ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ – ቅድመ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ ሀዋሳ ላይ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ጅማሮውን ያደርጋል። ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታም ሀዋሳ ላይ የሚከናወን የዛሬ ብቸኛው መርሐ ግብር ነው። 
በሊጉ ከአራቱ ጨዋታዎች ሦስቱን በማከናወን አምስት ነጥቦችን የሰበሰበው ሲዳማ ቡና በሁለት አቻ እና አንድ ድል ከሸንፈት ርቆ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እያለው ይህንን ጨዋታ ያደርጋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ በመጀመርያው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ በሜዳው ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ሁለተኛ ጨዋታውን ባለፈው ሳምንት ስሑል ሽረን 4-0 አሸንፎ ወደ ድል መመለስ ችሏል። ጊዮርጊስ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት ነው ሲዳማ ቡናን የሚገጥመው። 

በጨዋታው ባለሜዳው ሲዳማ ቡና እንደተለመደው በመስመር አጨዋወት ላይ በተመሰረተ እንቅስቃሴ የጎል እድሎችን በመፍጠር ድል ይዞ ለመውጣት እንደሚጥር ይጠበቃል። ሆኖም ለዚህ አቀራረቡ ሲያግዙት ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል ሐብታሙ ገዛኸኝን በቅጣት ማጣቱ የማጥቃት ኃይሉን እንዳያዳክመው እና በአዲስ ግደይ ላይ ብቻ እንዳይንጠለጠል ያሰጋዋል። ቡድኑ በአንፃራዊነት ጠንካራ ከሚባል የተከላካይ መስመር ጋር የሚገናኝ በመሆኑና በተመሳሳይ የመስመር የበላይነትን ለመውሰድ የሚጥር ቡድንን የሚገጥም በመሆኑ ከባድ ፈተና እንደሚጠብቀው ይገመታል። 

ከሜዳው ውጪ የዓመቱ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታውን የሚያደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ሳምንት በሰፊ ውጤት ድል ቢያስመዘግብም ሙሉ ለመሉ ወደ ቀደመ አቋሙ ስለመመለሱ ጥያቄ የሚነሳበት ቡድን ነው። ለአዲሱ አሰልጣኝ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ጨዋታ እንደመሆኑም በምን አይነት አቀራረብ ወደ ሜዳ እንደሚገባ መገመት አስቸጋሪ ነው። ሆኖም የቡድኑ ጠንካራ ክፍል የሆነውና በአማካዮች ሽፋን የሚያገኘው የተከላካይ መስመር ለቡድኑ ድል ዋንኛውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል። 

በሁለቱ ግንኙነት ከሚጠበቁት የሜዳ ላይ ጉዳዮች ሌላኛው ሊጠቀስ የሚገባ ጉዳይ ያለፈ ታሪካቸው ነው። ሲዳማ ቡና የዛሬ ተጋጣሚውን አሸንፎ ካለማወቁ አንጻር በስነ ልቡና የበላይነት ሊወሰድበት እንደሚችል ይገመታል። ሆኖም የሜዳው ጨዋታዎችን ወደ ሀዋሳ ከቀየረና አልፎ አልፎ አምና ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገዱ በመልካምነቱ የሚጠቀስ ነው። 

በሲዳማ ቡና በኩል ሐብታሙ ገዛኸኝ በአዳማው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክነያት የማይሰለፍ ሲሆን አጥቂው ጸጋዬ ባልቻ ከጉዳት ይመለሳል። ባለፈው ሳምንት ያልተሰለፈው ግብ ጠባቂው መሣይ አያኖም ወደ መጀመርያ አሰላለፍ እንደሚመለስ ይጠበቃል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ አሁንም የሳላሀዲን ሰዒድ፣ ጌታነህ ከበደ እና መሐሪ መናን ግልጋሎት በጉዳት በዚህ ጨዋታ አያገኙም። 
እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 18 ጊዜ በሊጉ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 13 ድል በማስመዝገብ የበላይ ነው፡፡ 5 ጊዜ አቻ ሲለያዩ ሲዳማ ቡና በፕሪምየር ሊጉ በታሪኩ ቅዱስ ጊዮርስን አሸንፎ አያውቅም፡፡

– ሁለቱ ቡድኖች 5 ጊዜ አቻ ሲለያዩ በሁሉም ግብ አልተቆጠረም (0-0)

– በተገናኙባቸው 18 ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 27 ጎሎች ሲያስቆጥር ሲዳማ ቡና 6 አስቆጥሯል፡፡

– በሲዳማ ቡና ሜዳ ላይ ሁለቱ ቡድኖች 9 ጊዜ ተገናኝተው 6 ጨዋታዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ 3 ጨዋታዎች በአቻ  ውጤት ተፈጽመዋል፡፡

– ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 1-0 ውጤቶች ሲያሸንፍ ባለፉት 5 ተከታታይ ግንኙነቶች ሲዳማ ቡና አንድም ጎል ማስቆጠር አልቻለም።

– ሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ካስቆጠራቸው 6 ግቦች መካከል በሜዳው ማስቆጠር የቻለው አንድ ጎል ብቻ ነው። 

ያለፉት 3 ጨዋታዎች አቋም 

(በሁሉም ውድድሮች)

ሲዳማ ቡና | አሸነፈ | አቻ | አቻ

ቅዱስ ጊዮርጊስ | ተሸነፈ (መለያ ምት)| ተሸነፈ | አሸነፈ

ዳኛ 

ፌዴራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ይህን ጨዋታ እንዲመራ ተመድቧል። ይህ ጨዋታ ለኃይለየሱስ ሁለተኛ ነው።
ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሃ – ፈቱዲን ጀማል – ግርማ በቀለ – ግሩም አሰፋ

ሰንደይ ሙቱኩ – ዮሴፍ ዮሀንስ – ዳዊት ተፈራ

ጸጋዬ ባልቻ – መሐመድ ናስር – አዲስ ግደይ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

አብዱልከሪም መሐመድ – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ኄኖክ አዱኛ

ሙሉዓለም መስፍን – ምንተስኖት አዳነ – ናትናኤል ዘለቀ

አሌክስ ኦሮቶማል – አሜ መሐመድ – አቡበከር ሳኒ