ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በሜዳው ሁለተኛ ጨዋታውን አሸንፏል

በ6ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሀግብር ዛሬ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ደቡብ ፖሊስን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

እንደወትሮው ሁሉ የሶዶ ስታድየም በተመልካች የተሞላ ሲሆን ፤ ጨዋታው መጀመር ከነበረበት ሰዓት ስድስት ደቂቃዎችን ዘግይቶ 9:06 ላይ በኢትዮጵያ ቤሔራዊ መዝሙር ታጅቦ ተጀምሯል።

ወላይታ ድቻ በ5ኛው ሳምንት መርሀግብር ከኢትዮጰያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርቶ ከተመለሰው ስብስብ ውስጥ ኄኖክ አርፊጮን በያሬድ ዳዊት ፤ ሙባሪክ ሽኩርን በዐወል አብደላ እንዲሁም ሳምሶን ቆልቻን በፀጋዬ ብርሃኑ በመተካት ሲገባ በአንፃሩ ደቡብ ፖሊስ ባሳለፍነው ሳምንት ሽንፈት ካስተናገደበት ስብስብ ውስጥ በጉዳት ያረፉ እንዲሁም ወደ ተጠባባቂ የተመለሱ ተጫዋቾችን ጨምሮ ሠባት ለውጦችን አድርጓል። በለውጦቹም ፍሬው ገረመው ፣ ዮናስ በርታ ፣ አዳሙ መሐመድ ፣ ብርሃኑ በቀለ ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ ፣ ብሩክ አየለ አና ልዑል ኃይሌ ከቋሚ አሰላለፍ የወጡ ሲሆን በምትካቸውም ዳዊት አሰፋ ፣ ሳምሶን ሙሉጌታ ፣ ቢኒያም አድማሱ ፣ በኃይሉ ወገኔ ፣ መስፍን ኪዳኔ ፣ ኄኖክ አየለ እና አናጋው ባደግ ተክተዋቸው ወደ ሜዳ ገብተዋል።


የመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች መስተናገድ ያልቻሉበት እና የፉክክር መንፈስ ያልነበረው ሆኖ አልፏል። በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ውስጥ ወላይታ ድቻዎች ኳስን መሀል ለመሃል መስርትው ለመውጣት እና በብቸኝነት ላሰለፋት አጥቂ አንዱዓለም ንጉሴ ለማድረስ ቢሞክሩም መሀል ሜዳ ላይ በተደጋጋሚ ኳሶች እየተቆራረጡ ሲቀሩባቸው ተስተውለዋል። በነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ ደቡብ ፖሊሶች ባገኟቸው ኳሶች ተጠቅመው ወደ ሁለቱም መስመሮች ለመጣል ጥረት ሲያደርጉም ነበር። በተለይም በግራ መስመር ላይ ተሰልፎ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ብሩክ ኤልያስ የድቻን የተከላካይ ክፍል በመጠኑም ቢሆን ማስጨነቅ ችሏል። በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ወላይታ ድቻዎች በተለይም ከ25ኛው ደቂቃ በኃላ በበረከት ወልዴ ፣ አብዱልሰመድ ዓሊ እንዲሁም በኄኖክ ኢሳያስ አማካይነት ኳስን በተረጋጋ ሁኔታ ማንሸራሸር የቻሉ ቢሆንም አንድም የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።ሁለቱም ቡድኖች በረጃጅም ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም በጭማሪ ደቂቃ ከመዓዘን የተሻማ ኳስ አብዱልሰመድ ዓሊ ከሳጥን ውጪ አግኝቶ ወደ ጎል ሞክሮ ከወጣችበት ኳስ ውጪ ጨዋታው ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳይስተናግድበት ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወደ ግብ የቀረቡ ሙከራዎች የተስተዋሉበት እንዲሁም የዕለቱ ብቸኛ ግብም የተገኘችበት ክፍለ ጊዜ ነበር። በ48ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር የተሰለፈው የድቻው ፀጋዬ አበራ ሁለት የደቡብ ፖሊስ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ያሻማውን ኳስ ከግብ ጠባቂው አጠገብ ይገኝ የነበረው አንዱዓለም ንጉሴ በግንባሩ ሲገጭ የግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ስህተት ታክሎበት መረብ ላይ አርፋለች። ከዚህች ጎል መቆጠር በኃላ በይበልጥ በተነቃቁት ባለሜዳዎቹ ድቻዎች በኩል በተደረገ መከራ በመስመር በኩል ከአንዱዓለም ንጉሴ ጋር በመቀባበል 60ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ ያገኘውን ኳስ ወደ ወጪ ልኳታል።


ደቡብ ፖሊሶች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ የጀመሩት መሉዓለም ረጋሳን በ62ኛው ደቂቃ ቀይረው ካስገቡ በኋላ ሲሆን የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ድቻ የግብ ክልል ሲገቡ ተስተውሏል። በዚህም መሰረት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ብሩክ ኤልያስ በ66ኛው ደቂቃ ጥሩ የግብ ዕድል አግኝቶ ሲሞክር በውብሸት አለማየሁ ተደርባ የወጣችበት ሲሆን በ68ኛው ደቂቃ ሙሉዓለም ረጋሳ ጥሩ አድርጎ የመታት ቅጣት ምትም በታሪክ ጌትነት ተመልሳለች። በ78ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ድቻዎች ባገኙት የቅጣት ምት ኄኖክ ኢሳያስ ሲያሻማ እሸቱ መና በግንባሩ ወደ ውስጥ ሞክሮ ሳጥን ውስጥ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ቸርነት ጉግሳ በግንባሩ ቢገጭም ዳዊት አሰፋ አድኖበታል። ግብ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች በጨዋታው የመጨረሻ እና የሚታስቆጭ የግብ ዕድል በ90ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ አናጋው ባደግ ከተከላካዮች ጀርባ ገብቶ ቢጨርፈውም ታሪክ ጌትነት እንደምንም አድኗታል። በዚህም መሰረት ወላይታ ድቻ በተከታታይ ያደረጋቸውን ሁለት የሜዳው ላይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ወሳኟን ሦስት ነጥብ ሲያሳካ በአንፃሩ ደቡብ ፖሊስ ጥሩ ያልሆነውን የሊጉን አጀማመር ገፎቶበታል።