አአ U-17 | ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ 5ኛ ድሉን ሲያስመዘግብ መድን እና አካዳሚም አሸንፈዋል

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር 5ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። በዛሬው ዕለት አራት ጨዋታዎች ተካሂደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢ/ወ/ስ አካዳሚ እና ኢትዮጵያ መድን ድል ማስመዝገብም ችለዋል።

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ የምድቡ አንደኛ ቅዱስ ጊዮርጊስን በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኛ ደረጃ ከሚከተለው ኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ 03:00 ላይ ባገናኘው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ አምስተኛ ተከታታይ ድል ይዞ ወጥቷል።

እንደተጠበቀው ጠንካራ ፉክክር ባስተናገደው በዚህ ጨዋታ ከማዕዘን ምት የተሻገረው ኳስ ተደርቦ ሲመለስ ሐብታሙ ደሴ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀዳሚ መሆን ችሏል። የሜዳውን ስፋት ከመጠቀም ይልቅ በመሐል ሜዳ ላይ ተገድቦ የቀጠለው ጨዋታ በኢትዮ ኤሌትሪክ በኩል የመስመር አጥቂው ይበልጣል ቻሌ በግሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ነበር።

ከእረፍት መልስ ኢትዮ ኤሌትሪኮች በተሻለ በመንቀሳቀስ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም መጨረሻ ደቂቃ ላይ ፀጋዬ መለሰ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር የፈረሰኞቹን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ፀጋዬ በውድድሩ ያስቆጠረውን ጎል ወደ አምስት አድርሷል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ አምስተኛ ጨዋታውን በማሸነፍ መሪነቱን ማስፋት ችሏል።

* ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተጫዋች እና ከኢትዮ ኤሌትሪክ በኩል ከ18 ተጫዋቾች ውጭ በሆነ ተጫዋች መካከል የተፈጠረው ፀብ ወደ ሌሎቹ ተዛምቶ ለመቆጣጠር በሚያስቸግር መልኩ ከፍተኛ ግርግር የተፈጠረ ሲሆን እንዳጋጣሚ ሆኖ በአካዳሚው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለስብሰባ የመጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የተፈጠረውን ችግሩን ሊቆጣጠሩት ችለዋል። ሆኖም የሁለቱ ቡድኖች አመራሮች ውድድሩ የታዳጊዎች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዲህ ያለ ከእግርኳስ መርህ ውጭ የሆነ ተግባር ከዚህ በኋላ ተጫዋቾቹ እንዳይፈፅሙ በሚገባ ሊያስተምሯቸው፣ ሊቆጣጠሯቸው ይገባል መልክታችን ነው።

ከተባለበት ጊዜ ዘግይቶ የተጀመረውና ኢ/ወ/ስ አካዳሚ እና አዳማ ከተማን ያገናኘው ሁለተኛ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር አስተናግዶ ተጨማሪ ደቂቃ ላይ በተቆጠረ ጎል አካዳሚ 3-2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻሉት አዳማዎች ሲሆኑ ጎሉንም ፍራኦል ጫለ አስቆጥሯል። ፍራኦል እስካሁን ያስቆጠራቸውን ጎሎች ወደ ስምንት በማድረስ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል። ከደቂቃ በኋላ የአካዳሚው አምበል ከድር ዓሊ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከእረፍት መልስ በአካዳሚ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ከድር ዓሊ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ አካዳሚን መሪ አደረገ። በሁለቱም በኩል በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመሄድ የጎል ዕድል ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቀጥሎ አዳማዎች በነቢል ኑሪ አማካኝነት የአቻነት ጎል አስቆጥሮ 2-2 መሆን ችለው የነበረ ቢሆንም ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል በተጨማሪ ደቂቃ ላይ መልካሙ የስጋት ባስቆጠረው ጎል አካዳሚ ጣፋጭ የሆ ሦስት ነጥብ አግኝቶ ጨዋታው በአካዳሚ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

04:00 በጎፋ ሜዳ ኢትዮጵያ መድን ከሠላም ያገናኘው ጨዋታ ከእረፍት መልስ ወገኔ ገዛኸኝ ፣ ጌታሁን ካሳዬ እና አሸብር ደረጄ አከታትለው ባስቆጠሩት ጎሎች ኢትዮጵያ መድን 3-0 ማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሎ ወደ ሁለተኝነት መምጣት ችሏል።

በማስከተል 6:00 ላይ መከላከያ እና ሀሌታ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አጥቂው ምስግናው መላኩ የውድድሩ 5ኛ ጎሉን አስቆጥሮ መከላከያ መምራት ሲችል ሀሌታዎች በሐብታሙ ዓለማየሁ የአቻነት ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውድደሩ ነገ በአንድ ጨዋታ ሲቀጥል አፍሮ ፅዮን ከኢትዮጵያ ቡና 03:00 ላይ በጃን ሜዳ ይጫወታሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *