ሽመልስ በቀለ እና ሙሉዓለም መስፍን ስለ ኬንያው ጨዋታ…

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ  ማጣሪያ ከኬንያ ጋር ስለሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ የቡድኑ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ሽመልስ በቀለ እና ሙሉዓለም መስፍን ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

ሽመልስ በቀለ 

ቡድኑን የተቀላቀልከው ከዘገየ ቢሆንም ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል ?

ቡድኑን ከተቀላቀልኩት አጭር ጊዜ ቢሆንም ጥሩ ነው። በፊት ከነበረው ነገር የወጣ ነገር ባልመለከትም ተጫዋቾቹ ላይ ጥሩ የመነቃቃት ነገር አይባቸዋለው። በሴራሊዮኑ ጨዋታ ጊዜ የነበረው ነገር ነው አሁንም ያለው እንቅስቃሴ ፤ ለኔ የሚታየኝ እንደዛ ነው። ምናልባት አዲስ ሊሆንሚችለው ባህርዳር ላይ መሆኑ ነው። የመጫወቻ ሜዳው ከሀዋሳ የተሻለ በጣም ጥሩ ሜዳ ነው። በመሆኑም ሜዳው ጥሩ ነገርን ይፈጥርለናል ብዬ ነው የማስበው። በሴራሊዮኑ ጨዋታ ብዙ ስህተት ሰርተን ነበር። አሁን ግን ሜዳውም ስለሚያግዘን ጥሩ ውጤት ይዘን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ ፤ በልምምድም ያን ነገር እያየን ነው ፡፡

የባህር ዳር ሜዳ (ሳሩ) አመቺ ነው ብለሀል። አመቺነቱን ተጠቅሞ ውጤት ለማስመዝገብ በተለየ መልኩ የሰራችሁት ስራ ይኖራል?

ለአንድ ጨዋታ ሜዳ በጣም ተፅዕኖ ያደርጋል። ኳስ በምትቀባበልበት ወቅት በጣም ተፅዕኖ አለው ፤ እና በዚህ ሁለት ቀን መጥቼ የሰራነው ልምምድ  ከመጀመሪያው ምን ያህል ለውጦችን የሚያሳይ መሆኑን አይቻለሁ። በአጭር ቦታ ላይ አራት ለአራት በመሆን እንዲሁም ሜዳው ሰፍቶህ የምትጫወተው ጨዋታ የተለየ ነገር ነው።

ቡድኑ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ አጭር የዝግጅት ወቅት (ዘጠኝ ቀናት) ነበረው። የዝግጅቱ ቀናት ማነስ ተፅዕኖ አይፈጥርም ትላለህ ?

ተፅዕኖ ብዬ የማስበው ከጨዋታ ስትርቅ የሚኖረውን ነው። በልምምድ ግን ዕርስ በዕርስ ትተዋወቃለህ። በውድድር ላይም ስላለን ብቃታችንም እንደዛው ነው። የመዋሀዱ ነገር በተጫዋቾቹ ላይ የተመሰረተ ነው። ለዚህኛው ጨዋታ ግማሾቹ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ብዙም አላረፉም። ዋናው አዕምሮ ነው በሌላው ዓለም አንድ ጨዋታ ለማድረግ ሳምንት ወይም አራት ቀን ሲቀረው ነው ከቡድናቸው ጋር የሚቀላቀሉት። ውድድር ላይ ስለሆኑ ብቻ ግዴታ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ ባይጠበቅም ዕርስ በዕርስ በሚኖርህ ነገር የተሻለ ነገር ይመጣል ብዬ አስባለሁ።

በግብፅ ሊግ እያሳየህ ያለህው ብቃት እጅግ አስገራሚ ነው። በሴራሊዮኑ ጨዋታም ጥሩ ነበርክ። በነገው ጨዋታ እንደ ግልም ሆነ እንደ ቡድን ምን እንጠብቅ ?

እንደ ቡድን ነው መናገር ያለብኝ። እንደ ቡድን ደግሞ ስናገር እኔ ብቻ አደለሁም ፤  አንድ ሰው ተነጥሎ ሊወጣ አይችልም። ለምሳሌ ሜሲ በአንድ ቡድን ተነጥሎ ወጥቶ ጥሩ ሊሆን ይችላል። እኛጋም እንደዛ ማድረግ የሚችሉ ተጫዋቾች አሉ። እንደ ቡድን ማሰብ ግን ስላለብን ሁሉም በየቦታው አንድ አይነት ኳሊቲ አላቸው። እኔም በግብፅ ያለኝን ነገር አምጥቼ ማሳየት ብቻ ሳይሆን እዛ ከነበረኝ በተሻለ እዚህ ማሳየት ያለብኝ። ይህን ስል ብሔራዊ ቡድን በጣም ከባድ ነው። ለምሳሌ ሜሲ እና ሮናልዶ በቶርናመንት ሚያስቆጥሯቸው ጎሎች በጣም ትንሽ ናቸው። ይህ ለክለብ እና ለሀገር መጫወት ያለው ልዩነት ማሳያ ነው። ወደኛ ስንመጣ ማንም ጎል ያግባ ምንፈልገው ውጤት ነው። እኔ ለክለቤ ማደርገው ክለቤ ስለሆነ አይደለም ለጎል በቀረብኩበት ሰዓት ግን ግብ አስቆጥራለሁ። ወደዚህ ግን ስትመጣ ከባድ ነው። በክለብ ብዙ ነጻነት ኖሮኝ ልጫወት እችላለሁ። እዚህ ግን በነፃነት እጫወታለሁ ብል እኔ ብቻ አደለሁም። ይህም ማለት ያ አንድ ክለብ ነው ፤ ይሄ ደግሞ አንድ ሀገሬ ነው። ከዚህም የተነሳ ብዙ ነገሮችን ልታጣ ትችላለህ።  እኔም በተቻለኝ ሁሉ ወደ ጎል እየቀረብኩኝ ለጎደኞቼ በጣም ብዙ ነገር እያደረኩ የተሻለ ነገርን ፈጥራለሁ ብዬ አስባለሁ። ብዙ ጊዜ እኔ ወደ ብሔራዊ ቡድን ስመጣ  እንደ አዲስ አልሆንም። መጀመሪያ እንደመጣሁ አድርጌ ነው ማስበው። ያም ነገር ውስጤ ውስጥ ስላለ ራሴን ዘና አድርጌ መመልከት አልፈልግም። 


ከዚህ ጨዋታ በኃላ በቀናት ውስጥ ከኬንያ ጋር በድጋሚ ትጫወታላችሁ…

የቀኑ መጥበብ የደርሶ መልስ ጨዋታም መሆኑ ለነሱም ሆነ ለእኛ ከባድ ነው የሚሆነው። ተጋጣሚያችንን እናከብራለን። አሰልጣኞቻችን የሚሰጡን ምስሎች አሉ። እነሱን እናያለን፤ ኬንያ ጋናን አሸነፈች ሲባል በጣም ነው ሲገርመን የነበረው። ግን ዛሬም ትላንትናም ስናየው በወቅቱ የተሻለ ሆና የቀረበችሁ ጋና ነበረች። ብዙ ኳሶችንም ስታለች። ኬንያ ምንድናት ብለን ምስሉን ስንመለከት በራስ መተማመን እንዲሰማን ሆኗል። የቀኑ ማጠር አሁን ለምንጫወተው ጨዋታ ነጥቡ ወሳኝነት አለው። እዚህ ላይ ውጤት የምንይዝ ከሆነ ያሉንን ሁለት ጨዋታዎች በሂደት የምናየው ይሆናል።

ሙሉዓለም መስፍን

ዝግጅታችሁ እንዴት ነው?

ዝግጅታችን በተወሰነ መልኩ አሰልጣኛችን ከያዘው ፕሮግራም አንፃር የተስተጓጐለ ነው የሚመስለኝ ፤ ተስተጓጉሏልም። ምክንያቱ ደግሞ የጥሎ ማለፉ ውድድሩ ከአምናው ወደ ዘንድሮ የተላለፈ በመሆኑ ነው። እሱ ማለቅ ስለነበረበት በተወሰነ መልኩ መስተጓጐል ነበረበት። ቢሆንም ግን ጥሩ ነገር እየሰራን ነው። በምስል ቪዲዮ በተደገፉ የክላስ ውስጥ ትምህርቶች በመስጠት ከሜዳ  በተረፈ ስራዎች ተሰርተዋል። እናም ምንም አጭር ቢሆን ጥሩ ነው ብዬ ነው የምገምተው። እንዲሁም ባለፈው የነበሩ ልጆች ስለሆኑ ምንም የተለየ ነገር የለውም። ማጠሩም ያን ያህል ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም።  በእኔ በኩል በጥሩ  እየሄደ ነው ዝግጅታችን።

ሀዋሳ ላይ ረጅም የዝግጅት ጊዜ ነበር የወሰዳችሁት ወደ ባህርዳር  ስትመጡ ግን አጭር የዝግጅት ጊዜ ነበር…

ጊዜው ተገኝቶ ቢሆን እና በተያዘለት ፕሮግራም ብንሰራ ከዚህ የበለጠ ነገር መስራት ይቻል ነበር። ያ አልሆነም። ያስላልሆነ ደግሞ  እንደ አማራጭ ባለን ጊዜ መስራት እና መዘጋጀት ነው ያለብን። ያንን አድርገናል። በእኔ በኩል ያን ያህል ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ግን ፈፅሞ ተፅዕኖ የለውም ማለትም አይቻልም። በተወሰነ መልኩ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ምክንያቱ አሰልጣኙ የሚያስበው ብዙ ነገር ይኖራል። በዚህ በአንድ ሳምንት ውስጥ ደግሞ ልስራ ቢል በጣም ጫና ይኖረዋል። ሆኖም ግን በተለየ መለኩ ተዘጋጅተናል ከእግዚአብሔር ጋር ጥሩ ነገር እንሰራለን።


የቡድናችሁ መንፈስ ምን ይመስላል ?

ደስ ይላል ስሜቱ። ልምምድ ሜዳ ጀምሮ  ያለው ነገር ለመስራት የሚያነሳሳ ነው። ሰውም ደስ የሚልነዉ። ልምምድ ቦታ መጥቶ ሚያበረታታ ነው። በጣም ደስ የሚል እና የሚያነሳሳ ነው።  የቡድኑ መንፈስ አጅግ በጣም ጥሩ ነው ብየ ነው የማምነው። በጣም ጥሩ የሆነ ነገር አለ። ቡድኑ ውስጥ አሰልጣኙም ያ እንዲሆን በ ብዙ መልኩ እየሰራ ነው እና ጥሩ ነገር  እና አንድነት ቡድኑ ውስጥ እየመጣ ነው ።

የሴራሊዮን ጨዋታ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ለመሸፈን አሰልጣኙ የተለየ ነገር ሲያደርግ ነበር ?

አዎ ብዙ የተለዩ ነገሮች ሲያደርግ ነበር። ክፍተቶችን ለመሸፈን የሴራሊዮኑን ጨዋታ በተንቀሳቃሽ ምስል ደጋግመን  ስናይ ነበር።  ከዛጋ የነበሩ ክፍተቶች ለምሳሌ ያህል የማጥቃት ዞን ውስጥ ስንገባ የመጣደፍ እና ያለመረጋጋት ነገሮች ነበሩ።  ማጥቃት አካባቢ ስንደርስ ምን ማድረግ እንዳለብን ተንቀሳቃሽ ምስሎች አይተን ከነሱ ተምረን በብዙ መልኩ ክፍተቶች ለመሸፈን እየተሰራ ነው። እንዲሁ ሌሎች ቦታዎች ላይ የነበሩ ክፍተቶችን የማረም ስራም ሜዳ ላይ እየሰራን ነው ፤ ተሻሽለን እንቀርባለንም ብለን አንስባለን ።

በባህርዳር ነው ጨዋታውን የምታደርጉት እና ከህዝቡ ምን አይነት ድጋፍ ትጠብቃለህ ? ምታስተላልፈዉ መልእክትም ካለ?

የባህርዳር ህዝብ ለድጋፍ አዲስ አይደለም። ብሄራዊ ቡድኑን ያውቀዋል። ከዚህ በፊት እዚህ መጥቶ ውጤት አጥቶ አያውቅም። ምክንያቱም የህዝብ ድጋፍ ከፍተኛ ነው። በጣም ያንን ነገር እንዲያደርጉ ነው ምንፈልገው። እኛም ውጤቱም ለማምጣት የበኩላችንን  እናደርጋለን። ህዝቡም እንደ ከዚህ በፊቱ ከዛም በበለጠ መልኩ ከእኛ ጋር እንዲቆም እንጠይቃለን ።