5 ግቦችን ሲያስቆጥሩ መቐለዎች 1 አስመዝግበዋል።

መቐለ 70 እንደርታዎች በመጨረሻው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ተመስገን ተስፋዬ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም። በኢትዮጵያ መድን በኩል በረከት ካሌብ እና ቤንጃሚን ኮቴ በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ በአሁኑ ወቅት በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ቆሞ የህልውና ፍልሚያ እያደረገ ይገኛል። ቡድኑ እስካሁን ባደረጋቸው 31 ጨዋታዎች 34 ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ በ18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ድል አለማስመዝገቡ እና ባለፈው ሳምንት በነገሌ አርሲ 3 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት መሸነፉ የቡድኑን ስነ-ልቦና በእጅጉ ጎድቶታል። የቡድኑ ዋነኛ ድክመት 33 ጎሎች ያስተናገደው እና የትኩረት መበታተን የሚታይበት የተከላካይ ክፍሉ ሲሆን ቡድኑ ካለው የቆየ ታሪክ አንጻር በዛሬው ጨዋታ የሚያሳየው የትግል መንፈስ ብቸኛው የመዳኛ ተስፋው ነው።

በተቃራኒው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ አጋማሽ በ41 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን በሊጉ ታሪክ ለየት ያለና አስገራሚ ክብረ ወሰን እያስመዘገበ ይገኛል። የጣና ሞገዶቹ እስካሁን ካደረጓቸው ጨዋታዎች ውስጥ 17ቱን በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ በሊጉ ቀዳሚ ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ 12ቱ ጨዋታዎች 0 ለ 0 የተጠናቀቁ መሆናቸው ቡድኑን በመከላከል ረገድ በሊጉ ያለውን ጥንካሬ ያሳያል። በ31 ጨዋታዎች 22 ጎል ብቻ መቆጠሩ ትልቅ ጥንካሬ ቢሆንም ጎል የማስቆጠር ችግሩ እና ድልን በአቻ ውጤት የመቀየር አባዜው አሁን ካለበት የደረጃ ሰንጠረዥ ከፍ እንዳይል አድርጎታል። ዛሬም ይህንን የተከላካይ ጥንካሬውን ይዞ የድሬዳዋን ግድግዳ ሰብሮ በመውጣት በማጥቃት ረገድ የተሻለ ነገር ካሳየ ወደ መጀመሪያዎቹ ስድስት ቡድኖች የመጠጋት እድሉ ሰፊ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 13 አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን 5 ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ተፈፅመው ባህር ዳር ከተማዎች በ6 ጨዋታዎች ባለድል ሲሆኑ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ 2 ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በጨዋታዎቹ ባህር ዳሮች 21 እንዲሁም ድሬዎች ደግሞ 10 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 ውድድር ዓመት አልተካተተም)

ድሬዳዋ ከተማዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም። ባህር ዳር ከተማዎች በበኩላቸው ማንያዘዋል ካሳ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ነው።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሸገር ከተማ

የ2016 የሊጉ ባለክብር የነበረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት ባደረጋቸው 31 ጨዋታዎች 38 ነጥብ በመያዝ በ14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች የተመዘገበው ውጤት እንደሚያሳየው በተለይም ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መድን 2 ለ 1 መሸነፉ ትልቅ የነጥብ ኪሳራ አስከትሎበታል። የባንኮቹ ዋነኛ ጥንካሬ 38 ጎሎችን ያስቆጠረውና በሊጉ ካሉ ክለቦች ሁሉ ከፍተኛ ጎል የማስቆጠር ብቃት ያለው የማጥቃት መስመራቸው ቢሆንም አሁን ላይ ያንን አቅሙን እያጣው ይገኛል። በ31 ጨዋታዎች 37 ጎሎች ያስተናገደው የመከላከል ድክመቱ ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ ስጋት ነው። ንግድ ባንክ ካጣው 55 ነጥቦች አገግሞ ወደ ላይ ለመምጣት ዛሬ በመከላከል ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

ሸገር ከተማ በበኩሉ ጊዜያዊ አሰልጣኝ የነበሩትን ዶክተር ኢያሱ መርሃጽድቅን በቋሚነት በዋና አሰልጣኝነት በመሾም የዛሬውን ጨዋታ ያደርጋል። ቡድኑ በ31 ጨዋታዎች 40 ነጥብ በመሰብሰብ በ12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናግድ (2 ድል እና 3 አቻ) መቆየቱ እና ባለፈው ሳምንት መሪው ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 መርታቱ ለቡድኑ ትልቅ መነሳሳት ሆኗል። የሸገር ከተማ ዋነኛ መለያ እና ጥንካሬ በሊጉ 16 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት በመጨረስ የሚታወቀውና 26 ጎል ብቻ ያስተናገደው የጠነከረ የመከላከል መዋቅሩ ነው። ምንም እንኳን ጎል የማስቆጠር መጠኑ (28 ጎል) አነስተኛ ቢሆንም ቡድኑ ያለው መረጋጋት የንግድ ባንክን የማጥቃት መስመር ለመግታት ዋነኛ መሣሪያቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን በጨታውም ነጥብ የተጋሩ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች አንድ አንድ ግቦችን አስቆጥረዋል።

ሸገር ከተማዎች ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነፃ ሆነው የዛሬውን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግብ ጠባቂው ጊቢ ጆቤ እና የፊት መስመር ተጫዋቹ ናትናኤል ዳንኤል ከቅጣት መልስ አግኝቷል።