ፌዴሬሽኑ የወልዲያን የቅጣት ውሳኔ ሽሯል

የወልዲያ ስፖርት ክለብ ባሳለፍነው ወር ቡድኑን ሳይቀላቀሉ በቀሩት ፍፁም ገብረማርያም ፣ ያሬድ ብርሀኑ እና ታደለ ምሕረቴ ላይ የ150,000 ብር ቅጣት እና የሁለት አመት ዕገዳ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው። ሆኖም ከሶስቱ ተጨዋቾች መሀከል ፍፁም ገብረማርያም እና ያሬድ ብርሀኑ ቅጣቱን አስመልክተው ለፌዴሬሽኑ የዲስፕሊን ኮሚቴ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

ይህን ተከትሎም ኮሚቴው ከትናንት በስቲያ ባደረገው ስብሰባ የተጨዋቾቹን የአቤቱታ ደብዳቤ እና የወልዲያ ስፖርት ክለብ ያቀረባቸውን የመከላከያ ነጥቦችን ተመልክቷል።  በተጨዋቾቹ እና በክለቡ መሀከል ሐምሌ 1 ቀን 2009 የተደረገውን የቅጥር ውል ስምምነት እንዲሁም በዚሁ ዕለት ክለቡ አውጥቶ በስራ ላይ ያዋለው የዲስፒሊን እና የውስጥ መተዳደሪያ ደንብም ለኮሚቴው ውሳኔ ግብዓት መሆናቸው በውሳኔው ተገልጿል።

በዚህም መሰረት ኮሚቴው በክለቡ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተጠቀሱ የቅጣት ዝርዝሮች በተጨዋቾቹ ላይ በቀጥታ መተላለፋቸውን ቢረዳም ውሳኔው ክለቡ ከተጨዋቾቹ ጋር የገባውን ዉል ዓንቀፅ አምስት ያላከበረ መሆኑን ገልጿል። በአንቀፁ መሰረት በተጨዋቾች እና በክለቡ መሀከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በቅድሚያ ጉዳዩ በግልግል ጉባዔ ታይቶ በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት እና ይህ የማይሳካ ከሆነ ግን በውስጥ መመሪያው መሰረት እርምት እንደሚወሰድ ተጠቅሷል። 

በመሆኑም ኮሚቴው ክለቡ የተጠቀሰውን አንቀፅ ቅደም ተከተል ባልጠበቀ መልኩ የቅጣት ውሳኔውን ከማስተላለፉ በፊት በቅድሚያ ጉዳዩ ለግልግል ጉባዔ ቀርቦ መታየት እንደነበረበት አምኗል። በዚህ መሰረትም የዲስፕሊን ኮሚቴው በውሳኔው በተጨዋቾቹ ላይ የተጣለውን ቅጣት የሻረ ሲሆን ክለቡም ከተጨዋቾቹ ጋር በገባው ውል አንቀፅ አምስት መሰረት ጉዳዩን ለግልግል ጉባዔ አቅርቦ መፍትሄ እንዲያፈላልግ ወስኗል።         

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *