ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኤሌክትሪክ እና ንግድ ባንክ ድል አስመዝግበዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዓርብ ጀምሮ ሲካሄዱ ዛሬም ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው ኤሌክትሪክ እና ንግድ ባንክ ድል አስመዝግበዋል።

አዲስ አበባ ስታዲየም ጥሩነሽ ዲባባን ያስተናገዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል፡፡ ባለ ሜዳዎቹ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተሻሉ በነበሩት የመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ግብ በመድረስም ፍፁም የተሻሉ ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈትን ያስተናገዱት ኤሌክትሪኮች በዛሬው ጨዋታ ጫና መፍጠር የጀመሩት ገና በማለዳ ነበር፡፡ በ14ኛው ደቂቃ ቅድስት አባይነህ ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ በግንባሯ ገጭታ ወደ ግብ ብትሞክርም ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥታለች። በተመሳሳይ በ17ኛው ደቂቃ ላይ ዓለምነሽ ገረመው የጥሩነሽ ተጫዋቾችን ስህተት ተጠቅማ ያቀበለቻት ኳስ ወርቅነሽ ሚልሚላ በቀጥታ ወደ ግብ ብትልከውም ድንቡሽ አቦ በግሩም ሁኔታ ልታድንባት ችላለች፡፡

በ21ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪኮች በአጥቂያቸው ወርቅነሽ ሚልሚላ ላይ በተሰራው ጥፋት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ዓለምነሽ ገረመው አስቆጥራ ቡድኗን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች፡፡ በመቀጠልም በጨዋታው ድንቅ ብቃቷን ማሳየት የቻለችው አለምነሽ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ የላከቻት ኳስ ደንቡሽ አቦን አልፋ ከመረብ ተዋህዳ የኤሌክትሪክን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች። ከተጋጣሚያቸው አንጻር ፍጹም ደካማ የነበሩት ጥሩነሽ ዲባባዎች በ36ኛው ደቂቃ ጤናዬ ለተሞ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላከቻትና እስራኤል ከተማ ካዳነችባት ኳስ ውጪ ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩነሽ ዲባባዎች ከመጀመሪያው በተሻለ መቀሳቀስ ሲችሉ በአንጻሩ ኤሌክትሪኮች ከመጀመሪያው አጋማሽ ተዳክመው ቀርበዋል፡፡ እምብዛም በግብ ሙከራዎች የታጀበ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በኢትዮ ኤሌክትሪኮች የ2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፤ በዚህም ውጤት መሠረት ኤሌክትሪክ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል በሦስተኛው ሳምንት ማሳካት ችሏል፡፡

በሌላ ጨዋታ ዲላ ላይ ጌዴኦ ዲላን የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 በማሸፍ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል፡፡ በክረምቱ ደደቢትን ለቃ ወደ ሀምራዊ ለባሾቹ ያመራችው ብርቱካን ገብረክርስቶስ በ88ኛው ደቂቃ ያስቆጠረችው ጎል ነው ንግድ ባንክን ድል ያስጨበጠው።