ፌዴሬሽኑ ከፕሪምየር ሊግ ዳኞች ጋር ተወያየ

በፕሪምየር ሊጉ ቀሪ መርሀ ግብር መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ፌዴሬሽኑ ከዳኞች ጋር ዛሬ ውይይት አድርጓል።

ፌድሬሽኑ ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል ከጠዋቱ 3:00 አንስቶ እስከ ምሳ ሰአት ድረስ ለሚዲያ ዝግ በሆነ መድረክ በፕሪምየር ሊጉ ከሚያጫውቱ ዳኞች ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡ በአወያይነት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ እና ምክትል የፅህፈት ቤት ኃላፊው ሰለሞን ገብረሥላሴ በመገኘት ከዳኞቹ ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችሁ መረጃ መሠረት ዳኞች ለፌዴሬሽኑ በርካታ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን የፀጥታ አካላት በበቂ ሁኔታ አለመኖር በዋነኝነት ስጋት እንደሆነባቸው እና ለቻምፒዮንነትና ላለመውረድ የሚጫወቱ ቡድኖችን ሲያጫውቱ ይህ ነገር ይበልጡኑ ስጋት እንደሆነባቸው ተገልጿል።

የፌድሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢይሳያስ ጂራ “ዳኞች ከህግ አግባብ ውጪ አንድን ክለብ ለመጥቀም ጥረት እንዳያደርጉ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፣ ዳኞች ከአቅም በታች የሆነ ጨዋታን በፍፁም ማጫወት የለባቸውም።” ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ በሚደረጉ የሊጉ ወሳኝ የተባሉ ጨዋታዎችን የካሜራ ባለሙያዎችን በመላክ ለማስቀረፅ ፌዴሬሽኑ ማሰቡን የገለፁ ሲሆን ውይይቱ ቀን 6:00 ላይ ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡