ቅዱስ ጊዮርጊስ ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገባ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዋሳ ከተማው ጨዋታ አስቀድሞ የተከሰተውን የደጋፊዎች ግጭት አስመልክቶ ዝርዝር ሁኔታውን ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አሳወቀ።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል ባሳለፍነው እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም ሊደረግ ከነበረው ጨዋታ አስቀድሞ በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ጨዋታው ወደ ሰኞ ተሻግሮ በዝግ በመካሄድ 0-0 በሆነ ውጤት ቢጠናቀቅም ብዙ አስገራሚ ትዕይንቶች የተስተናገዱበት ሆኖ ማለፉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በወቅቱ የተፈጠረውን ሁኔታ በዝርዝር የሚያስረዳ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ማስገባቱን ክለቡ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አሳውቋል። የደብዳቤው ፍሬ ሀሳብ በሦስት መሰረታዊ ነጥቦች ላይ ያተኮረ ሲሆን የመጀመርያው የፀጥታ አካላትን ችግሩ ከመፈጠሩ አስቀድሞ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎችን ተቀራርበው እንዳይቀመጡ ለመከላከል ክለቡ የጠየቀው ጥያቄ በቂ ምላሽ አለማግኘቱ ለተፈጠረው ችግር መነሻ መሆኑን የሚያስረዳ ነው።

በሁለተኝነት የዕለቱ የጨዋታው ኮሚሽነር ጨዋታውን ለማስጀመር የሚያስችል በቂ የፀጥታ አካል መኖሩን ዋስትና ቢያገኙም የተቀመጠውን የእግር ኳስ ደንብ አልተረጎሙም። በመሆኑም የተሰጣቸውን ኃላፊነት እና ተግባር በብቃት መወጣት ያልቻሉ በመሆናቸውም የሥነ ሥርዓት ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚጠይቅ ነው። ክለቡ በሦስተኛነት ባስቀመጠው ነጥብም የሀዋሳ ከተማ የቡድን ተወካዮች በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች የዕለቱን ሁኔታ አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት መሠረተ ቢስና ከንቱ ውንጀላ መሆኑን ያትታል።

በመጨረሻም ክለቡ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ በመግለፅ

በቀጣይም እያንዳንዱ የውድድር ተሳታፊ ክለብ አመራር ፌዴሬሽኑ ላወጣቸው ደንቦች እና ህጎች ተገዢ መሆን እንዳለበት እንዲሁም የስርዓት አልበኝነት ስሜት ለስፖርቱ ሰላም ጠንቅ እንደሆነ በመገንዘብ ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ዕርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ በማሳሰብ ያበቃል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የተፈጠረውን ሁኔታ የዕለቱ ኮሚሽነር የሚያቀርቡትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ የፌዴሬሽኑ የዲሲፒሊን ኮሚቴ በቅርቡ የመጨረሻ ውሰኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።