አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በወቅታዊ የብሔራዊ ቡድን ጉዳዮች ዙርያ የሰጡት መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በትላንትናው ዕለት በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው ስለ ወቅታዊ የብሔራዊ ቡድን እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ማብራርያ ሰጥተዋል።

ስለ ጋዜጣዊ መግለጫው

በቅድሚያ እንዲህ ዓይነት መድረክ በመዘጋጀቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬቱን ላመሰግን እወዳለሁ። በቀጣይም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዲህ በተቀናጀ መልኩ ከሚድያ ጋር መገናኘት እንችላለን ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ሚድያዎች በተናጠል ስለብሔራዊ ቡድኑ መረጃ ስንለዋወጥ የቆየን ቢሆንም የሚድያ ፕላን የሚኖረን ከሆነ እና ባህሉም እየተለመደ ሲመጣ ወደ ጥሩ መንገድ እንመጣለን ብዬ አስባለሁ።

ስለ ውድድሮች

በኤርትራ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የወጣቶች ውድድርን (የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ) በተመለከተ ደብዳቤ የደረሰን ትላንት ነው። ከኤፕሪል 11-20 ይደረጋል ተብለናል። ጊዜው ሲቃረብ አሰልጣኝ መድበን ሥራ እንጀምራለን። አሁን ላይ የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችኖ ተዟዙረን እየተመለከትን እንገኛለን። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን እንዲኖረን ይህ ቡድን መጠናከር ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር ነው እየተንቀሳቀስን የምንገኘው።

በኦሊምፒክ ማጣርያ አንደኛ ዙር ከማሊ ጋር የምናደርገው ጨዋታ የመርሐ ግብር ማሻሻያ ተደርጎበት ከካፍ ተልኮልናል። ማርች 23 አዲስ አበባ ላይ ሲደረግ ማርች 26 ባማኮ የመልሱ ይደረጋል። የጊዜውን መጣበብ ከግምት በማስገባት ለሁለታችም ሀገራት አመቺ በሚሆን መልኩ ቀኑን ለማስተካከል ጥረት እያደረግን እንገኛለን።

የወዳጅነት ጨዋታዎች

ዋናው ብሔራዊ ቡድንን በተመለከተ የፊፋ የወዳጅነት ጨዋታዎች ሳምንትን ሳትጠቀምበት ቆይታለች። አሁን ግን ከፌዴሬሽኑ ጋር በመተባበር ጨዋታ ለማግኘት እየሰራን እንገኛለን። በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከሴሳሊዮን ጋር የምናደርገው ጨዋታ በሴራሊዮን እገዳ ምክንያት የማይደረግ በመሆኑ በሱ ምትክ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ አስበናል።

የኦሊምፒክ ቡድናችን ማርች 1 የሚሰበሰብ ይሆናል። እስከ ማሊው ጨዋታ ድረስም ከሲሸልስ እና ሱዳን ጋር ጨዋታ ለማድረግ አቅደናል። ቡድኖቹ አዲስ አበባ ላይ ካምፕ በማድረግ ዝግጅት ስለሚያደርጉ አጋጣሚውን ለመጠቀም በዝግጅት ላይ ነው ያለነው። ሱዳን የዋናው እና ከ23 ዓመት በታች ቡድኖቿ የሚመጡ በመሆኑ ሁለቱንም ለመግጠም ነው የተዘጋጀነው።

የተጫዋቾች ምርጫ

ለኦሊምፒክ ቡድን 33 ከፕሪምየር ሊግ እና ሌሎች የውስጥ ሊጎች ተጫዋቾችን ለይተናል። በየቦታው ሦስት ተጫዋቾችን ይዘናል። ከሱዳን እና ሲሸልስ ጋር በሚደረጉት ሦስት የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ በመመርኮዝም ወደ 22 የምንቀንስ ይሆናል።

ተጫዋቾችን ለመምረጥ በተለያዩ ቦታዎች ከረዳቶቼ ጋር በመከፋፈል ስንመለከት ቆይተናል። ሁሉንም ባናዳርስም ልናይ የሚገባንን አይተናል።

ስታፍ ማዋቀር

ብሔራዊ ቡድኑን ጠንካራ ለማድረግ ዘመናዊ የሆነ ስታፍ ለማሟላት እየሰራን እንገኛለን። የህዝብ ግንኙነት አግኝተናል። የሥነ-ምግብ ባለሙያ እና ሁለት የሥነ-አዕምሮ ባለሙያዎች አግኝተናል። የቪድዮ ትንተና ከዚህ ቀደምም በበጎ ፍቃደኝነት ሲሰሩልን የነበሩ ባለሙያዎች አሉ። አሁን አግባብ ባለው መንገድ ክፍያ ተፈፅሞላቸው የሚሰሩ ይሆናል። አቅም ያለው የአካል ብቃት ባለሙያ ማግኘት ከባድ ነው። ከሌሎች ሀገራት ለማምጣት ዋጋቸው ውድ በመሆኑ በስፖንሰር መልክ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው። ሙያተኛ እስክናገኝ ድረስ ከጀርመን በሚመጣ የተጫዋቾችን ብቃት በሚለካ ማሽን እየታገዝን እንቆያለን።

ስለ ትጥቅ

የትጥቅ ጥራት እና አቅርቦት ሊኖር እንደሚገባ ፌዴሬሽኑን ሲጎተጉቱ ከነበሩ ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ። ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ በሚልዮን የሚቆጠሩ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎችም አሉ። በምንለብሰው መለያ ሊኮሩ ይገባል። ከዚህ ቀደም የሰራሁባት የመን እንኳን በጦርነት እየታመሰች ጥራት ያለው መለያ ነበራት። ይህ መንፈሳዊ ቅናት ሲያሳድርብኝ ቆይቷል።

በኦሊምፒክ ቡድኑ ላይ የአቅርቦት ችግር በመኖሩ ሌላ ብራንድ ተጠቅመን ነበር። ከዚህ ቀደምም ውጪ ሆኜ ብሔራዊ ቡድኑ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ማልያዎች ልምምድ ሲሰራ ተመልክቻለሁ። ጋቶች በሁለት አጋጣሚዎች ለጨዋታ የተመደበለት ማልያ ስለጠበበው ብብቱ አካባቢ ተጨማሪ ጨርቅ ገብቶለት እንዲሰፋ ተደርጎ ነበር። ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ምቾት ተሰምቷቸው ሊጫወቱ ይገባል።

ስፖርት ዲፕሎማሲ እና በውጪ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ስለመጠቀም

ሌሎች ሀገራት ለእግርኳሳቸው እድገት የሚሰሩትን ስራ እኛም መስራት ይኖርብናል። ውጪ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ግንኙነት እየፈጠርን እንገኛለን። ሁሉንም አምጥተን ሙከራ በማድረግ ብክነት ከመፍጠር የተወሰኑ ባለሙያዎችን ቦታው በመውሰድ ህጋዊነታቸውን እና ብቃታቸውን በማረጋገጥ ለመመልመል አቅደናል።

ወደ ሌሎች ሀገራት እየተጓዝን ካምፕ በማድረግ የወዳጅነት ጨዋታ የማድረግ እቅድ አለን። ሌሎቹ ሀገራት ያደርጋሉ፤ እኛስ ለምንድነው ወጣ የማንለው? ወጣ ብለን ልምምድ ስናደርግ የተጫዋቾች የትኩረት መጠን ከፍ ይላል፤ ዓለምአቀፍ ልምድ ያገኛሉ። ስለዚህ ከአረብ ሀገራት ጋር ባለኝ ግንኙነት ተጠቅሜ ካምፕ የማድረግ እና የሙያ ድጋፍ ማግኘት የምንችልበትን መንገድ እየፈለግን እንገኛለን። ከካታር ጋርም በዚህ ጉዳይ ላይ እየተነጋገርን ነው። እድገት እስከምናስመዘግብ ድረስ ካደጉ ሀገራት ተጠግተን መስራት ይኖርብናል። በመንግስት ደረጃ እንኳን የውጪ ምንዛሪ ችግርን ለመቅረፍ ወደ አረብ ሀገራት ነው ያመራነው።

የቴክኒክ ድጋፍ ለማግኘት ከጃፓን ጋር እየተነጋገርን ነው። በቅርቡ ቢሮ እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ። አንድ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰኞ ወደ ቢሮ ሲገባ ጠረጴዛ ላይ በሳምንቱ መጨረሻ የተደረጉ ጨዋታዎችን ቅጂ ተቀምጦ ሊያገኝ ይገባል። እኛ ጋር ያለው ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ ሁሉንም ጨዋታዎች ማግኘት ካለመቻሉ በተጨማሪ የሚቀረፁት ጨዋታዎችም በኋላቀር ካሜራዎች ነው። በዚህ ረገድ ከጃፓን እርዳታ ለማግኘት እንፈልጋለን።

ውይይቶች

ብሔራዊ ቡድን የሚገነባው ከክለቦች በሚመረጡ ተጫዋቾች ነው። ከሠውነት ቢሻው ጋር ተነጋግረን የሁሉንም የፕሪምየር ሊግ ክለብ አሰልጣኞችን ከነምክትሎቻቸው በመጥራት በብሔራዊ ቡድን ድክመቶች እና በክለቦች በኩል ስለሚጠበቀው ነገር እንወያያለን። ውይይቱድ ያሰብነው በዚረ ሳምንት ቢሆንም የአንደኛው ዙር ባለመጠናቀቁ ምክንያት ሁሉም ጨዋታዎች ከተጠናቀቁ በኋላ የካቲት 23 እናደርጋለን። ይህ በየደረጃው ያሉ ብሔራዊ ቡድኖቻችንን ለማጠናከር ግብዓት ይሆነናል ብዬ አምናለሁ።

ከውይይቱ በተጨማሪ አሰልጣኞቻችን የሙያ ማሻሻያ ኮርሶች የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር ይኖርብናል። በአውሮፓ በየ3 ወራት የሙያ ማሻሻያ ኮርስ አለ። ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ደግሞ የኤ ላይሰንስ የወሰደ አሰልጣኝ ሦስት ዓመት ሙሉ ምንም ኮርስ እነሰዳላገኘ ሲያጫውተኝ ነበር። ሦስት ዓመት በጣም ሰፊ ጊዜ ነው። በእግርኳስ ሁኔታዎች ቶሎ ቶሎ ይቀያየራሉ። አንድ ጊዜ እንደውም ‘እግርኳስ በበጊዜው ሳይሆን በየ 90 ደቂቃው ይቀያየራል’ ሲሉ የቀድሞ የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዤራር ሁዬ መናገራቸውን አስታውሳለሁ። ስለዚህ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ የአቅም ግንባታ ስራ ከፊፋ እና ካፍ በመተባበረረ እንዲሰጥ ጥረት እያደረግን እንገኛለን።

ሌላው የነ ሴኔጋል፣ ግብፅ፣ ካታር፣ ስፔን እና የመሳሰሉ ሀገራትን ልምድ በመቅሰም የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን መጠቀም ላይ ስራዎች እንሰራለን። የብሔራዊ ቡድን ማልያ የለበሱ ተጫዋቾች ከሁሉም በላይ ስሜቱ ይገባቸዋል። ስለ ድክመቱ እና ሊስተካከል ስለሚገባው ነገር እነሱን ማዋየት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ከውይይት በተጨማሪ ለነሱ ክብር የምንሰጥበት አንዱ አጋጣሚ ይህ ነው የሚሆነው። ስለዚህ የካቲት 24 በዚህ ጉዳይ ላይ ቀጠሮ ይዘናል።

ከቀድሞ ተጫዋቾች ጋር ከውይይት ባሻገር ወደ ሙያው ቀረብ የሚሉበትን መንገድ ለመፍጠር ስልጠና ለማዘጋጀት ከቴክኒክ ዲፓርትመንቱ ጋር እየሠራን እንገኛለን። ይህ ያቀረሙ ብቻ ሳይሆን በመጫወት ላይ ያሉ እና ሜዳ ላይ ጥሩ የመምራት ችሎታ ያላቸውንም ያካትታል። መድረኩ ስላልመቻቸ እንጂ ብዙዎቹ የመማር ፍላጎት አላቸው። ዮርዳኖስ ከድሬዳዋ ደውሎልኝ ነበር ሌሎችም አሉ። እነዚህን ወደ ሙያው ማምጣት ያስፈልጋል።

ስልጠናው የሚያተኩረው በጨዋታ ትንተና (Game analysis) እና ምልመላ (Scouting) ላይ ነው። በዚህም ተጠቃሚ ይሆናሉ። የምልመላ ችሎታ ካላቸው ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድን መጠቆም ይችላሉ። በትንታኔ ደግሞ በየ ጣቢያዎቹ በሚተላለፉ ጨዋታዎች ላይ እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል።

ከአሰልጣኙ መግለጫ በኋላ ከጋዜጠኞች የተሰነዘሩ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን መግለጫቸው የቴክኒክ ዳይሬክተርነት ሚና ያለው ስለመምሰሉ፣ ስለ ማልያ ዲዛይን፣ የትውልደ ኢትጵያውያን የዜግነት ጉዳዮች፣ የወዳጅነት ጨዋታዎች በoff-season ወቅት ስለመሆናቸው፣ የኦሊምፒክ ቡድን የእድሜ ጉዳይ፣ ስለ ግብ ጠባቂ አሰልጣኝ፣ የአካል ብቃች ደረጃ እና ዲሲፕሊን ማብራሪያ ተሰጥቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *