​ደደቢት ከ መከላከያ | ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ ከተደረጉ ጨዋታዎች በተጨማሪ ዛሬ 11 ሰዐት ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የደደቢት እና መከላከያን ጨዋታ ያስተናግዳል። ይህንን ጨዋታ እንደሚከትለው ዳሰነዋል።

አምና በመጀመሪያው ዙር 11ኛ ሳምንት ሲገናኙ ያለግብ ተለያይተው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች የዛሬው ጨዋታቸው በፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ የመሀል ዳኝነት የሚካሄድ ነው። የሊጉ መሪ ደደቢት ከስድስት ጨዋታዎች የአሸናፊነት ጉዞ በኃላ በጅማ አባ ጅፋር የደረሰበት ሽንፈት ከተከታዮቹ ሊርቅ የሚችልበትን ዕድል ብቻ ሳይሆን ወሳኝ አጥቂውን እና አሰልጣኙንም ጭምር ያሳጣው ነበር። ቡድኑ 14ኛ ሳምንት ላይ የነበረው ጨዋታ በመተላለፉም ተከታዮቹ ይበልጥ እንዲጠጉት ሆኗል። በመሆኑም የዛሬው ጨዋታ የነጥብ ልዩነቱን ከማስፋት ሌላ የቡድኑን የአሸናፊነት መንፈስ ለመመለስም እጅግ ጠቃሚ ጨዋታ ይሆናል። ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ያሉት መከላከያ ወልዋሎ ዓ.ዩን እና ድሬደዋ ከተማን አከታትሎ ያሸነፈበት ውጤት መድገም ሳይችል ደብዛዛ የውድድር አመት እያሳለፈ ይገኛል። በወራጅ ቀጠናው ያስቀመጠውን ውጤቱን ለማሻሻልም ዛሬ ሊጉን እየመራ ካለው ቡድን ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ የሚኖረው ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል።

በጨዋታው መከላከ ቴዎድሮስ በቀለን እና አዲሱ ተስፋዬን  በጉዳት ሲያጣ የደደቢቱ አቤል ያለውም ለጨዋታው የመድረሱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ውጪ በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ጌታነህ ከበደ የአራት ጨዋታ ቅጣቱን እንዲሁም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ከዚሁ ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የተላለፈባቸውን የሶስት ወር ቅጣት ዛሬ የሚጀምሩ ይሆናል።

መከላከያ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ በተጋራበት እንዲሁም ደደቢት በአባ ጅፋር በተሸነፈበት ጨዋታ የዛሬዎቹ ተጋጣሚዎች የመሀል ሜዳ ብልጫ ተውስዶባቸው ታይቷል። በውህደት መጠኑ ሲሞገስ የነበረው የደደቢት የአማካይ ክፍል ከመስመር አጥቂዎቹ እገዛን ማግኘት ባለመቻሉ በጨዋታው ሁለቱን ጎሎች ባስተናገደባቸው የመጀመርያ ደቂቃዎች ተበታትኖ ታይቷል። በተለይም ተከላካይ አማካዩ አስራት መገርሳ ክፍተቶችን ለመሙላት ወደፊት ገፍቶ ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ቡድኑ ወደ መከላከል በሚያደርጋቸው ሽግግሮች ወቅት ላይ አማካዩ ትክክለኛው ቦታው ላይ እንዳይገኝ ሲያደርገው በተደጋጋሚ ታይቷል። መከላከያም በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ከተከላካይ አማካዩ በሀይሉ ግርማ ፊት ያሰለፋቸው ሶስቱ የመስመር አማካዮች ሳሙኤል ታዬ ፣ መስፍን ኪዳኔ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ጥምረት ሁነኛ የኳስ አቀጣጣይነት ባህሪ ያለው ተጨዋችን የያዘ ባለመሆኑ የኳስ ቁጥጥር ስኬቱ የወረደ ሆኖ በጨዋታው አብዛኛው ደቂቃዎች በቁጥር በሚያንሰው የሲዳማ የመሀል ክፍል እንዲበለጥ አድርጎታል። ሁለቱ ቡድኖች ይህን ደካማ ጎናቸውን ዛሬም ሳይቀርፉ ወደ ሜዳ የሚገቡ ከሆነ ጨዋታው በተቆራረጡ ቅብብሎች እንዳይሞላ ያሰጋል። ዛሬ ደደቢት በስድስት ጨዋታዎች የአሸናፊነት ጉዞው ወቅት በአማካይ በጨዋታ አንድ ጎል ያስቆጠረው ጌታነህ ከበደ አለመኖር ቡድኑ በዚህኛው እና በቀጣይ ጨዋታዎች በማጥቃት ስትራቴጂው ላይ ሊያደርግ የሚችላቸውን ለውጦችንም የምናይበት ይሆናል። በጥቅሉ ሁለቱም ቡድኖች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በማሳካት ዕድሎችን ለመፍጠር ይሞክሩበታል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ጨዋታ ከመሀል ሜዳ ተሰላፊዎቻቸው ፍልሚያ ውጪ በደደቢት በኩል የመስመር አማካዮቹ የኮሪደር እንቅስቃሴ እንዲሁም በመከላከያ በኩል በሁለተኛ አጥቂነት የሚሰለፈው ተጨዋች በአማካይ ክፍሉ ቅብብሎች ላይ የሚኖረው ተሳታፊነት እና ስኬት የሚኖራቸው ሚንም ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *