ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አዳማ ከተማ

ከ17ኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር መካከል ነገ በሚደረገው ብቸኛ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታዎቻቸው ማሽነፍ ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ነገ 11፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይገናኛሉ። የዓመቱ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪው ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ 12 ከፍ ብሏል። ባለፉት ሦስት የሊግ ጨዋታዎቻቸው ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት ፈረሰኞቹ ከ13ኛው ሳምንት በኋላም ድል አላስመዘገቡም። በመሆኑም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት የነገውን ጨምሮ በቀጣይ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦችን ማሳካት ይጠበቅባቸዋል። አዲስ የፊት መስመር ጥምረት እየተጠቀሙ የሚገኙት ጊዮርጊሶች በነገው ጨዋታ በዋነኝነት ከመስመር ተመላላሾቻቸው በሚነሱ ኳሶች ጥቃቶችን ለመክፈት እንደሚጥሩ ሲጠበቅ በአመዛኙ ከወገብ በላይ ባለው የቡድኑ ክፍል ላይ ተደጋጋሚ ለውጦች ከመደረጋቸው አንፃር በቶሎ ወደ ግብ ማስቆጠሩ በመመለስ በራስ የመተማመን መንፈሱን ማጎልበት ይጠበቅበታል። ቡድኑ በቅርቡ የቀዶ ጥገና ህክምና ያደረገው ሳላዲን ሰዒድ ፣ ሳላዲን በርጌቾ ፣ መሀሪ መና እና ጌታነህ ከበደን በጉዳት ምክንያት የማያሰልፍ ይሆናል።

እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ግቦችን ማስቆጠር እየከበዳቸው ያሉት አዳማዎች የመጨረሻዎቹን አምስት ጨዋታዎቻቸውን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ከሦስቱ ተጋጣሚዎቻቸው ጋር 0-0 በሆነ ውጤት ነበር የተለያዩት። በአንፃሩ በስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዳቸው ደግሞ እንደጥንካሬ የሚወሰድ ነው። ከበረከት እና ከነዓን አለመኖር ጋር ተዳምሮ ሁለት የፊት አጥቂ ጥምረትን መጠቀም የጀመረው አዳማ በነገውም ጨዋታ ተመሳሳይ አካሄድ እንደሚኖረው ሲጠበቅ የመከላከል ባህሪ ባላቸው የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቹ ለኋላ ክፍሉ ጥሩ ሽፋን በመስጠት ወደ መልሶ ማጥቃት በሚያደላ አቀራረብ ወደ ጨዋታው እንደሚገባ ይገመታል። አዳማ ከተማ ቡልቻ ሹራ እና አንዳርጋቸው ይላቅን በጉዳት ሲያጣ ከነዓን ማርክነህ እና በረከት ደስታ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ውስጥ በመካተታቸው ሮበርት ኦዶንካራ ደግሞ ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን በመመረጡ ምክንያት የማይጠቀምባቸው ሲሆን ብሩክ ቃልቦሬ ከጉዳት ሱለይማን ሰሚድ ደግሞ ከቅጣት ይመለሱለታል።

የቀድሞው የፌስቡክ ገፃችን በኛ ቁጥጥር ስር የማይገኝ በመሆኑ አዲሱ ገፃችንን ሊንኩን በመከተል ላይ ያድርጉ – facebook.com/SoccerEthiopia

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 35 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 17 ድል በማስመዝገብ የበላይ ሲሆን አዳማ ከተማ 7 አሸንፏል፡፡ 11 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2005 የውድድር ዓመት 7-0 ያሸነፈበትን ጨዋታ ጨምሮ እስካሁን 44 ግቦች ሲያስቆጥር አዳማ ከተማ ደግሞ 24 ጎሎች አሉት፡፡

– ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ ጋር በተገናኘባቸው 17 የሜዳው ላይ ጨዋታዎች አንዴም ሽንፈት አልገጠመውም። በዚህም 13 ጊዜ አሸንፎ 4 ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ አዳማ ከተማ ሰባት ግቦችን ብቻ ሲያስቆጥር በአንፃሩ 33 ግቦችን አስተናግዷል።

– አዳማ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን አዲስ አበባ ላይ በገጠመባቸው የመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠመውም። የመጨረሻው ሽንፈቱ የተመዘገበው 2007 ላይ ነበር።

– የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታዎቹን በሽንፈት የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስምንት ጨዋታዎች ግማሹን ሲያሸንፍ ሦስት የአቻ እና አንድ የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግቧል።

– አዳማ ከተማ እስካሁን ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች መከላከያን በገጠመበት ጨዋታ ብቻ ነው ድል የቀናው። ከዛ ውጪ ሁለቴ ሲሸነፍ አምስቴ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። ከአምስቱ ጨዋታዎች አራቱን አቻ የተለያየው በመጨረሻ ባደረጋቸው የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ነበር።

ዳኛ

– እስካሁን በዳኘባቸው ስምንት ጨዋታዎች 40 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን እና አንድ ቀጥታ ቀይ ካርድ የመዘዘው ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ – ምንተስኖት አዳና – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

አብዱልከሪም መሀመድ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ – ኄኖክ አዱኛ

ሃምፍሬ ሚዬኖን

ሪቻርድ አርተር – አቤል ያለው

አዳማ ከተማ (4-4-2)

ጃኮ ፔንዜ

ሱራፌል ዳንኤል – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

ኤፍሬም ዘካርያስ – አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ ዐመለ ሚልኪያስ

ሙሉቀን ታሪኩ – ዳዋ ሆቴሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply