​አአ ከተማ ዋንጫ፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ነጥብ ተጋርተዋል

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ለ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ኢትዮ ኤሌክትሪከ ሲያሸንፈ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ አቻ ተለያይተዋል፡፡

09:00 ላይ የተጀመረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በአምናው ቻምፒዮን 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ እስካሁን ከተደረጉት ጨዋታዎች በተሻለም በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተስተናግደውበታል፡፡

እስከ ግማሽ ሰአት ድረስ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ ከ27 ደቂቃ ጀምሮ በሁለቱም በኩል ጠንካራ የግብ ሙከራዎች ታይተዋል፡፡ በተለይም ተክሉ በግል ጥረቱ ከመስመር ወደ ውስጥ በመግባት ግልጽ የግብ አጋጣሚ ፈጥሮ ያመከናት ኳስ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ ልታደርግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች፡፡ በአዳማ በኩል ደግሞ በ32ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባር ገጭቶ በሚያስቆጥራቸው ግቦች የሚታወቀው አላዛር ፋሲካ መትቶ ዮሀንስ በዛብህ በቅልጥፍና ያወጣበት ሙከራ የሚጠቀስ ነበር፡፡ ከአላዛር ሙከራ የተመለሰው ኳስ በመልሶ ማጥቃት ኤሌክትሪኮች ወደ ወደ አዳማ ግብ በመቅረብ በጥላሁን ወልዴ አማካኝነት ሞክረው ጃኮ አውጥቶበታል፡፡

ከ5 ደቂቃዎች በኋላ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ተክሉ ተስፋዬ ያሻገረለትን ኳስ በግቡ የግራ መስመር በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ጫላ ድሪባ ሳይጠቀምበት የቀረበት ፣ በ40ኛው ደቁቃ ሱራፌል ዳንኤል ከቀኝ መስመር በግምት ከ40 ሜትር የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ በረጅሙ ወደ ግብ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀሱ ሌሎች ሙከራዎች ነበሩ፡፡

በርካታ ጥፋቶች እና ጉሽሚያዎች በተስተዋሉበት ሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመርያው ሁሉ ግብ ሊሆኑ የግብ ሙከራዎች ተስተናግደዋል፡፡ በተለይ በአዳማ በኩል በ48ኛው ደቂቃ ሱራፌል በግራ መስመር በኩል የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ የግቡን አግዳሚ የመለሰበት እንዲሁም አላዛር ፋሲካ ሳጥን ውስጥ ጥሩ የማስቆጠር አጋጣሚ አግኝቶ ያመከነው ኳስ የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ 

በ58ኛው ደቂቃ ተስፋዬ መላኩ በሰራው አደገኛ ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ ቀሪውን ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደደው ኤሌክትሪክ የመጨረሻ 30 ደቂቃዎችን የተዳከመው አዳማን ተቆጣጥሮ አሸንፎ መውጣት ችሏል፡፡ በ74ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባውና በሙከራ ላይ የሚገኘው በላይ አባይነህ በአዳማ ተከላካዮች ስህተት ያገኛትን ኳስ በግብ ጠባቂው እግሮች መሀል አሾልኮ የኤሌክትሪክን የማሸነፍያ ጎል አስቆጥሯል፡፡ 

ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ የአዳማ ከተማው ሱራፌል ዳኛቸው የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተዘጋጀውን ዋንጫ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እጅ ተቀብሏል፡፡

11:30 ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ህብረ ዜማ ደምቆ የተካሄደው የመከላከያ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ተፈጽሟል፡

ሁለቱም ቡድኖች በዝግታ በመቀባበል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲያደርጉ የነበረው ጥረት በተደጋጋሚ ሲቆራረጥ የተስተዋለ ሲሆን አመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በመሀል ሜዳ የተገደበ ሆኖ ዘልቋል፡፡ በክፍት ጨዋታ የተፈጠረ የግብ እድል ለመፍጠርም ከአንድ ሰአት በላይ ለመዝለቅ ተገደዋል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ በመከላከያ በኩል የሚጠቀስ የግብ ሙከራ ያልነበረ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በሁለት አጋጣሚዎች አበባው ቡታቆ የመታቸው ቅጣት ምቶች ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ወደ ውጪ ወጥተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያ ጨዋታውን አሸንፎ ሊወጣ የሚችልባቸውን የግብ እድሎች ማግኘት ቢችልም ምንይሉ ወንድሙ ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡ በተለይ በ62ኛው እነና 85ኛው ደቂቃ ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ሰብሮ በመውጣት የፈጠራቸውን መልካም አጋጣሚዎች ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡

ጨዋታው እምብዛም አስደሳች እንቅስቃሴ ሳይታይበት ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈጽሟል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም ኒኪማም የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተዘጋጀውን ዋንጫ ከአቶ ዮሴፍ ተስፋዬ እጅ ተቀብሏል፡፡ 

እስካሁን በሲቲ ካፑ 4 ጨዋታዎች ተደርገው 2 ግቦች (በጨዋታ በአማካይ 0.5) ብቻ መቆጠራቸውና በጨዋታ ላይም የሚጠቀሱ የግብ ሙከራዎች ጥቂት መሆናቸው አሳሳቢ ሆኗል፡፡ 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *