ሪፖርት | የወልዲያው ጨዋታ በአሳዛኝ ትዕይንት ተቋርጧል

ወልዲያ ፋሲል ከተማን በሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታድየም ያስተናገደበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት የዛሬው መርሀግብር በፋሲል ከተማ 2-1 መሪነት ለመጠናቀቅ ቢቃረብም የመጨረሻ ደቂቃው ክስተት ነገሮችን ቀይሯል።

በድምቀት በተጀመረው ጨዋታ የወልዲያ ደጋፊዎች ከ35 ኪሎ ሜትር ጀምሮ ለእንግዶቹ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ ፋሲሎች ለወልዲያ ስፖርት ክለብ የፋሲል ግምብን ምስል የያዘ ስጦታ አበርክተዋል።

ጨዋታው በጀመረ 4ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ባለሜዳዎቹ ወደ ግብ መድረስ የቻሉት። በአጋጣሚውም በላይ አባይነህ ከርቀት የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል። 7ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው አማካይ ይስሀቅ መኩሪያ ብሩክ ቃልቦሬ በፈፀመበት ጥፋት ተጎድቶ ወጥቷል። ኄኖክ ገምቴሳም ተጨዋቹን ተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል።

በጨዋታው አፄዎቹ በመልሶ መጥቃት አጨዋወት የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ወልዲያዎች ደግሞ ከኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመነሳት ነበር ወደ ፋሲሎች የግብ ክልል ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ የነበረው። በዚህ ሂደት ውስጥ 23ኛው ደቂቃ ላይ የወልዲያ ተከላካዮች ኳስን ከኃላ ለመመስረት ሲሞክሩ የፈጠሩትን ስህተት ተጠቅሞ ሀሚስ ኪዛ የሻገረለትን ኳስ ኤፍሬም አለሙ ወደ ግብ በመቀየር ፋሲል ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ። በወልዲያዎች በኩል 39ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ሸዋለም ከአንዷአለም ንጉሴ ከርቀት የተሻገረለትን ሳይጠቀምበት መቅረቱ ተጠቃሽ ነው።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ወልድያ የተሻለ ተጭኖ መጨወት ችሎ ነበር። ፋሲል ከተማ በአንፃሩ ወደ መጠንቀቁ በማመዘን ሀሚዝ ኪዛን አስወጥቶ ፍፁም ከበደን አስገብቷል። ቢሆንም ወልዲያዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ በአንዷለም ንጉሴ ፣ 61ኛው ደቂቃ ላይ በኤዶም ኮድዞ እንዲሁም በ69ኛው ደቂቃ ላይ በብርሀኔ አንለይ ጥሩ የሚባሉ ሙከራዎችን ማድረጋቸው አልቀረም። ከሶስቱ ተከታታይ ሙከራዎች በኃላ ግን 79ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ከበደ ኳስ በእጁ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አንዷለም ንጉሤ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል። ፉሲሎችም በፍሊፕ ዳውዝ እና ሰንደይ ሙቱኩ ጥሩ የሚባሉ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በድጋሚ መሪ ለመሆን እስከጨዋታው መገባደጃ መጠበቅ ነበረባቸው። በጨዋታው ድንቅ ክህሎቱን ያሳይ ከነበረው የፋሲል ከተማ ግብ ጠባቂ ሚካኤል ሳሚኪ ከርቀት የተላከ ኳስ ከንክኪዎች በኃላ ወደ ወልዲያ ሳጥን ውስጥ ሲደርስ በፋሲል አጥቂ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የ90ኛ ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት ከድር ኸይረዲን ወደ ግብነት ቀይሮት ፋሲል ሁለት ለአንድ መምራት ችሏል።

ሆኖም ከግቡ በኃላ የተወሰኑ የወልዲያ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት በመሀል ዳኛው ለሚ ንጉሴን እና ረዳት ዳኛው ሙስጠፋ መኪ እንዲሁም በክለቡን ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ላይ ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ጨዋታው እንዲቋረጥ ሆኗል። በወቅቱ የደጋፊዎች የእርስ በእርስ ግጭት ባይስተዋልም ከሶስቱ ግለሰቦች በተጨማሪ የወልዲያ ተጫዋች የሆነው ዳንኤል ደምሴ ነገሩ ከተረጋጋ በሆላ ከጭንቀት የተነሳ ራሱን ስቶ ወድቆ ታይቷል።

የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተር ወደ ሆስፒታል አቅንቶ እንዳረጋገጠው ተጨዋች ዳንኤል ሙሉ በሙሉ ተሽሎት ወደ ካምፕ ሲመለስ አሰልጣኝ ዘማርያም እና ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴም ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ ግን ከሌሎቹ በተለየ ጭንቅላቱ ላይ የመፈንከት አደጋ አጋጥሞት አሁንም በሆስፒታል ይገኛል።

የአሰልጣኞች አስተያየት


አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – ፋሲል ከተማ

ጥሩ የጎል አጋጣሚዎችን ስንፈጥር ነበር። እነሱም አልፎ አልፎ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ነበር። በኃላ ግን ውጤቱን ማስጠበቅ ነበረብን። ጉጉት ጫና ፈጥሮብን ነበር። በአጠቃለይ ግን እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ጥሩ ነበር ።
– የአሰልጣኝ ዘማርያምን አሰተያየት በተፈጠረው ሁኔታ ምክንያት ማካተት አልቻልንም።