‹‹ኃይለየሱስ ባዘዘውን አልቀጣንም›› የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ልኡልሰገድ በጋሻው

አወዛጋቢው የኢንተርናሽናል ዳኞች ምርጫ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴን አባላት ለሁለት ከፈለ?

በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር ከሚገኙ ኮሚቴዎች መካከል አንዱ በሆነው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰሞኑን ከኢንተርናሽናል ዳኞች ምርጫ ጋር በተያያዘ አወዛጋቢ ጉዳዮች በተደጋጋሚ እየተሰሙ ይገኛሉ። የዳኞች ኮሚቴን የአሰራር ክፍተትን በግልፅ በመቃወሙ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው ለሁለት አመት ከማንኛውም ውድድር እንዲታገድ እና የገንዘብ ቅጣት እንዲተላለፍበት እንደተወሰነ ቢነገርም ‹‹ሀሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱ ሊከበርለት ይገባል›› በማለት እንደማይቀጣ ተሰምቷል፡፡ የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ልኡልሰገድ በጋሻውም ኃይለየሱስ ተቀጥቷል መባሉን አስተባብለዋል፡፡ ‹‹መቀጣቱን ከሚዲያ ነው የሰማነው፡፡ ከሚቴው ስብሰባ ባልተሰበሰበበት ሁኔታ እንዴት ነው ቀጣችሁት የሚባለው›› ብለዋል፡፡

ሌላው ከሰሞኑ መነጋገሪያ ርዕስ የሆነው ጉዳይ በኢንተርናሽናል ዳኞቹ ዘካርያስ ግርማ እና ኃይለየሱስ ባዘዘው ምትክ አዲስ ኢንተርናሽናል ዳኛ በመሆን ስማቸው ወደ ፊፋ ከተላኩ ሁለት ዳኞች መካከል የዳዊት አሳምነው መመረጥ በኮሚቴው አባላት መካከል ልዩነት የፈጠረ ሆኗል፡፡ በጉዳዩ ላይ በለዲጠቀሰተየብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ውስጥ ያሉ አንድ አባል በዳዊት አሳምነው መመረጥ ዙርያ ከፍተኛ ተቃውሞ ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት ለረጅም ጊዜ በኢንተርናሽናል ዳኝነት ሊቆይ ለማይችል ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ከምንሰጥ ብ ጊዜ ሊያገለግል ለሚችል ዳኛ እድሉ ቢሰጥ ይሻላል ማለታቸው እየተነገረ ይገኛል።

በተፈጠረው ልዩነት ላይ ያለውን መረጃ ይዘን በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው በተጠባባቂነት ተይዘው የነበሩትን ዳኞች ፈተናውን ባላላፉ ዳኞች እንደተተኩ ገልፀዋል፡፡ ” አስቀድሞ ሁለቱ ኢንተርናሽናል ዳኞች ይወድቃሉ ብለን አላሰብንም፡፡ ከወደቁ ደግሞ በእነርሱ ምትክ መተካት ስላለብን መስፈርት አወጣን ፤ በመስፈርቱ መሰረት ልምድ ያለው ዳኛ በነበረው ዘካርያስ ግርማ ምትክ ዳዊት አሳምነውን ፣ በኃይለየሱስ ባዘዘው ምትክ ደግሞ ወጣቱ ቴዎድሮስ ምትኩን ኮሚቴው ተወያይቶ በመነጋገር ወስነናል፡፡›› ያሉት አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው በኮሚቴው መካከል ምንም የሀሳብ ልዩነት እንደሌለ እና በቃለ ጉባኤ ተማምነው ያፀደቁት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *