ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ደቡብ ፖሊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ስታድየም ገድ ያልተለየው ደቡብ ፖሊስን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ጉዳዮች ልናነሳ ወደናል። 

የ24ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ነገ 10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደቡብ ፖሊስን ያገናኛል። ከመሪው አስር ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ የደበዘዘ የሚመስለው የቻምፒዮንነት ተስፋውን ከፍ ለማድረግ ቀድመውት ጨዋታቸውን የሚጀምሩት ሦስት ክለቦች ውጤት ወሳኙ ቢሆንም ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥቦችን አጥብቆ ይፈልጋል። ከመከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ነጥብ ሸምተው ወደ ተመለሱባት መዲናዋ የመጡት ደቡብ ፖሊሶችም እንደነሱ ሁሉ ሰሞኑን ውጤት እየቀናቸው ያሉት የወራጅ ቀጠና ተፎካካሪዎቻቸውን ለመስተካከል በባዶ እጃቸው መመለስ አይኖርባቸውም። 

አምስት ጨዋታዎችን ያለሽንፈት መጓዝ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግብ ያለማስቆጠራቸው ጉዳይ የአሰልጣኝ ስትዋርት ሀል ዋነኛ ራስ ምታት ነው። ቀዳሚ ተመራጭ የነበሩ አጥቂዎቹን በጉዳት ያጣው ቡድኑ በርካታ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩም በኩልም ድክመት እየተስተዋለበት ይገኛል። በዚህ ረገድ ወደ ፊት ገፍተው የመጫወት ልማድ ያላቸው ደቡብ ፖሊሶች ነገም መሀል ሜዳ ላይ በቀላሉ የበላይነቱን እንዳይወስድ ሊያደርጉት ይችላሉ። በመሆኑም በድኑ በቀጥታ ወደፊት በሚጣሉ እንዲሁም የመስመር አጥቂዎቹን ፍጥነት ማዕከል ባደረጉ ኳሶች ወደ ተጋጣሚው ሳጥን መድረስን ዋነኛ የማጥቃት አማራጩ አድርጎ ሊወስደው ይችላል። በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ውድድር ዓመቱ መገባደጃ ድረስ እንደማይጠቀምባቸው ከታወቁት ሳላዲን ሰዒድ ፣ ጌታነህ ከበደ እና መሀሪ መና በቀር ቀሪው ስብስቡ ሙሉ ጤንነት ላይ ሲገኝ ምንተስኖት አዳነ እና ናትናኤል ዘለቀም ወደ ሜዳ እንደሚመለሱ ይጠበቃል። በተለይም የናትናኤል መመለስ ከደቡብ ፖሊስ ፈጣሪ አማካዮች በመነሳት ወደ ፊት የሚሄዱ ኳሶችን ለማቋረጥ ሊጠቅመው እንደሚችልም ይታመናል። 

በሊጉ ታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን የመርታት ፈተና የሚጠብቃቸው ደቡብ ፖሊሶች  ውጤቱ አስፈላጊያቸው ከመሆኑም ባሻገር አጥቅተው መጫወት ምርጫቸው መሆኑ ሲታሰብ ነገም ተመሳሳይ መንገድ እንደሚመርጡ ይጠበቃል። በዘላለም ኢሳያስ የሚመራው የበድኑ አማካይ ክፍል የኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ ለሦስቱ የፊት አጥቂዎች ኳሶችን በማድረስ ቢያንስ ግቦችን እስኪያ ስቆጥር ድረስ ሙሉ ትኩረቱን በማጥቃት ላይ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል። በዚህም ቡድኑን እየታደገ ከሚገኘው ሄኖክ አየለ በተጨማሪ የመስመር አጥቂነት ሚና ተሰጥቶት በአዳማው ጨዋታ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ብርሀኑ በቀለ እንቅስቃሴ ተጠባቂ ይሆናል። ደቡብ ፖሊስ ኤርሚያስ በላይን በህመም በረከት ይስሀቅን በጉዳት ወደ አዲስ አበባ ይዞ ያልመጣ ሲሆን ከቀድሞ ክለቡ ጋር የሚገናኘው  አበባው ቡታቆ የመሰለፍ ጉዳይም አጠራጣሪ እንደሆነ ታውቋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች ስድስት ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ አራቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ደቡብ ፖሊስ በሊጉ ጊዮርጊስን አሸንፎ አያውቅም፡፡  

– የአዲስ አበባ ስታድየም ላይ 12 ጨዋታዎች ያከናወነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰባቱን ሲያሸንፍ አራት የአቻ እና አንድ የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግቧል።

– ከ11 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በአምስቱ ሽንፈት የገጠመው ደቡብ ፖሊስ ሁለቴ አሸንፎ አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ በመጋራት ተመልሷል።       

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ይህን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ኃይለየሱስ በእስካሁኖቹ ስምንት ጨዋታዎች 16 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲያሳይ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የሰጠ ሲሆን አንድ ጊዜ ደግሞ ሁለተኛ የቢጫ ካርድን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ኢሱፍ ቡርሀና

                  
ናትናኤል ዘለቀ – ሙሉዓለም መስፍን – ታደለ መንገሻ

አቤል ያለው – ሪቻርድ አርተር – አቡበከር ሳኒ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ

አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ  – ዘሪሁን አንሼቦ – አበባው ቡታቆ

 ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ኪዳኔ አሰፋ

የተሻ ግዛው – ኄኖክ አየለ – ብርሀኑ በቀለ    

error: