ሱራፌል ዳኛቸው – ከእርሻ መንደር እስከ ፋሲል ከነማ 

በአንድ የእርሻ መንደር ውስጥ ነው ይህ ወጣት ባለ ተስጥኦ የተወለደው። የእግርኳስ ህይወቱ ጅማሬን በአዳማ በተስፋ ቡድን አድርጎ በመቀጠል በዋናው ቡድን ተጫውቶ አሁን በፋሲል ከነማ ይገኛል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ20 ዓመት በታች እና በዋናው ቡድን ለመጫወት ጥሪ ቢቀርብለትም በተለያዩ ምክንያቶች በበቂ ሁኔታ አለመጫወቱ ያስቆጨዋል። አምና በአዳማ ከተማ ጋር ከጉዳት ጋር እየታገለ ጥሩ የሚባል የውድድር ጊዜ በማሳለፍ የቻለ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ወደ ዐፄዎቹ በማቅናት ለሁለት ዓመት የሚያቆየውን ውል ፈርሟል። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነፃ የጨዋታ ሚና ተሰጥቶት ድንቅ አጀማመር ማድረግ ችሏል። እስካሁን በሊጉ አራት ጎሎች በስሙ ያስመዘገበው ወጣቱ የአጥቂ አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ስለ እግርኳስ ህይወቱ እና እድገቱ በቀጣይ ስለሚያስባቸው ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

ትውልድ እና እድገትህ የት ነው?

መርቲ ጀጁ እርሻ ልማት (የላይኛው አዋሽ አግሮ እንደስትሪ) ብዙዎች የሚያውቁት መርቲ የሚባል የቆርቆሮ ቲማቲም በሚመረትበት ማምረቻ የእርሻ ግቢ ውስጥ ሰራተኛ ከሆኑ እናት እና አባቴ የመጀመርያ ልጅ ሆኜ ተወለድኩ። ለእኔ ታናሽ የሆኑ ሁለት ወንድም እና እህት አሉኝ።

ከቤተሰቦችህ መካከል በተለይ ደግሞ ወላጅ አባትህ በእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወት ያለፉ ናቸው?

በክለብ ደረጃ ባይሆንም አባቴ ኳስ ይጫወት እንደነበረ አውቃለው እንጂ ይሄን ያህል ከቤተሰቤ መካከል ገፍቶ በመሄድ እግርኳስ ተጫውቶ ያለፈ የለም። ቅድም እንዳልኩሁ በመርቲ የእርሻ ልማት ግቢ ውስጥ መኖርያቸውን አድርገው ተቀጥረው ከሚሰሩት ስራ ውጭ እግርኳስን ተጫውተው አላለፉም። ባይሆን ከእኔ በኋላ ታናሽ ወንድሜ ኪሩቤል ዳኛቸው በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነው። በአዳማ ተስፋ ቡድን ነበር ከዛም ኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን ሄደ በዚያም አሰልጣኝ ፖፓዲች ወደ ዋናው ቡድን አሳድጎት የነበረ ቢሆንም ወዲያው ወጥቶ አሁን አዳማ ጎልደን ስቴት የሚባል ቡድን እየተጫወተ ይገኛል።

ወደ እግርኳስ ተጫዋችነት እንድታመራ የገፋፋህ ምክንያት ምንድነው?

የገፋፋኝን ምክንያት ለጊዜው ይህ ነው ባልልም ግቢ ውስጥ ኳስ እጫወት ነበር። በተፈጥሮ ያገኘሁት የሆነ የተሰጠኝ ነገር አለ ብዬ አስባለው። ይህችን ተሰጥኦ ለማሳደግ እጥር ነበር። ይገርምሀል በተለይ ሌሊት ሁሉ ሳይቀር እየተነሳው ብቻዬን ልምምድ እሰራ ነበር። አንድ ቀን እንዳጋጣሚ ሌሊት 11:00 ተነስቼ ብቻዬን ስጫወት ኃይሉ ካሱ የሚባል ሰው ያየኛል፤ ይመስለኛል እርሱ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ሲወጣ ነው ያየኝ። ኳስ ይዤ ብቻዬን ስጫወት በዛ በልጅነት እድሜ የማደርገው ነገር በጣም ገርሞት ደንግጦ ‘እንዴ ገና ሳይነጋ በዚህ ሰዓት ልምምድ የሚሰራው ማነው?’ ብሎ ሲያየኝ ልጅ ነኝ። እንዴት በዚህ ሰዓት ልምምድ ይሰራል ብሎ በመገረም ሰዎችን አወራቸው። ማነው ሲላቸው የዳኛቸው ልጅ ነው አሉት። አባቴን ለማግኘት እና ነግቶ እኔ ከልጆች ጋር አብሬ ስጫወት ለማየት የአዲስ አበባ ጉዞውን ሰርዞ እዛው ቀረ። በዚህ አጋጣሚ ከኃይሉ በፊት በጣም ህፃን ሆኜ ሱልጣን መሐመድ የሚባል ሰው ወተት እያጠጣኝ፤ ሽሮ እንዳልበላ ስጋ እያበላኝ፤ የመጫወቻ ትጥቅ እየገዛልኝ ኳስ ተጫዋች እንድሆን ገፋፍቶልኛል። ቅፅል ስም አውጥቶልኝ “ፋብሪጋስ” ይለኝ ነበር። ወደ ፊት አንተ ትልቅ ኳስ ተጫዋች መሆን አለብህ ይለኝ ነበር።

ምን የተለየ ነገር ብታደርግ ነው የዶ/ር ኃይሉ ካሱ የአዲስ አበባ ጉዞን ያስቀረህው ?

(እየሳቀ) በተፈጥሮ የተሰጠኝ ስጦታ አለ። አሁን በሜዳ ላይ የምትመከቱት ነገር ሁሉ በልጅነት እድሜዬ የማደርጋቸው ናቸው። ኳስ አክርሮ የመምታት በጫፉ እግሬ ኳስ ቆርጦ በጠበበ ቦታ መስጠት፣ ሰው ቀንሶ ማለፍ፣ ሜዳ ውስጥ ያለ ድካም መሮጥ… ይህ ሁሉ በልምምድ ልጅ ሆኜ እዛው የእርሻ ግቢ ውስጥ፤ ተስፋ የሚባል ቡድንም ውስጥም ስጫወትም ይሄን የተለየ ነገር አደርግ ነበር።

ወደ ዶ/ር ኃይሉ ካሱ ልመልስህ ከጉዞ አስቀርተህዋል። ታዲያ አንተን ከልጆች ጋር አብረህ ስትጫወት አይቶህ ምን አለ?

በማደርገው ነገር ተገርሟል። የተቋቋመ የተደራጀ ቡድን እዛ የለም። ያው የእርሻ ልማት ካምፕ ስለሆነ እንዴት እንደዚህ ያለ ልጅ ይወጣል በማለት በወቅቱ ደንግጦ ነበር። በቃ ይህ ልጅ ከዚህ በኋላ እዚህ መኖር የለበትም አዲስ አበባ ይዤው በመሄድ ለክለቦች ማሰየት አለብኝ ብሎ ቤተሰቦቼን አስፈቅዶ 2006 ላይ ወደ አዲስ አበባ ይዞኝ መጣ። እንዳጋጣሚም የአስረኛ ፈተና ውጤት አልመጣልኝም ነበር፤ አዲስ አበባ ፈቀደ ቲጋና ለተባለ አሰልጣኝ እንድጫወት ሰጠኝ።

ይህ ለእግርኳስ ህይወትህ መነሻ የሆነው ሰው አሁን ላይ እዚህ ደርሰህ ስታስበው ምን ይሰማሀል? ለእርሱስ የምታስተላልፈው መልዕክት አለህ ?

በመጀመርያ የፈጣሪ ፍቃድ ነው። በመቀጠል ለእርሱ ያለኝ ከአክብሮት እና ምስጋና በቃላት የሚገለፅ አይደለም። እርሱ ከእዛ ባያወጣኝ ኖሮ ወደ ፊት ምን ልሆን እንደምችል አላውቅም። ግን ከምልህ በላይ ለእርሱ የላቀ ምስጋና አለኝ። አሁንም አገኘዋለሁ እንገናኛለን።

አዲስ አበባ ከመጣህ በኋላ የነበረህ ቆይታ ምን ይመስላል?

አሰልጣኝ ፈቀደ (ቲጋና) የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚባል ብሔራዊ ሊግ ላይ የሚሳተፍ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ ያሰራ ነበር። እሱ ጋር ሄድኩ፤ ልጅ ነኝ ስጫወት አየኝ፤ ሂድ እጠራሀለው አለኝ። በሳምንቱ ብዙ ሳይቆይ ወድያውኑ ጠርቶኝ “ልጅ ነህ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታዳጊ ቡድን እወስድኃለው። ነገር ግን እስከዛ ድረስ ለዋናው ቡድን መጫወት ባትችልም እኔ አሰራሀለው ልምድ እያገኘህ ትቆያለህ” ብሎኝ እርሱ እያበላኝ እያጠጣኝ አበበ ቢቂላ ሜዳ ልምምድ እየሰራው ቆየሁ ። ዶ/ር ኃይሉ ካሳ ደግሞ ወደ ፒያሳ ሰባ ደረጃ አካባቢ ቤት ተከራይቶልኝ አንድ ዓመት ያህል መኖር ቻልኩ። ከቡድኑ ጋር አብሬ ባልጫወትም አብሬ ከሰራሁ በኋላ 2007 አዳማ ከተማ ተስፋ ቡድን መግባት ቻልኩ።

በአዳማ ከተማ የተስፋ ቡድን ቆይታህ እንዴት ነበር? ወደ ዋናው ቡድን መቼ አድገህ መጫወት ጀመርክ?

በ2007 በአዳማ ተስፋ ቡድን እጅግ በጣም ደስ የሚል የማይረሳ ቆይታ ነበርኝ። በወቅቱ አብረውኝ ይጫወቱ የነበሩ እና አሁን በፕሪምየር ሊጉ እየተጫወቱ ያሉ በወቅቱ ጎልተው የወጡ እንደ ከነዓን ማርክነህ እና ቡልቻ ሹራ አብረውኝ ተጫውተዋል። በወቅቱም የውድድሩ የዋንጫ አሸናፊ ሆነን አጠናቀቅን። 2008 ላይ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን እንድናድግ ተደር.ጓል።

በአዳማ ከተማ የሦስት ዓመት ቆይታህ ምን ይመስላል ?

አዳማ የነበረኝ ቆይታ በጣም አሪፍ ነው። የመጀመርያው ዓመት ብዙም የመሰለፍ እድል አላገኘንበትም፤ ያው ከቡድኑ ጋር አብረን እንሰራለን ገና ልጆች ስለነበርንም በአንድ ጊዜ በእኛ ላይ እምነት ጥሎ ለማጫወት ትንሽ ይከብድ ነበር። 2008 ወጣ ገባ እያልን በተስፋው በዋናው ቡድን ቆይቼ በ2009 ወደ ውድድሩ መጠናቀቂያ ላይ የመሰለፍ ዕድል አግኝቻለው። ያም ቢሆን ባገኘነው አጋጣሚ ጥሩ ነገር ለመስራት እንጥር ነበር ። ከ2010 ጀምሮ የመጫወት ዕድል እየሰጠኝ መጥቼ ምንም እንኳ በዋንጫ ያልታገዘ ቆይታ ቢኖረኝም ከሞላ ጎደል በአዳማ ከተማ ለዛሬው የእግርኳስ ህይወቴ መሰረት የጣልኩበት ብዙ ነገር የተማርኩበት ቤት ነው። በውድድር ዓመቱም አምስት ጎል አስቆጥሬያለው። በአጠቃላይ በአዳማ የነበረኝ ቆይታ በተለይ በአሰልጣኝ አሸናፊ በነፃነት ያለኝን ነገር አውጥቼ እንድጫወት ዕድል ተሰጥቶኛል። በደጋፊውም ጥሩ ተወዳጅነት አትርፌበታለው።

በዚህ ወቅት 2008 ላይ በአሰልጣኝ ግርማ በሚመራው ከኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎልህ ተቀንሰሀል። ምን ነበር ምክንያቱ?

የብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጥሪዬ ነው። ከቡድኑ ጋር ተቀላቅዬ እየሰራው ሳለ ከቢንያም በላይ ጋር በልምምድ ላይ ተጋጨን። የአሁኑ የአዳማ ዋና አሰልጣኝ የሆነው በዛን ወቅት ም/ አሰልጣኝ የነበረው ሲሳይ አብርሃ እኔን ብርቻ ጠርቶ በዲሲፕሊን ምክንያት ተቀንሰሀል አለኝ። መጫወት እየቻልኩ ይህ አለመሆኑ አበሳጭቶኝ ምንም አላልኩም፤ ጥዬ ሄድኩ። በጣም የሚገርምህ ከዛ በኋላ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ ክለቤ አዳማ የጥሪው ወረቀቱ ደርሷቸው ደብቀውኝ አንለቅም ብለው ወደ ወልድያ ይዘውኝ በመሄዳቸው ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን ሜዳ ውስጥ ብኖርም ተናድጄ ምንም ሳልሰራ የወጣሁባትን ቀን አልረሳውም። ምክንያቱም ለብሔራዊ ቡድን መጫወት የሁሉም ተጫዋች ህልም በመሆኑ እንዴት እንደምትጓጓ አስበው። በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የኦሊምፒክ ቡድን ተጠርቼ የፋሲል ጨዋታ በመኖሩ ምክንያት ቀርቻለው። ሳስበው አጋጣሚዎቹ ይገርሙኛል።

በዚሁ የብሔራዊ ቡድን ዙርያ አንድ ጥያቄ ላንሳልህ። አሁን ካለህ ወቅታዊ አቋም የተነሳ በቀጣይ በብሔራዊ ቡድን የመጠራት አጋጣሚ ቢፈጠር ምን ለማድረግ ታስባለህ ?

ወደ አንተ ለቃለ መጠይቅ ከመምጣቴ በፊት ከከነዓን ጋር እያወራሁ ነበር። በአሁን ሰዓት አንድ እና አንድ የማስበው ብሔራዊ ቡድን መጫወት ነው። በፕሪምየር ሊጉ ላይ መጥፎ የማይባል ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው። በብሔራዊ ቡድን ተጠርቼም መጫወት እፈልጋለው። ታዲያ መቀመጥ አይደለም ወይም ደርሶ መመለስ አይደለም የምፈልገው። በደንብ መጫወት ነው የምፈልገው። ያለኝን ነገር አውጥቼ ያለውን ክፍተት ከጓደኞቼ ጋር በመድፈን ጥሩ ነገር ለሀገሬ ለማምጣት እፈልጋለው።

ከፋሲል ከነማ ጋር ያለህ የግማሽ ዓመት ቆይታህ ስኬታማ ነው። በክለቡ ደጋፊዎችም ተወዳጅ ተጫዋች ሆነሀል። እዚህ ቦታ ላይ ከእኔ ጋር ተቀምጠህ እንኳ መጥተው አድናቆታቸውን የሚገልፁ ደጋፊዎች እየተመለከትኩ ነው። እንዴት አገኘኸው የፋሲል ቆይታህን ?

በመጀመርያ ደረጃ ፈጣሪን አመሰግናለሁ። ፋሲል ከመጣሁ ገና አምስት ወር ያህል አካባቢ ነው። ከዝግጅት ጀምሮ ጥቂት ሰዎች ካልሆኑ በቀር ብዙም የሚያውቁኝ አልነበሩም። ከዛ በኋላ ከዕለት ወደ ዕለት በጣም ጥሩ ነገር ነው ያለው። ጭራሽ ጎል የማግባት አቅሜ እየጨመረ ሲመጣ ያለው ነገር እንደምታየው ሆኗል። በጣም ፈልጌ ወድጄ ፈቅጄ ነው ፋሲል የመጣሁት። በዛ ላይ አብሬው መስራት የምፈልገው ሰው ጋር ነው የመጣሁት። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ኳስ መስርቶ የሚጫወት ቡድን መስራት ይችላል። ኳስ የሚጫወት ቡድን ውስጥ ደግሞ እንደ እኔ አይነቱ ጉልበት የማይጠይቅ ኳስን ብቻ የሚጫወት ተጫዋች ያስፈልጋል። ነፃነት ሰጥቶኝ በማጫወቱ ደግሞ የበለጠ አቅሜን አውጥቼ እንድጠቀም ረድቶኛል።

ኳስን የሚጫወት ቡድን ውስጥ ነፃ ሚና ተሰቶህ መጫወት እንደምትፈልግ እየገለፅክልኝ ነው። በዚህ ረገድ በሀገራችን እግርኳስ ለተጫዋቾች የሚሰጠው ነፃነት ውስን ነው። ብዙዎቹም ከአቅም በላይ በሚሰጡ ትዕዛዞች ተጫዋቾችን ጫና ውስጥ ይከታሉ። ለምሳሌ በቅርቡ የደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾች ከአሰልጣኝ ዘላለም ስንብት በኋላ በነፃነት እየተጫወቱ ተከታታይ ድል አስመዝገበዋል። በዚህ መልኩ ይህ ለተጫዋቾች የሚሰጥ ነፃ ሚና አስመልክቶ ምን ትላለህ ?

ብዙ ጊዜ የእኛ ሀገር አጨዋወት የተገደበ ነው። ይህ ነፃ ሚና የሚባለው ነገር እኛ ሀገር ከባድ ነው። ተከላካይ አብዝተው ነው የሚጫወቱት። ቀድመህ ታገባለህ፤ ከዛ ትዘጋለህ አለቀ። ተመልካቹ ሜዳ ገብቶ ተደስቶ የማይወጣበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ይህ መስተካከል አለበት። አሁን ያለሁበት ቡድን እንደዚህ አይነት ነገር አላየሁም። ብዙ ክለብ ተጫውቼ ባላውቅም እዚህ የማየው በሜዳችንም ከሜዳ ውጭ በጣም ነው የምናጠቃው። ብዙ የጎል እድሎችን እንፈጥራለን። ስንሸነፍ እንኳ ለምሳሌ ከሲዳማ ጋር የነበረን ጨዋታ ብዙ ኳሶችን ስተን ነው። ኳስን ይዘን ነው የምንጫወተው። ይህ በሁሉም ክለቦች መለመድ አለበት። በሌለን ነገር ከምንሰራ ያለንን አቅም አውጥተን ብንጠቀም መልካም ነው የምለው።

ከተክለ ሰውነትህ አንፃር ከሳጥን ውጭ ጠንካራ ኳሶችን በመመታት ጎል እያስቆጠርክ ትገኛለህ። ይህ ልምድ ከየት መጣ ?

ቅድም እንደነገርኩሁ የመርቲ እርሻ ልማት ግቢ አካባቢ ወንዝ የሚሄድበት አሸዋ አለ። ለገፈርዳ ይባላል። ወንዙ ውስጡ አሸዋ ነው። ወንድማማቾቹ እንዳለ መለዮ እና በዛብህ መለዮ (እንዳለ ኳስ ያቆመ መሰለኝ፤ በዛብህ አሁን በፋሲል ከነማ አብሮኝ እየተጫወተ ነው።) እነርሱ ኳሱን አሸዋ ውስጥ ከተው እግራቸው እንዲጠነክር ልምምድ ሲሰሩ እመለከት ነበር። ይገርምሀል ሌሊት ተነስተው ቶርሽን ጫማ አድርገው አሸዋው ላይ ይሮጡ ነበር። እነዚህ ወንድማማቾች አይተሀቸው ከሆነ በጣም ጠንካራ ጡንቻ ነው ያላቸው። እነርሱ አድገው ወደ ክለብ ሲሄዱ እኔም እንደ እነርሱ ሌሊት እየተነሳው አሸዋው ላይ መሮጥ ጀመርኩ ከእዛ ወጥቼ ሜዳው ላይ ስጫወት በጣም ነው የሚቀለኝ። ምክንያቱም አሸዋ ውስጥ በጣም ይከብዳል። ከዛ ልምምድ የመጣ ነው የጡንቻዎቼ መጠንከር የሚመስለኝ። አሸዋ ውስጥ የተለያዩ ተናዳፊ እንስሳትን ሁሉ ተቋቁመን ነበር የምንሰራው። ውሀ በፕላስቲክ አሸዋ ውስጥ ቀብረን እናቆይና ልምምድ ሰርተን እስክንጨርስ ውሃው ይቀዘቅዛል። እርሱን ጠጥተን ነበር ወደ ቤት የምንገባው።

ሱራፌል በየትኛው አጨዋወት ቢጫወት ይመርጣል። በመስመር አጥቂ፣ ከአጥቂ ጀርባ ወይስ የአማካይ ስፍራ ?

አዳማ እያለሁ መስመር አጥቂ ነበርኩ። ከቀኝ መስመር እየተነሳው ወደ ግራም መስመር እየቀያየርኩ ነው የምጫወተው። አንዳንዴ አማካይ አድርጎ አሰልጣኝ አሸናፊ ያጫውተኝ ነበር። አሁን ፋሲል ነፃ ሚና ነው የተሰጠኝ፤ ከአጥቂ ጀርባ መጫወትን። ይህ ደግሞ በጣም ጠቅሞኛል። አንደኛ ጎል አስቆጥራለው ሁለተኛ የሚመለሱ ኳሶችን ከርቀት የመምታት አጋጣሚን አገኛለሁ። ሦስተኛ ሳልቆም ሜዳውን ሁሉ ሸፍኜ እንድጫወት ስለሚያደርገኝ በመስመር ከመጫወት ይልቅ ከአጥቂ ጀርባ በነፃ ሚና ተሰቶኝ መጫወትን እመርጣለው።

በቀጣይ ከፋሲል ከነማ ጋር ምን ታስባለህ?

በቀጥተኛ እና በአጭሩ የማስበው ዋንጫ ማንሳት ነው። ስመጣም አልሜ እና አስቤ የመጣሁት በጣም ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች እኔ ከመምጣቴ በፊት ከመፈረማቸው አንፃር እንዲሁም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እዚህ መኖር እንዲሁም በጣም ብዙ እና ምርጥ ደጋፊዎች ስላሉት ከእነርሱ ጋር ጠንክሬ ሰርቼ ዋንጫ ለማንሳት ነው የመጣሁት። ስፈርም ለኋላፊዎቹ የተናገርኩት ዋንጫ ለማንሳት እንደሆነ ነው።

በግልህ ከኢትዮጵያ ውስጥ የማን ተጫዋች አድናቂ ነህ?

ከልጅነቴ ጀምሮ አሁንም ጭምር የዳዊት እስጢፋኖስ አድናቂ ነኝ። የእርሱ አጨዋወት በጣም ያስደስተኛል።

አንተ ያገኘህውን እድል ሌሎች ታዳጊዎች እንዲያገኙ ምን መደረግ አለበት ትላለህ ?

በተለይ እኔ በነበርኩበት ቦታ ብዙ አቅም ያላቸው ታዳጊዎች አሉ። ከሚመለከታቸው የእግርኳስ ባለሙያዎች በላይ እንደ እኔ አይነቱ በእዛ ቦታ በችግር ያለፉ ተጫዋቾች ታዳጊዎቹ ወጥተው እንዲጫወት የተቻለንን ድጋፍ ማድረግ አለብን ብዬ አስባለሁ።

በመጨረሻም አሁን ያለህበት ደረጃ መልካም የሚባል ቢሆንም ገና ብዙ ይቀረሀል እና በቀጣይ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ምን ታስባለህ ?

ትልቁ ቁም ነገር እርሱ ነው። ከዚህ በተሻለ ለመድረስ በግሌ እሰራለው። የምሰራባቸው ማቴሪያል አሉኝ። ለምሳሌ እንደ ፓራሹት ጀርባዬ ላይ አስሬ የምሮጥበት አለኝ። ከአሁኑ የተሻለ ነገር ለማድግ እጥራለው። ሰው ሞራል ሲሰጥህ ጨርሻለው ብለህ የምትዘናጋበት ሳይሆን የበለጠ የምትነሳሳበት መሆን አለበት። ብዙ ጊዜ ሰው ሲያበራታታህ፣ ሲያጨበጭብልህ የጨረስክ ይመስልሀል። እኔ ግን ገና እየጀመርኩ እንደሆነ እና ከዚህ የተሻለ በጣም ብዙ ነገር መስራት እንዳለብኝ ነው የማስበው።


© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *