ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በመቻሎች የበላይነት ሲጠናቀቅ ምደረገነት ሽረ ድል ቀንቶታል

ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በመቻሎች የበላይነት ሲጠናቀቅ ምደረገነት ሽረ ድል ቀንቶታል

መቻል ነጌሌን 4ለዐ ሲረመርም ምድረገነት ሽረዎች ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ አንድ ደረጃ ከፍ ያሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

ምደረገነት ሽረ ከ ከኢትዮጵያ ቡና

ምድረ ገነት ሽረን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው በአዳማ የተደረገው ቀዳሚው ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራ ቡድኖቹ ያላደረጉበት ነበር። ሆኖም ግን ሽረዎች የጨዋታ ጅማሮ ላይ ወደ ፊት ሄደው አደጋ ፈጥረው ቀዳሚ የሆኑበት ግብ አግኝተዋል። 12ኛው ደቂቃ ላይ ከመልስ ውርወራ የጀመሩት ኳስ ተጨርፎ የሳጥኑ ጠርዝ ወደ ነበረው አቤል እንዳለ ጋር ደርሶ አክርሮ መትቶ መረብ ላይ በማሳረፍ መሪ አድርጓቸዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ቡናማዎቹ ሙሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው በመስመሮች እየገቡ ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የጠራ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹ ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ቡናማዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ የተጠቀሙበትን ረጅም ሰዓት ከኳስ ጋር የመቆየት አጨዋወት ወደ ማጥቃት አሳድገው እጅግ ለግብ የቀረቡ አደገኛ እና አስቆጪ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን በተለየም በአቡበከር አዳሙ አስገዳጅ ቅያሪ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው በረከት ብርሃኑ ግብ ጠባቂው ወጥቶ እያለ ብቻውን ሆኖ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ተካልኝ ደጀኔ ሳይጠበቅ ከእግሩ ስር ያወጣበት አጅጉን አስቆጪው አጋጣሚ እንዲሁም ራምኬል ጀምስ በግንባሩ ገጭቶ አድርጎት ለጥቂት ከፍ ብሎ ያለፈበት አቻ ሊያደርጋቸው የቀረበ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ካሉበት ወራጅ ቀጠና ስጋት ትንሽም ቢሆን ፈቀቅ ለማለት ነጥቡን አብዝተው ይፈልጉ የነበሩት ሽረዎች ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ሙሉ ለሙሉ ወደኋላ አፈግፍገው እየተጫወቱ የቡናማዎቹን ጥቃት ሲከላከሉ እያስተዋልን ጥረታቸውም ተሳክቶ በጨዋታውም ግብ ሳያስተናግዱ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረ ብቸኛ ግብ ሶስት ነጥብ አሳክተው ጨዋታው ተቋጭቷል።

መቻል ከነጌሌ አርሲ

የሳምንቱ ተጠባቂው የእለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የዋንጫ ፉክክር ላይ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙትን መቻልን ከነጌሌ አርሲ አገናኝቷል። ነጌሌዎች አስቆጪ አጋጣሚ በመፍጠር በጀመሩበት በጨዋታው ከተከላካይ ጀርባ የተጣለ ኳስ ግብ ጠባቂው ለመያዝ ጥረት ሲያደርግ ተጨርፎ አልፎ ገብረመስቀል ዱባለ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ካለፈበት በኋላ ዘለግ ላለ ደቂቃ የጨዋታ ብልጫ ተወስዶባቸው ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

በአጋማሹ ሙሉ የጨዋታ በላይነት የወሰዱት መቻሎች ገና 7ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በመስመር በኩል ኮሊንስ ኮፊ እና ቸርነት ጉግሳ ባደረጉት ጥሩ መግባባት ቸርነት ጉግሳ በግሩም ሁኔታ ሾልኮ በመውጣት ግብ ጠባቂውን አልፎ በጠባብ አንግል መትቶ ኳስ እና መረብ ማገናኘት ችሏል። ከግቡ በኋላ ከፍ ባለ ተነሳሽነት መቻሎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል።

የአጋማሹ መገባደጃ ላይ ነጌሌዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ አደገኛ ሙከራ በሀቢብ ከማል አማካኝነት አድርገው ለጥቂት ከፍ ብሎ ካለፈባቸው በኋላ ተጨማሪ ግብ ሳይጠበቅ አስተናግደዋል። ጭማሪ በታየው ላይ መቻሎች ኳስ ይዘው ሳጥን ውስጥ በሚገቡበት ቅፅበት ሮቦት ሰላሎ እና ዳዊት መለሰ ቸርነት ጉግሳ ላይ በሰሩት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቷቸው ፈቱዲን ጀማል ወደ ግብነት ቀይሮ አጋማሹ በመቻል 2ለ0 መሪነት ተገባዶ ወደ መልበሳ ክፍል አምርተዋል።

ነጌሌዎች ተጠናክሮ የተመለሱ በሚመስሉት በሁለተኛው አጋማሽ ምንም እንኳን የመቻሎችን በር ማንኳኳት አጠናክረው ቢቀጥሉም የጠራ ሙከራ ሳያደርጉ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ተዳክመው ጨዋታውን ለመቆጣጠር የገቡ የሚመስሉት መቻሎች 65ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ማሞ ከግራ መስመር ያሻገራትን ኳስ ቻርሌስ ሙሴጌ በቀላል ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ ጨዋታው 3ለ0 እንዲሆን አስችሏል።

በቁጥር በርከት ብለው ወደ ማጥቃቱ የገቡት ነጌሌዎች ይዘው የሚገቡትን ኳስ ለመጠቀም ሲቸገሩ የተመለከትን ሲሆን መቻሎች በበኩላቸው ወደ ኋላ ያፈገፈጉ እየመሰሉ በመልሶ ማጥቃት አራተኛውን ግብ አስቆጥረዋል፤ 78ኛው ደቂቃ ላይ ጉግሳ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ በረከት ደስታ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ጨዋታውን ጨርሶታል። ነጌሌዎች እየተቀዛቀዙ ሲሄዱ እየተመለከትን አልፎ አልፎ ጥቃት የሰነዘሩ ቢሆንም ጨዋታው በመቻል 4ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።