የወልዋሎ ሜዳን ሳር የማልበስ ስራ ተጀምሯል

በ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አነጋጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ወልዋሎ ዓዲግራት ዩንቨርስቲ ጨዋታዎቹን የሚያደርግበት ሜዳ አንዱ ነበር። በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ አፈራማ የሆነው ሜዳ ደረጃን አሻሸሎ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ብቁ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

የግንባታውን ሒደት በመምራት ላይ የሚገኙት አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ ከሶከር ኢትዮጽያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሜዳውን ስራ ሒደት አብራርተዋል። ” ውድድር ከተጠናቀቀ ጊዜ አንስቶ ግንባታ ለመጀመር ተንቀሳቅሰናል። ሜዳውን በአዲስ መንገድ መስራትም ጀምረናል። አሁን ያለበት ደረጃ የበፊቱን አፈር ሙሉ ለሙሉ ለማንሳት ቁፋሮ ላይ ስንሆን ቆፋሮው ከተጠናቀቀ በኋላ የገራጋንቲ ሙሌት የምናደርግ ይሆናል። እነዚህን ተግባራት ለማጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ ነው የሚቀረን። በመቀጠል የአሸዋ እና የለም አፈር ሙሌት ከተከናወነ በኋላ የሳር ተከላውን ጨረታ የምናወጣ ሲሆን የፍሳሽ ስራዎችም በተጓዳኝ በመስራት ላይ እንገኛለን። ሜዳውን ለመስራት አስቸጋሪ እንዳይሆንብን ቀደም ብለን ጥናት አድርገን ወደተግባር የገባን በመሆኑ እስካሁን ችግር አላጋጠመንም።” ብለዋል።

በአካባቢው የውሀ እጥረት ከመኖሩ ጋር በተያያዘ የሳር ተከላው ከተጠናቀቀ በኋላ በቂ እርጥበት ባለማግኘት መልሶ ወደቀደመ መልኩ ይመለስ ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። የግንባታ ባለሙያው አቶ ገብረእግዚአብሔር ግን ለዚህ መላ ተበጅቶለታል ይላሉ። ” ከሜዳ ስራው በተጓዳኝ በስታድየሙ አቅራቢያ የውሃ ጉድጉድ ቁፋሮ የሚደረግ ሲሆን ይህም ቆፋሮ ሲያልቅ ለሜዳው የሚሆን በቂ የውሃ አቅርቦት ከዚህ የምናገኝ ይሆናል። ” ብለዋል።

ክለቡ ከመጫወቻ ሜዳው በተጨማሪ የተመልካች መቀመጫ ቦታን የማስፋት ስራ ቢጀምርም በብረት እጥረት ምክንያት ለጊዜው እንደቆመና አቅርቦቱ ሲሟላ እንደሚቀጥል የተገለፀ ሲሆን በአጠቃላይ ስራውን ለመጨረስ ይህን ወር ጨምሮ የሶስት ወር ጊዜ እንደሚያስፈልግ ተነግሯል። የግንባታው ሒደት ይፈጃል በተባለው የሶስት ወር ጊዜ ውስጥ እስኪጠናቀቅ ምናልባትም የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ሊጀመር ይችላል። የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ገብረህይወትም ሁኔታውን ከግምት እንዳስገቡትና የመጀመርያዎቹን የሊግ ጨዋታዎች መቐለ ላይ ለማድረግ መታቀዱን ገልፀውልናል።

የወልዋሎ ስታድየም ከሜዳው ስራ በኋላ በተለያዩ ወቅቶች በሚደረጉ ግንባታዎች በመጨረሻ ይህን ገፅታ ይላበሳል ተብሎ ይጠበቃል።