ስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ትኩረቱን ያደረገው የሁለት ቀናት ውይይት ተጠናቋል

በሀገራችን ስታድየሞች ላይ እየታዩ ባሉ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረገ በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግሮች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ትላንት ማክሰኞ ተጀምሮ እስከዛሬ ተደርጓል፡፡ የደቡብ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ከክልሉ እግር ፌድሬሽን ጋር በቅንጅት ያዘጋጁት ውይይት በሀዋሳ ገዛኸኝ እና እልፍነሽ ሪዞርት ሲካሄድ ቆይቶ ነው የተጠናቀቀው። 

ውይይቱ በርካታ የፕሪምየር ሊግ ፣ ከፍተኛ ሊግ ፣ አንደኛ ሊግ ፣ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና የታዳጊ ወጣቶች ሊግች ላይ የሚሰሩ አሰልጣኞች ፣ ተጫዋቾች ፣ የቡድን እና የደጋፊ ማህበራት አመራሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው የስፖርቱ ባለሙያዎችን እንዲሁም ለእግር ኳሱ ቅርበት ያላቸው የሚዲያ አካላትን በዋነኝት ያሳተፈ ነበር። በርካታ ውይይቶች የተደረጉበት ይህን መድረክ ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የደቡብ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እና አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ የቢሮው የስፖርት ዘርፍ ሀላፊ በበላይነት የመሩት ሲሆን የመወያያ ሰነዶች ተዘጋጅተው ለታዳሚው ቀርበዋል። በየስታድየሞቹ የተፈጠሩት ችግሮችም በምስል በመታገዝ ቀርበዋል።

በክልሉ ሲካሄድ በዚህ አመት ብቻ ለአራተኛ ጊዜ የሆነው ይህ ስብሰባ በርካታ ሀሳቦች ተንሸራሽረውበታል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችም ያልተገቡ ጥያቄዎችን እና የግል ፍላጎታቸውን ያንፀባረቁበትም ነበር። ከእግር ኳሱ ባለፈ ሁሉም የሌላ ስፖርት አካላት ድጋፍ ሊያደርጉለትም ይገባል ተብሏል። በዋነኝነት መንስኤ ሆነው የተቀመጡት ሀሳቦችም በየክለቦች ውስጥ ዝቅተኛ አቋም የሚያሳዩ ተጫዋቾች ተመልካቹን ለፀብ መገፋፋታቸው ፣ የዳኞች ውሳኔ መጓደል ፣ የክለብ አመራሮች የእግር ኳሱ በቂ እውቀት ያሌላቸው መሆኑ እና በአመራርነታቸው ለመቆየት ሲሉ ከእግር ኳስ ውጪ የሆኑ ድርጊቶች ላይ መሳተፋቸው ፣ ክለቦች ችግር ፈጣሪ ሆነው የፈጠሩትን ክፍተት አለማመናቸው ፣  የአሰልጣኞች በቂ እውቀትን ሳይዙ መገኘት ፣ የደጋፊው በስሜት የተሞላ ድጋፍ አሰጣጥ ፣ በዋነኝነት አሰልጣኞች በቴክኒክ ክልል ጨዋታ እየመሩ የሚያሳዩት ስሜታዊ ድርጊት (ለምሳሌ የውሀ ፕላስቲኮችን መምታት ፣ ወደ ደጋፊዎች ዞሮ መቀስቀስ) የመሳሰሉት ድርጊቶች ናቸው በማለት ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። በውይይቱ የተነሱት እንደዚህ ችግሮችን ለመቅረፍ አስፈላጊ ናቸው ተብለው የተነሱ ነጥቦችም ነበሩ።

አመራሮች በስፖርት እውቀት ማለፍ አለባቸው ፣ እግር ኳሱን የሚያውቅ ሰው መምራት አለበት ፣ በእግር ኳሱ ሰበብ የግል ጥቅማቸውን የሚፈልጉ ሰዎችን ከሀላፊነት መነሳት አለባቸው ፣ ፌዴሬሽኑ ከጠቅላላ ጉባኤ ውጪ ክለቦችን መገምገም አለበት ፣ በሜዳ ላይ የፀጥታ አካላት ስራቸውን አክብረው ቡድኖችን በዕኩል እይታ ማየት አለባቸው ፣ ክለቦች ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የሚፈጥሩትን ችግር የእኔነት ስሜት ኖሯቸው አምነው መቀበል አለባቸው ፣ ሁከት አስነሺውን ከወገናዊነት በፀዳ መልኩ ለሚመለከተው አካል መጠቆም እና መቃወም አስፈላጊ ነው ፣  ክለቦች ስለ ስፖርቱ ህጎች ለተጨዋቾቻቸው ለአጠቃላይ የቡድን አባሎቻቸው ስልጠናዎችን መስጠት አለባቸው ፣ ለዳኞችም እንዲሁ ለሙያቸው እገዛ የሚያደርጉ ስልጠናዎች ሊዘጋጁ ይገባል እንዲሁም ሚዲያው ባለው ችግር ልክ መስራት እና የጋራ ርብርብ ማድረግ አለበት የሚሉ እና ሌሎች የመፍትሄ ሀሳቦች ተነስተው እና ውይይት ተደርጎባቸው ፕሮግራሙ  ፍፃሜውን አግኝቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ከመሰል ተደጋጋሚ ውይይቶች የሚነሱ ነጥቦችን ወደ ታች አውርዶ የመስራት ችግሮች እየተስተዋሉ የመጡ በመሆኑ አሁንም በአፅንኦት ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባልም ተብሏል፡፡