ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ከሜዳው ውጪ ደደቢትን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው መራቅ ችሏል

አምስት ጎሎች በታዩበት ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ ደደቢትን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው መራቅ ችለዋል።

ሰማያዊዎቹ ባለፈው ሳምንት መከላከያን ካሸነፈው ስብስባቸው መድሃኔ ብርሃኔ፣ ፉሴይኒ ኑሁ፣ አሸናፊ እንዳለ፣ ዳግማዊ ዓባይን በመድሃኔ ታደሰ፣ እንዳለ ከበደ፣ አለምአንተ ካሴ እና ሙሉጌታ ዓምዶም ተክተው ሲገቡ ብርቱካናማዎቹ በአንፃሩ ባሳለፍነው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ካሸነፈው ስብስባቸው ምንም ቅያሪ ሳያደርጉ ነበር የገቡት።

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ኮሚሽነር መብራቱ አዲሱ በተደረገ የህሊና ፀሎት በተጀመረውና ብዙም ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ ብዙ የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት ሲሆን በአንፃራዊነት የብርቱካናማዎቹ ሙከራዎች ወደ ግብ የተሻለ ወደ የቀረቡ ነበሩ። ዘነበ ከበደ ከቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ከርቀት አክርሮ መቶ ረሺድ ማታውኪል ባወጣው ሙከራ ጥቃታቸው የጀማሩት ድሬዎች መሪ ምታደርጋቸው ግብ ለማግኘት ብዙም አልጠበቁም። በአስራ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ዘነበ ከበደ ከረመዳን ናስር ተቀባብሎ የገባትን ኳስ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል የታየው እንቅስቃሴ ብዙም ጥሩ ሳቢ ባይሆንም ድሬዳዋ ከተማዎች ግን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ከማድረግ አልቦዘኑም። በተለይም በሳጥኑ ግራ በኩል ኤርምያስ ሃይሉ ከ ምንያህል ተሾመ የተላከለትን ኳስ መቶ ዳዊት ወርቁ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተደርቦ ያወጣት ሙከራ የብርቱካናማዎቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች። በአንፃሩ በጨዋታው ብዙም ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ሰማያዊዎቹ ምንም እንኳ ለግብ የቀረቡ ባይሆኑም በአለምአንተ ካሳ አማካኝነት ሁለት ዕድሎች ፈጥረው ነበር። የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ብርቱካናማዎቹ በረመዳን ናስር ግሩም የቅጣት ምት ግብ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

በበርካታ የዳኝነት ስህተቶች ታጅቦ በተካሄደው ሁለተኛው አጋማሽ የሰማያዊዎቹ ብልጫ የታየበት እና ጥቂት የግብ ዕድሎች የታዩበት ነበር። ሄኖክ መርሹ ከርቀት መቶ ሳምሶን አሰፋ ባዳነበት ሙከራ የጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ያስመለከተን ጨዋታው ተጀምሮ ብዙም ሳይዘልቅ ነበር በዚህም መድሃኔ ታደሰ ከ እንዳለ ከበደ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራ ሲሆን ከግቡ ቋሚ ለጥቂት ነበር የወጣው።

በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ የነበራቸው ደደቢቶች በ67ኛው ደቂቃ በያብስራ ተስፋየ የቅጣት ምት ግብ ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ ማድረግ ችለዋል። ከግቡ በኋላም ፍፁም ብልጫ የነበራቸው ደደቢቶች ምንም እንኳ አቻ የሚያደርጋቸው ጎል ባያገኙም በርካታ ዕድሎች መፍጠር ችለው ነበር። በአንፃሩ ግብ ካሰተናገዱ በኃላ ጫና ውስጥ የገቡት ድሬዎች አፈግፍገው መጫወት ምርጫቸው ካደረጉበት ቅፅበት ብዙም ሳይቆዩ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። ፍሬድ ሙሸንዲ ኤልያስ ማሞ ከቅጣት ምት ያሻማውነረ ኳስ ተጠቅሞ ግሩም የግንባር ኳስ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን በድጋሚ ያረጋጋች ግብ ያስቆጠረው።

በርካታ የዳኝነት ስህተቶች እና እሱን ተከትለው በሚመጡ እሰጣ ገባዎች ታጅቦ የቀጠለው ጨዋታው በተለይም በመጨረሻወቹ አስር ደቂቃዎች ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉት ደደቢቶች በሰማንያ ስምንተኛው ደቂቃ በመድሃኔ ታደሰ አማካኝነት ግሩም ግብ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ ማድረግ ችለዋል። አጥቂው ከመሃል ሜዳ የተላከለትን ኳስ ተጫዋች አልፎ በግሩም ሁኔታ በመምታት ነበር ግቡን ያቆጠረው። ከዚ ውጭ ደደቢቶች ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት በመድሃኔ ታደሰ አማካኝነት የሞከሩት ወርቃማ ሙከራም ጨዋታውን ወደ አቻ ውጤት ለማምራት ተቃርቦ ነበር።

ውጤቱ ተከትሎ ተከታታይ ድል ያስመዘገቡት ብርቱካናማዎቹ ካንዣበበባቸው ወራጅ ቀጠና ሲርቁ በአንፃሩ በጥሩ መነቃቃት የነበሩት ደደቢቶች ባሉበት አስር ነጥብ ረግተው እንዲቆዩ ያስቻለ ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡