ሪፖርት | መከላከያ ከሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

በመከላከያ የአፍሪካ ውድድር ተሳትፎ ምክንያት በ4ኛው ሳምንት ሳይካሄድ በተስተካካይነት ተይዞ የነበረው የደደቢት እና መከላከያ ጨዋታ መቐለ ላይ ተካሂዶ ጦሩ 3-0 አሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ባለፈው ሳምንት በሲዳማ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድናቸው ኤፍሬም ጌታቸውን በኩማ ደምሴ፣ አብርሃም ታምራትን በዓለምአንተ ካሳ፣ እንዳለ ከበደን በአክዌር ቻሞ ተከተው ወደ ሜዳ ሲገቡ መከላከያዎች በበኩላቸው የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በሰመረ አረጋዊ፣ አማኑኤል ተሾመ እና አዲሱ ተስፋዬ ምትክ ዳዊት ማሞ፣ ሙሉቀን ደሳለኝ እና ምንተስኖት ከበደ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

መከላከያዎች በሚያደርጓቸው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች የጀመረው ጨዋታው ግብ ያስተናገደው ገና እንደተጀመረ ነበር፤ ፍሬው ሰለሞን ዳዊት እስቲፋኖስ በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ በግሩም አጨራረስ አግብቶ እንግዳውን ቡድን መሪ ማድረግ ችሏል።

በመከላከያዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የቀጠለው ጨዋታው በመጀመርያው ደቂቃ እንግዶቹ በአንፃራዊነት የተሻሉ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል።  ፍሬው ሰለሞን ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ከግቡ አቅራቢያ ነፃ አቋቋም የነበረው ምንይሉ ወንድሙ ከማግኝቱ በፊት ክዌክ ኢንዶህ እንደምንም ያወጣው እና በተመሳሳይ መንገድ ፍሬው አሻምቷት ምንይሉ ያመከናት ኳስም ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉት ደደቢቶች የመከላከያን ተከላካይ መስመር አልፈው ንፁህ የግብ እድል ባይፈጥሩም ከሩቅ  ከተሞከሩ ኳሶች ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ክዌክ ኢንዶህ ከሩቅ አክርሮ መቷት ይድነቃቸው ኪዳኔ ያዳናት እና አሌክሳንደር ዓወት ከመዓዝን የተሻገረችለትን ኳስ ተጠቅሞ አክርሮ መቶ ለጥቂት የወጣችበት ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ብዙም ሳቢ እንቅስቃሴ ባልታየበት ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት እንግዶቹ መከላከያዎች በ35ኛው ደቂቃ በምንይሉ ወንድሙ ሁለተኛው ግብ አክለዋል። ምንይሉ ከዳዊት እስጢፋኖስ የተሻገረችለት ኳስ ተጠቅሞ ተጫዋቾች በማለፍ ነው ግሩም ግብ ያስቆጠረው።

ደካማ እንቅስቃሴ እና እጅግ የወረደ የፉክክር መንፈስ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጥቂት የግብ መከራዎች ያስተናገደ ሲሆን ግብ ለማስተናገድ ግን ብዙ ደቂቃ መጠበቅ አላስፈለገም። በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ምንይሉ ወንድሙ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ለመመለስ ባደረገው ጥረት በፈጠረው ስህተት ኳሷ ግብ መሆን ችላለች።

ሶስተኛው ግብ ከታየ በኋላ ጨዋታው በባሰ መልኩ እጅግ የወረደ ፉክክር የታየበት ሲሆን  ደደቢቶች ቀስ በቀስ ወደ ጥሩ የጨዋታ ቅኝት ቢገቡም ከራሳቸው ግብ ክልል አልፈው ተከታታይነት ያለው ቅብብል ማድረግ አልቻሉም። ሆኖም ጫና በፈጠሩባቸው ደቂቃዎች ጥቂት የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። የዓብስራ ተስፋዬ ከሩቅ መቷት ለጥቂት የወጣችው እና አክዌር ቻሞ ከመስመር መቷት ወደ ውጭ የወጣችው በደደቢቶች ከተሞከሩት ጥቂት ሙከራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በሁለተኛው አጋማሽ ረጃጅም ሩጫዎች  ከማድረግ ለመቆጠብ አስበው የገቡ ከሚመስሉት መከላከያዎችም ከኳስ ቁጥጥር ብልጫ ያለፈ ብዙ ንፁህ ዕድሎች ባይፈጥሩም ጥቂት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ከነዚህም ፍፁም ገ/ማርያም ከግቡ ቅርብ ቦታ ላይ አክርሮ መቷት ወደ ውጭ የወጣችው እና በጨዋታው ሁለት ግቦች ማስቆጠር የቻለው ምንይሉ ወንድሙ አክርሮ መቷት ዳዊት ወርቁ ተደርቦ ያወጣት ኳስ የተሻለ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ውጤቱ በዚ መጠናቀቁ ተከትሎ ደደቢቶች አስራ ሶስተኛ ሽንፈታቸውን ሲያስተናግዱ የዚህ ዓመት ሁለተኛ የሜዳ ውጪ ድላቸውን ያገኙት እንግዶቹ መከላከያዎች ከተከታታይ 7 ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መመለስ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *