የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር የስራ ስምምነት ተፈራረመ

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አአ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር የመጀመርያ ህክምና እርዳታ አሰጣጥ ስልጠና ፣ የመጀመርያ ህክምና እርዳታ ሙያዊ ድጋፍ ፣ የአንቡላንስ አገልግሎት እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ዛሬ ከ08:00 ጀምሮ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሀ የስምምነቱን ሁኔታ አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በስሩ ከ80 በላይ ክለቦች ሲኖሩ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የህክምና ባለሙያ እና በውድድሮቹ ላይ ለሚደርሱ አደጋዎች የመጀመርያ ህክምና የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ በቀላሉ የሚድኑ ህመሞች ወደ ከፋ ጉዳት እያመሩ ይገኛሉ። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የመጀመርያ እርዳታ የሚሰጡ ባለሙያዎች ምደባ ፣ የመጀመርያ የሙያ ዕርዳታ አሰጣጥ ስልጠናን፣ የደም ልገሳ እና የበጎ ተግባር ስራዎችን ለመስራት የስምምነት ውል እንደፈፀሙ ተናግረዋል።

መርጌሳ ካሳ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአአ ቅርንጫፍ የቦርድ ሰብሳቢ በመቀጠል ባደረጉት ንግግር ” በበጎ ፍቃደኝነት ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ማኅበር በመሆኑ ስልጠናዎችን፣ የማማከር ስራዎችን እና በውድድሮቹ የመጀመርያ እርዳታ የሚሰጥ ይሆናል። ይህ መልካም ጅማሮ እንደ ቤተሰብ ብዙ አብሮ የሚያሰራን እንደሚሆን እንዲሁም ስፖርት እና ቀይ መስቀልን አስተሳስረን እንደምንጓዝ ግምት አለኝ።” ብለዋል።

ከአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሀ ከቀይ መስቀል ማኅበር አበባው በቀለ የሰነድ ፊርማ ስምምነቱ ያካሄዱ ሲሆን በመቀጠል ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ቀርበዋል።

ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል “የስምምነቱ ዝርዝር ነገሮች ምንድናቸው? ስምምነቱ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሁሉም ክለቦች ላይ ነው የሚሰራው? የአአ አብዛኛው ውድድሮች የሚደረጉበት ጃንሜዳ ለጉዳት ቅርብ ነውና ስምምነቱ እነዚህን ታሳቢ ያደርጋል ወይ? የቀይ መስቀል አገልግሎት የሚሰጠው በሁሉም ሜዳ ነው ወይስ በተወሰኑት ላይ? የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ ፍስሀ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል።

” ስምምነቱ ሁሉንም ክለቦች ያጠቃልላል። ከ80 በላይ ከለቦች አሉ። ለእነዚህ ክለቦች ወጌሻዎች የመጀመርያ እርዳታ አሰጣጥ ስልጠና ቢሰጥ ሁሉም ጋር ተዳረሰ ማለት ሲሆን ስምምነቱ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ክለቦች ነው። ጃንሜዳን በተመለከተ አራት ሜዳ በውስጡ አለ። በእነዚህ ሜዳዎች እርዳታ ሰጪ ቃሬዛ እና ድንኳን ሊያቀርቡልን ተስማምተናል። እንዲሁም ከጃንሜዳ ውጪ ባሉ የህክምና ባለሙያ በሌላቸው ሜዳዎች ጭምር ይህን አገልግሎት ለመስጠት ተስማምተናል። አንቡላስ በተመለከተ በአራቱ ሜዳ አንድ ከተደረገ ለጊዜው በቂ ነው በቀጣይ ስምምነቱን እያሰፋን እንሄዳለን።” በማለት ምላሽ ሰተዋል።

በተጨማሪ ምላሽ የሚያሻቸውን ጉዳዮች አቶ በለጠ ዘውዴ እና ኢንስፔክተር የማነህ ማብራርያ በመስጠት መርሐ ግብሩ ተፈፅሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: