አአ U-17 | መድን መሪነቱን ሲያጠናክር ኤሌክትሪክ እና አዳማ ደረጃቸውን አሻሽለዋል

በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ ተካሂደው ኢትዮጵያ መድን፣ አዳማ ከተማ፣ ኤሌክትሪክ እና አፍሮ ፅዮን ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

ረፋድ 3:00 ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድን ሀሌታን 4-1 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል። መድኖች በጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት የተሻማ ኳስ አሸብር ደረጄ በጭንቀት በመግጨት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መሪ መሆን ችለዋል። ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በሙከራ ደረጃ ግን ጥሩ የሚባሉ ሙከራዎች ያልነበሩ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽም በመድን 1-0 መሪነት ነበር የተጠናቀቀው።

ከእረፍት መልስ የተሻለ ተጭነው የተጫወቱት ሀሌታዎች ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ እስጢፋኖስ ይስሀቅ በቅኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ወደግብ ቀይሮ አቻ መሆን ቢችሉም መድኖች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በድጋሚ ወደ ጨዋታው በመመለስ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ አሸብር ደረጀ በጭንቅላት በመግጨት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ በድጋሚ መምራት ችለዋል።

መድኖች በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ግብ በማስቆጠር የግብ መጠናቸውን ወደ አራት አድርሰዋል። 89ኛው ደቂቃ ላይ እስማኤል ረሽድ በግራ መስመር ይዞ በመግባት ወደ ሳጥን መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ የሀሌታ ተከላካዮች ለማራቅ ባለመቻላቸው አምበሉ ጌታነህ ካሳየ ወደግብ ቀይሮ ልዩነቱን ማስፋት የቻለ ሲሆን በጭማሪ ደቂቃ ላይ በድጋሚ ከተካላካዮች መሀል አምልጦ በመውጣት ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ጌታነህ ካሳየ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ መድህን 4-1 ማሸነፍ የቻለበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

5:00 ላይ በአካዳሚ ሜዳ በቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን የገጠመው አዳማ ከተማ 4-1 በማሸነፍ ደረጃውን ከፍ አድርጓል። ጨዋታው በተጀመረ በሰከንዶች ውስጥ ግብ ማስቆጠር መቻላቸው ለአዳማዎች ጨዋታውን ማሸነፍ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረው አጋጣሚ ነበር። ከመሃል የመጀመሪያውን ኳስ የጀመሩት አዳማዎች ቀጥታ ወደ አካዳሚ የግብ ክልል በመጣል የተከላካዮች መዘናጋት ታክሎበት ፍራኦል ጫላ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደግብ በመቀየር አዳማዎችን መሪ በማድረግ ለቡድኑ መነቃቃትን ፈጥሯል። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ከግራ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሙባረክ ሸምሱ ይዞት የገባውን ኳስ ለነቢል ኑሬ አሻግሮለት  ነቢል ከሳጥን ውጭ ወደግብ አክርሮ በመምታት ሁለተኛውን ግብ ለአስቆጥሮ ይበልጥ በራስ መተማመናቸውን ጨምረዋል። አዳማዎች የተሻለ የመሀል ሜዳ ብልጫ በመያዝ ነቢል ኑሬ ከሙባረክ ሸምሱ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብለው ይዘውት የገቡትን ኳስ ነቢል በግሩም ሁኔታ ወደግብ ቀይሮ ልዩነቱን ሲያሰፋ በድጋሚ ከደቂቃዎች በኋላ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ ከተከላካዮች ተገጭቶ ሲመለስ ያገኝውን ሙባረክ ሸምሱ ቀጥታ ወደግብ አክርሮ በመምታት አራተኛውን አስቆጥሮ ወደ እረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኳስ ተቆጣጥረው የተጫወቱት አካዳሚዎች ወደፊት የአዳማን የተከላካይ ክፍል ሰብሮ መግባት ከብዷቸው ነበር። በጨዋታው መገባደጃ የተወሰኑ ደቂቃዎች ሲቀሩት ያገኙትን የማዕዘን ምት በሚሻማበት ወቅት ጥፋት ተሰርቷል በሚል የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አንዋር አብደላ ወደ ግብ ቀይሮ ከሽንፈት ያላዳነቻቸውን ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በአዳማ ከተማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጃንሜዳ ላይ በተደረጉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ መከላከያን 3-1 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ሲያደርግ አፍሮ ፅዮንም በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስን 3-1 ማሸነፍ ችሏል። ሠላም እና ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 1 – 1 አቻ ተለያይተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡