የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት – የማክሰኞ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

በሳምንቱ መጨረሻ በተደረጉት ሶስት ጨዋታዎች የተጀመረው የሊጉ 14ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ እና አርባምንጭ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል። እነዚህን ጨዋታዎችም በዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።


ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መቐለ ከተማ

ውርርድ – (እዚህ ይጫኑ)

ኤሌክትሪክ 1.85 | አቻ 1:19 | መቐለ 1:65


በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ የሚመራው ይህ ጨዋታ ሁለት በተለያየ መስመር ላይ የሚገኙ ክለቦችን የሚያገናኝ ነው። እስካሁን ያስመዘገቡት ውጤትም በሊጉ ካላቸው ታሪክ የተለየ ነው። የሁለት ጊዜ ሻምፒዮኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዘጠኝ ነጥቦች መጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ያላደረጋቸው ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ካልሆኑ በቀር ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳካበት ወቅታዊ አቋሙም በአንደኛው ዙር ራሱን ለማሻሻል ተስፋ የሚሰጠው አይደለም። 

በአንፃሩ ከስድስተኛው ሳምንት በኃላ ሽንፈት ያልገጠመው መቐለ ከተማ ሳምንት በሲዳማ ቡና ላይ ያስመዘገበው ድል ራሱን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እንዲያገኘው ምክንያት ሆኗል። ክለቡ የዛሬውን ጨዋታም ማሸነፍ ከቻለም ነጥቡን 24 በማድረስ ከደደቢት በአንድ ነጥብ አንሶ ሁለተኛ ላይ መቀመጥ የሚችል ይሆናል። ኢትዮ ኤሌክትሪክም ቢሆን ውጤት ከቀናው በተስተካካይ ጨዋታዎቹ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እንዲችል ነጥቡን ካሁኑ የሚያስተካክልበት ዕድል ይኖራል።

በመቐለ ከተማ በኩል መጠነኛ ህመም ከገጠመው አሌክስ ተሰማ በቀር የተሰማ የጉዳት ዜና ባይኖርም አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ በተላለፈባቸው የአምስት ጨዋታ ቅጣት ምክንያት ቡድናቸውን መምራት የማይችሉ ይሆናል። ጥላሁን ወልዴ ፣ ቢኒያም አሰፋ እና ዐወት ገ/ሚካኤል ደግሞ በኤሌክትሪክ በኩል ከጉዳታቸው ያላገገሙ ተጨዋቾች ሲሆኑ የኃይሌ እሸቱ የመሰለፍ ነገርም አለየለትም። ከዚህ ውጪ ግብ ጠባቂው ሱሊማን አቡ ከክለቡ ጋር ያለውን ቅሬታ ባለመፍታቱ አሁንም ወደ ሜዳ የማይመለስ ይሆናል።

የሁለቱ ክለቦች ወቅታዊ አቋም እና በደረጃ ሰንጠረዡ የሚገኙበት ቦታ ለጨዋታው የሚቀርቡበትን ሁኔታ የሚወስነው ይመስላል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካለበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ይገኛል። በመሆኑም ቢያንስ አንድ ግብ እስኪያገኝ ድረስ ጨዋታውን ሙሉ የማጥቃት ሀይሉን ተጠቅሞ እንደሚያደርገው ይጠበቃል። በሌላ በኩል ወትሮም ቢሆን በጠንካራ የመከላከል መሰረት ላይ የተገነባው መቐለ ከተማ ጥንቃቄን በመምረጥ ከመልሶ ማጥቃት በሚገኙ ዕድሎች ወደ ግብ ለመድረስ ወደ ሜዳ የሚገባበት ዕድል ሰፊ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በአማካይ ክፍላቸው ለተከላካይ መስመራቸው በቂ ሽፋን በመስጠት የሚታወቁት መቐለዎች ዛሬም ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የማጥቂያ አማራጮች በቀላሉ ክፍተት የሚሰጡ አይመስልም። ይልቁኑም አጨዋወቱን በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አድርጎ ወደ ሜዳ ሲገባ ከኃላ ክፍተት የማያጣው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለመቐለ ከተማ መልሶ ማጥቃት ምቹ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ። በዚህ ረገድ እምብዛም በማጥቃት ላይ የማይሳተፉት የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመስመር ተከላካዮች የመቐለ ከተማን ድንገተኛ ጥቃት ከሚያስጀምሩት የመስመር አማካዮች ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ ወሳኝ ይሆናል። ቡድኑ በቀጥተኛ አጨዋወትም መሀል ለመሀል ዕድሎችን በሚፈጥርበት አጋጣሚ ኳሶች ወደ ጋይሳ አፖንግ ከመድረሳቸው በፊት ለማቋረጥ የባለሜዳዎቹ አማካዮች ሀላፊነት ከፍ ያለ ነው። 

ማጥቃትን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አንፃር ስንመለከተው ደግሞ በሜዳው ቁመት በአማካይ ክፍሉ ጫፍ እና በፊት መስመር አጥቂነት የሚጣመሩት ካሉሻ አልሀሰን እና ዲዲዬ ለብሪ እንቅስቃሴ በእጅጉ ወሳኝ ይሆናል። በተለይ ካሉሻ አልሀሰን ከዲዲዬ የጎንዮሽ እና የኃላ እንቅስቃሴ በመነሳት በተጋጣሚው የአማካይ እና ተከላካይ መስመር መሀል የሚኖረውን ጠባብ ክፍተት ለመጠቀም በከፍተኛ ትኩረት መጫወት ይጠበቅበታል። ከዚህ ውጪ የነበሀይሉ ተሻገር የመሀል ሜዳ ቅብብል ስኬት ለቡድኑ የማጥቃት ሂደት ብቻ ሳይሆን ከድንገተኛ የመልሶ ማጥቃት ለመዳንም ጭምር አስፈላጊነቱ ከፍ ያለ ነው።



አርባምንጭ ከተማ ከ ድሬደዋ ከተማ

ውርርድ – (እዚህ ይጫኑ)

አርባምንጭ 1.32 | አቻ 1:52 | ድሬዳዋ 2:05


ይህ ጨዋታ ሁለት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችን እርስ በእርስ የሚያገናኝ ነው። ከአምስት ተከታታይ ሽንፈት በኃላ በአሰልጣኝ እዮብ ማለ እየተመራ አዳማ ከተማን አሸንፎ ከሜዳው ውጪ ባደረገው ጠንካራ ጨዋታ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራው አርባምንጭ ከተማ አሁን ላይ ከተጋጣሚው የተሻለ መነቃቃት ላይ ይገኛል። ያለፉት ሁለት ተጋጣሚዎቹ ጠንካራ የሚባሉ ከመሆናቸው አንፃር ቡድኑ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ እንደሆነ መናገር ይቻላል። 

ድሬደዋ ከተማ ግን አሁንም በሚፈለገው መጠን የተሻሻለ አይመስልም። ባሳለፍነው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ተስተካካይ ጨዋታ ነጥብ መጋራቱ ትልቅ ውጤት ቢሆንም የኢትዮጵያ ቡናውን ሽንፈት ጨምሮ ባለፉት ሳምንታት ባደረጋቸው ጨዋታዎች ዘንድሮ አንድ ጊዜ ብቻ ወዳጣጣመው ድል መመለስ አልቻለም። ዛሬ አርባምንጭ ላይ በፌደራል ዳኛ ሚካኤል አረአያ የመሀል ዳኝነት የምደረገው ይህ ጨዋታ በመሸናነፍ ከተጠናቀቀ ለአሸናፊው የሚኖረው ዋጋ ከፍ ያለ ነው። በተለይ ሌላው የወራጅ ቀጠና ተፎካካሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሽንፈት ከገጠመው የዚህ ጨዋታ አሸናፊ ከወራጅ ቀጠናው በጥቂቱም ቢሆን የመራቅ አጋጣሚ ይፈጠርለታል።

የአርባምንጮቹ ወንድሜነህ ዘሪሁን እና ወንደሰን ሚልኪያስ በጉዳት ለጨዋታው የማይደርሱ ሲሆን ገ/ሚካኤል ያዕቆብ እና ብርሀኑ አዳሙ ከቅጣት ይመለሳሉ። የድሬደዋ ከተማዎቹ ሀብታሙ ወልዴ ፣ ዘነበ ከበደ እና ሳምሶን አሰፋ አሁንም ከረዥም ጊዜ ጉዳታቸው ያላገገሙ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ እጁ ላይ ጉዳት የደረሰበት አህመድ ረሺድ ሙሉ ለሙሉ ባያገግምም ጨዋታውን የሚጀምርበት ዕድል አለ።

ከጨዋታው ከፍተኛ ዋጋ አንፃር ሁለቱም ቡድኖች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያስችሏቸውን አማራጮች በሙሉ ተጠቅመው ቀድመው ግብ በማስቆጠር ውጤት ይዘው ለመውጣት እንደሚጥሩ ይጠበቃል። በአርባምንጭ ከተማ በኩል በአዲሱ አሰልጣኙ ስር ከተከላካይ መስመር ሚናው ወደ ፊት አጥቂነት የመጣው ተመስገን ካስትሮ ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ዋነኛ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። በዚህም ተጨዋቹ ከድሬዎቹ የመሀል ተከላካዮች አንተነህ ተስፋዬ እና በረከት ተሰማ መሀል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለቡድኑ ስኬታማነት ወሳኝ ይሆናል። በተለይም ተመስገን ከመስመር አማካዩ እንዳለ ከበደ ጋር የሚኖረው የቅብብል ግንኙነት ለባለሜዳዎቹ የመጨረሻ ዕድሎችን የመፍጠር አቅም ይኖረዋል። የአማኑኤል ጎበና እና ምንተስኖት አበራ የአማካይ መስመር ጥምረትም አርባምንጮች ኳስ በሚቆጣጠሩባቸው ጊዜያት ከኢማኑኤል ላርያ ጀርባ ለመግባት የሚያስችላቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ይጠበቅበታል። ሆኖም ድሬዎች በጊዮርጊሱ ጨዋታ የነበራቸው የአማካይ መስመር የመከላከል ጥንካሬ ይህ እንዲሆን በቀላሉ የሚፈቅድ አይደለም። 

ከኢማኑኤል ላርያ ፊት የነበረው የዮሴፍ ደሙዬ እና ዘላለም እያሱ የመሀል እንዲሁም የአናጋው ባድግ እና ወሰኑ ማዜ የመስመር ጥምረት በማጥቃት ወቅት የፊት አጥቂው ኩዋሜ አትራምን ቀርቦ በቅብብሎች ከማግኘት ባለፈም የተከላካይ መስመሩ እንዳይጋለጥ ትልቅ እገዛ ነበረው። ቡድኑ ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ እና የተጨዋቾች የታታሪነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ከሆነ ከአርባምንጭ ነጥብ ይዞ የመመለስ ዕድልን መፍጠሩ የማይቀር ነው። በተለይም ኳስ በዮሴፍ ደሙዬ የግር ስር በሚገኝባቸው አጋጣሚዎች የቡድኑ አስፈሪነት ከፍ የሚል ሲሆን ተጨዋቹ ከምንተስንኖት አበራ ጋር የሚገናኝባቸው የጨዋታ ክፍሎችም ተጠባቂ ይሆናሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *