ከፍተኛ ሊግ ሐ | ሀዲያ ሆሳዕና መሪነቱን አጠናክሯል

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ 14ኛ ሳምንት አምስት ጨዋታዎች እሁድ ሲካሄዱ ሀዲያ ሆሳዕና መሪነቱን ያሰፋበትን ድል ከሜዳ ውጪ አሳክቷል። ወራቤ፣ ቤንች ማጂ እና ካፋ ቡናም ድል ቀንቷቸዋል።

ቡታጅራ ላይ ቡታጅራን ከ ሀድያ ሆሳዕና ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ በእንግዳው ሆሳዕና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የድሏን ብቸኛ ጎል በ65ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ጋናዊው አጥቂ መሐመድ ራዚክ ነው። አርባምንጭ ቅዳሜ ወደ ጅማ ተጉዞ ነጥብ በመጋራሁም ሀዲያ ሆሳዕና ልዩነቱን ወደ አምስት ከፍ አድርጎ በመሪነቱ ቀጥሏል።

ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ ሺንሺቾን አስተናግዶ 3-1 አሸንፏል። ተመስገን ዱባ ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር መልካሙ ፉንዱሬ ቀሪዋን ማስቆጠር ችሏል። በድሉ ታግዞ ስልጤ ወራቤ ነጥቡን 22 አድርሶ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ቦንጋ ላይ ክፋ ቡና ነገሌ ቦረናን ገጥሞ 5-1 አሸንፏል። በቅርቡ ከአሰልጣኙ ጋር የተለያየው ከፋ ቡና የቀድሞው ምክትል አሰልጣኝና በዘንድሮው ውድድር ዓመት በአውስኮድ ሲሰራ የቆየው ሰለሞንን ዋና አሰልጣኝ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብቷል። ለከፋ ቡና ኦኒ ኡጅሉ፣ ተከተል ደፋር፣ ካሳዬ በቀለ እና ባህሩ ከድር (ሁለት) ግቦቹን ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው። ለነገሌ ቦረና ደግሞ አዲሱ አላሮ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል።

ሚዛን ላይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን ያስተናገደው ቤንች ማጂ ቡና በ4ኛው ደቂቃ ቱሳ ሴንዴቦ ባስቆጠራት ጎል 1-0 ሲያሸንፍ ሻሸመኔ ከተማ ከነቀምት ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡