በደደቢት ጉዳይ ዙርያ የዲሲፕሊን ደንቡ ምን ይላል?

የደደቢት እግርኳስ ክለብ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በፋይናንስ ችግር ምክንያት “ጨዋታዎችን ለማድረግ እቸገራለሁ” ማለቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመርያ ላይ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ዋና ዋና ነጥቦች አንስተናል።

በዲሲፕሊን መመሪያ አንቀፅ 72 ላይ አንድ ቡድን የሁለት ዙር ውድድር እካፈላለሁ ብሎ ተመዝግቦ እየተወዳደረ ባለበት ወቅት በአንደኛው ዙር ከግማሽ በታች ብቻ ተጫውቶ ራሱን የሚያገል ከሆነ በደንቡ መሠረት የተመዘገበው ውጤት በሙሉ የሚሰረዙ ይሆናል። ከቡድኑ ጋር ለተወዳደሩ ክለቦች ያወጡትን የትራንስፖርት እና የሆቴል ሙሉ ወጪ የሚሸፍን ይሆናል። ሆኖም ደደቢት ቀሪ 7 ጨዋታዎች እየቀሩት ውድድር ለማድረግ እንደሚቸገር በመግለፁ ከላይ የተጠቀሱት ተግባራዊ አይሆኑም።

ከ24ኛው ሳምንት በኋላ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ለማከናወን እንደሚቸገር የገለፀው ደደቢት በዚሁ ውሳኔ የሚቀጥል ከሆነ በአንቀፅ 72 ላይ በተጠቀሰው መሠረት ከግማሽ በላይ ጨዋታዎችን ያከናወነ በመሆኑ በደንቡ ላይ የተጠቀሱ ሌሎች ውሳኔዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ።

1. አንድ ቡድን በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሜዳ ባለመገኘት ፎርፌ ከሰጠ ከውድድሩ ይሰረዛል።

2, ከዚህ ቀደም (ከማቋረጡ በፊት) የተካሄዱ ውጤቶች በሙሉ ይመዘገባሉ።

3. በቀሪ ጨዋታዎች ለተጋጣሚ ቡድኖች ሦስት ነጥብ እና ሦስት ንፁህ ጎሎች ይመዘገባሉ።

4. ውድድሩን አቋርጦ የወጣው ከክለቡ አቅም በላይ ችግር ከሆነ እና ምክንያቱ አሳማኝ ሆኖ ከተገኘ ምንም አይነት የዲሲፕሊን ቅጣት ሳይጣልበት ያለመቀጠል ጥያቄው ተቀባይነት የሚያገኝ ይሆናል።

የተጫዋቾች እና የቡድን አባላት እጣ ፈንታ

አንድ ክለብ ጨዋታዎችን ማድረግ ካቋረጠ ተጫዋቾቹ እና የቡድን አመራሮቹ ተዟዙሮ የመስራት መብት ያላቸው በመሆኑ ወደፈለጉበት ክለብ ሄደው የመስራት መብታቸው በደንቡ ላይ የተቀመጠ ነው።

– አንድ ክለብ ከተበተነ (ውድድር ካቋረጠ) ቡድን ተጫዋቾችን መውሰድ ቢፈልግ ሦስት ተጫዋቾችን ብቻ ነው ማስፈረም የሚችለው።

– ክለቡ ውድድር ያቋረጠው ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ሳይሆን በተጫዋቾቹ እና በክለቡ አመራሮች ችግር ሆኖ ከተገኘ ግን ለአንድ ዓመት ከማንኛውም ውድድር የሚታገዱ እና ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት የሚጣልባቸው ይሆናል።

ማስታወሻ

* መረጃዎቹ ከዲሲፕሊን መመርያው ላይ ቃል በቃል ተወስደው የተፃፉ አይደሉም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡