ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | አዳማ ለቻምፒዮንነት በእጅጉ ሲቃረብ ጊዮርጊስ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ወርዷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 21ኛ ሳምንት አምስት ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ሲካሄዱ አዳማ ከተማ ለዋንጫው በእጅጉ የቀረበበትን ድል አስመዝግቧል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መውረዱ ተረጋግጧል።

ጥረት 0-3 አዳማ ከተማ 

(በዳንኤል መስፍን)

ባህርዳር ከተማ ላይ ጥረት ኮርፖሬትን ከአዳማ ከተማ ጋር ያገናኘው ተጠባቂው ጨዋታ በአዳማ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮንነት ክብር ወደ ክልል ያመራ ይሆን የሚለውን ፍንጭ የሚሰጥ ጨዋታ በመሆኑ ተጠባቂ የነበረው ይህ ጨዋታ እንደተጀመረ ብዙም ሳይቆይ ነበር በ3ኛው ደቂቃ ራሷ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሎዛ አበራ መትታ ግብጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ስትተፋው በድጋሚ አግኝታ ወደ ጎልነት ቀይራው አዳማዎችን ቀዳሚ ማድረግ የቻለችው። ቀድመው ጎል በማስቆጠራቸው በስነ ልቦናው የተሻሉ መሆን የቻሉት እንግዶቹ አዳማዎች አማካዮቹ ከመሐል ሜዳ በሚጥሉት ኳሶች በሎዛ አበራ እና ሴናፍ ዋቁማ የባለሜዳዎችን ተከላካዮች ሲፈትኑ ተስተውሏል።

ጥረቶች አልፎ አልፎ ወደ አዳማ ግብ ክልል ቢሄዱም በተደራጀ መልኩ ጎል ለማስቆጠር የነበራቸው ዝግጅት አናሳ በመሆን ብዙ የጎል እድል ለመፍጠር ተቸግረዋል። ያም ቢሆን በጥረት በኩል በዕለቱ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው አማካይዋ ነፃነት ሰውአገኝ ከርቀት አክርራ መትታ የአዳማዋ ግብጠባቂ እምወድሽ ይርጋሸዋ እንደምንም ያዳነችባት ይጠቀሳል። በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነት የወሰዱት አዳማዎች ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎችን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በተለይ በጥሩ መንገድ ሴናፍ እና ሰርካዲስ ከመሐል ሜዳ ኳሱን አደራጅተው ወደ ፊት በመግባት ሎዛ አበራ አጥብቃ የመታችውን ግብጠባቂዋ ታሪኳ ያዳነችባት ተጠቃሽ ነው። ተቀዛቅዞ በቀጠለው የጨዋታው እንቅስቃሴ በጥረት በኩል ከሳጥን ውጭ የጎል እድል ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር ብዙም የረባ ነገር ባይታይም 34ኛው ደቂቃ ትመር ጠንክር ከርቀት አክርራ የመታችው ለጥቂት ወደ ውጭ ወቶባታል። ወደ ዕረፍት መዳረሻ በ45ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ተደርቦ ሲመለሰ ሎዛ አበራ በጀርባዋ ኳሱን በመሸፈን አዙራ በመምታት ለራሷም ለቡድኗም ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ጥረቶች ጠንካራ የጎል እድል በመፍጠር ነበር ጨዋታውን የጀመሩት። 47ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ነፃነት ሰውአገኝ የመታቸውን ጎል ሆነ ሲባል በማይታመን መልኩ የአዳማዋ ግብጠባቂ እምወድሽ ያዳነችባት የሚያስቆጭ ነው። ከዚህ በኃላ በቀሩት ደቂቃዎች ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ ብልጫ ወስደው ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች ወደ ዋንጫው የሚያደርጉትን ጉዞ ለማጠናከር ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የሚያስችላቸውን አጋጣሚዎች ከፊት መስመር አጥቂዎቻቸው የመወሰን ችግር የተነሳ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። 61ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ግብጠባቂዋ ታሪኳን አልፋ አገባችው ሲባል ከሴናፍ ዋቁማ ጋር ኳሱ ላይ በመደራረባቸው የተነሳ የጥረት ተከላካዮች በፍጥነት ደርሰው ያወጡት ኳስ ግብ መሆን የሚችል ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ 65ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ጣጣውን የጨረሰ ኳስ አቀብላት ሴናፍ ዋቁማ ወደ ጎልነት ቀይራው የአዳማዎችን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርጋለች። በቀሩት ደቂቃዎች ብዙም ወደ ጎል የሚደረጉ ሂደቶች ባይኖሩም የጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ 78ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ የታሪኳ ከግብ ክልሏ መውጣቷን ተከትሎ ወደ ግብ የመታችውን ሎዛ በግንባሯ ወደ ኃላ ገጭታ የግቡ ቋሚ የመለሰው ሌላ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ሆኖ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉን ተከትሎ የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታውን በሜዳው የሚያከናውነው አዳማ ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉን ክብር ለማግኘት በእጅጉ ተቃርቧል።

ንግድ ባንክ 1-0 ሀዋሳ ከተማ

(በአምሀ ተስፋዬ)

በተመሳሳይ ሰዓት ሲኤምሲ ባንክ ሜዳ ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዋሳ ከተማ መካከል የተካሄደውን ጨዋታ ንግድ ባንክ 1-0 አሸንፎ የዋንጫውን ፉክክር ወደ መጨረሻው ሳምንት አሻግሮታል። በመሐል ሜዳው በቁጥር በዝተው የተጫወቱት ባንኮች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በረጅም ሆነ በአጭር ኳስ ቅብብል ቶሎ ቶሎ ቢደርሱም ወደ ሶስተኛው የሜዳ የግብ ክልል ሲደርሱ በቀላሉ ሲያባክኑ ተስተውሏል። በ14ኛው ደቂቃ ብዙነሽ ሲሳይ በሁለት ተከላካዮች መሀል ሰንጥቃ ያቀበለቻትን ኳስ ረሂማ በነፃ አቋቋም ላይ ሆና ብታገኘውም ሳትጠቀምበት የቀረችው፤ በ18ኛው ደቂቃ ላይ ሽታዬ ሲሳይ አክርራ መትታ በግብ ጠባቂዋ የዳነባት፤ 34ኛው ደቂቃ ላይ ህይወት ዳንጊሶ ከቀኝ መስመር አክርራ መትታ ግብ ጠባቂዋ በአግባቡ ብታድነውም የሀዋሳ ተከላካዮች በራሳቸው የግብ ክልል ሲቀባበሉ የፈጠሩትን ስህተት ተጠቅማ ረሂማ ለሽታዬ አቀብላት ሽታዬ ወደ ግብ የመታችው ኳስ የግቡን የላይኛውን አግዳሚ ለትሙ ሲመለስ ነፃ የነበረችው ትዕግስት ዘውዴ በግንባሩ ገጭታ አስቆጠረች ሲባል ቅድስት ዘለቀ ከግብነት የታደገችው በዚህ አጋማሽ ባንኮች ከፈጠሯቸው የግብ አጋጣሚዎች ተጠቃሾቹ ናቸው።

ተጋጣሚያቸውሀአዋሳ ከተማዎች በአንፃሩ የተቃራኒ ቡድን ተጫዎቾችን እንቅስቃሴ በመግታት ተጠምደው የዋሉ ሲሆን በ29ኛው ደቂቃ ነፃነት መና በግምት ከ20 ሜትር ርቀት በቀጥታ መትታ በአግዳሚውን ወደ ውጪ የወጣባት እና ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ከመሐል ሜዳ የተላከውን ሰንጣቂ ኳስ ምርቃት ፈለቀ በጥሩ ሁኔታ ተከላካዮችን አምልጣ ብትወጣም በአግባቡ ሳትመታው ያመከነችው ኳሶች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ሁለተኛው አጋማሽ ጎል እስከተቆጠረበት ደቂቃ ድረስ ከቅብብል የዘለለ እንቅስቃሴ ያልታየበት እና የጠሩ የግብ ዕድሎች እምብዛም ያልተፈጠሩበት ነበር። በዚህም 60ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ አባይነሽ ኤርቄሎ በአግባቡ ሳትቆጣጠር ወደ መሬት የለቀቀችውን ገነሜ ወርቁ በአግባቡ ተጠቅማ የንግድ ባንክን ብቸኛ ግብ አስቆጥራለች። ከግቡ መቆጠር በኋላ መነቃቃት የታየባቸው ንግድ ባንኮች በረሂማ ዘርጋው እና ትዕግስት ዘውዴ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም በቀላሉ ተይዞባቸዋል። በተቃራኒው ሀዋሳ ከተማ በፈጣኗ አጥቂ መሳይ ተመስገን በ65ኛው እና 73ኛው ያደረጉት የግብ ሙከራ ተጠቃሽ ነው። በ86ኛው ደቂቃ ብዙነሽ ሲሳይ ምርቃት ፈለቀ ላይ በሰራችው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣች ሲሆን በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች ወደ ኃላ ማፈግፈግን ምርጫቸው በማድረግ ውጤታቸውን አስጠብቀው 1-0 አሸናፊ ሆነዋል።

ወደ አሰላ ያመራው መከላከያ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን በሔለን እሸቱ እና መዲና ዐወል ጎሎች 2-0 አሸንፏል። መከላከያ በድሉ ታግዞ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን አረጋግጧል።

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-1 ተለያይተዋል። ድሬዎች በመጀመርያው አጋማሽ ስራ ይርዳው ባስቆጠረችው ጎል ለረጅም ደቂቃዎች መምራት ቢችሉም ዓለምነሽ ገረመው በጭማሪ ደቂቃ ኤሌክትሪክን አቻ አድርጋለች። የአቻ ውጤቱ ኤሌክትሪክን መውረዱን ከማረጋገጥ ያተረፈች እና ጭላንጭል ያለመውረድ ተስፋን ሰጥቷል።

ዲላ ላይ በ08:00 ጌዴኦ ዲላ ቅዱስ ጊዮርጊስን በስመኝ በረዲ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፏል። ውጤቱን ተከትሎ የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሁለተኛ ዲቪዝዮን መውረዱን አረጋግጧል።

የሳምንቱ ቀሪ አንድ ጨዋታ ሰኞ ሲካሄድ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: Content is protected !!