” በመልሱ ጨዋታ የምፈራው የዳኝነቱን ነገር ነው እንጂ ተጋጣሚያችን ያን ያህል ከባድ አይደለም ” አዳነ ግርማ

የ2018 የቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የኮንጎው ካራ ብራዛቪልን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዳነ ግርማ ብቸኛ ግብ 1 – 0 ማሸነፍ ችሏል ። ተቀይሮ በመግባት የጨዋታውን ብቸኛ ጎል ካስቆጠረው አዳነ ግርማ ጋር የጨዋታውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ያደረግነው ቆይታ ይሄን ይመስላል።

ስለጨዋታው…

ጨዋታው አሪፍ ነበር። ውጥረት የተሞላበትም ጭምር ነበር ። እኛም አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም ፤ ተቀዛቅዘን ነበር። ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን ወደ ኃላ ላይ ወደ ጨዋታው ተመልሰን ጎልም በማስቆጠር ፋሲካን ፋሲካ አድርገነው ወጥተናል።

ስለተጋጣሚው እንቅስቃሴ…

ከመጀመርያው ጀምሮ ለመከላከል አስበው ነው የመጡት ፤ በጣም ሰአት ያባክኑ ነበር። ከሜዳ ውጭ እንደሚጫወት ቡድን መከላከልን አስበው ነው የመጡት። ወደ ፊት የሄዱበት አጋጣሚ አነስተኛ ነበር። ይህ ሊሆን እንደሚችል አስቀድመን እንጠብቅ ነበር። ግን መጨረሻ ሰአት አግብተንባቸው ማሸነፍ ችለናል። ይህን ውጤት ይዘን በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን አስጠብቀን አሸንፈን እንመለሳለን።

ተቀይሮ ገብቶ ስላስቆጠረው ጎል እና ስላልተቀመበት ሌላ የግብ ዕድል…

በጣም አሪፍ አጋጣሚ ነበር። በጥሩ ሁኔታ በግንባሬ ገጭቼ ጎል አስቆጥሬያለው። ሌላ ሁለተኛ አጋጣሚ አግኝቼ የነበረ ቢሆንም ኢላማውን አልጠበኩም ነበር እንጂ ኳሱን በግንባሬ በደንብ መትቼው ነበር። ብቻ ማሸነፋችን በጣም ደስ ብሎኛል ዋናው እሱ ነው።

ውጤቱ ለመልሱ ጨዋታ የሚኖረው የስነ ልቦና ጠቀሜታ…

ትልቅ ሞራል ነው የሚሰጠን። በአንደኛው ዙር ባልተለመደ መልኩ ብዙ ነጥብ ጥለናል። ደጋፊዎቻችን ከእኛ ብዙ ይጠብቁ ነበር። እንደዚህ ያለ ነገር በጊዮርጊስ ቤት አልተለመደም። ይህን ነገር ለመቀየር ሁለተኛው ዙር ላይ ተለውጠን መጥተናል። ከፋሲል ጀምረናል ዛሬም አሸንፈናል። የአሸናፊነት መንፈሳችን ትልቅ ነበር። አሁን ደግሞ ወደ ቦታው ተመልሷል። አዳዲስ የመጡልን ልጆች አሜ መሀመድ ፣ ሙሉአለም መስፍን እና ጋዲሳ መብራቴ ዛሬ ጥሩ ነበሩ። ከቡድኑ ጋር በጥሩ ሁኔታ እየተላመዱ ነው። ታላቁ ጊዮርጊስን ለመመለስ እየሰራን ነው። ጠንካራውን ጊዮርጊስ በቀጣይ ታዩታላችሁ።

ስለ መልሱ ጨዋታ…

ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ ሲጫወት ዳኛ ይያዝበታል። የዳኝነቱን ነገር ነው እንጂ የምፈራው ተጋጣሚያችን ያን ያህል ከባድ አይደለም። ዛሬ ያጫወቱትን የግብፅ ዳኞች እንዳየሀቸው በጥሩ ሁኔታ ነው ሁለታችንንም ያጫወቱን። ብዙ ጊዜ ጊዮርጊስ ከሀገር ውጭ ሲጫወት ዳኛን ጭምር አሸንፈን የምንወጣበት አጋጣሚ አለ። ስለዚህ ዋናው ዛሬ ማሸነፋችን ነው። የመልሱን ጨዋታም በዚህ የስነ ልቦና የበላይነት አሸንፈን እንመለሳለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *