ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት የሊጉን ዋንጫ ማሳካት የቻሉ ተጫዋቾች ምን አሉ?

ባሳለፍነው እሁድ ፕሪምየር ሊጉ በመቐለ 70 እንደርታ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። በክለቡ ውስጥም የሊጉን ክብር ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ያሳኩ አሰልጣኝ እና ሦስት ተጫዋቾች ይገኛሉ።

በታሪኩ ከሶስት የተለያዩ ክለቦች ጋር ሦስት የሊግ ዋንጫዎች ያነሳው ሁለገቡ ኄኖክ ኢሳይያስ፣ ከክለቡ ጋር ምርጥ ዓመት ያሳለፈው አሚን ነስሩ እና አማካዩ ዮናስ ገረመው ለሁለት ተከታታይ ዓመት የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ ማሳካት የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ሦስቱም ተጫዋቾች ስለዚህ ውድድር ዓመት ቆይታቸው እና ስለተከታታይ ድላቸው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል።

” ከመቐለ ጋር በእርግጠኛነት ዋንጫ እንደማነሳ ተናግሬ ነበር ” አሚን ነስሩ

° ዓመቱ እንዴት ነበር?

የውድድር ዓመቱ በጣም ጥሩ ነበር። ጥሩ ዓመት አሳልፍያለው ብዬ ነው የማስበው። ከሁለት ጨዋታዎች ውጭ ዓመቱን ሙሉ ቡድኔን አገልግያለው። ባጠቃላይ ከጓደቾቼ ጋር አሪፍ ዓመት አሳልፍያለው፤ የሊጉን ዋንጫ ማንሳታችን ልዩ ደስታ ፈጥሮልኛል።

° ተከታታይ ዓመት ዋንጫ ማንሳትህ ምን ስሜት ፈጠረብህ?

በዚህ በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ። በሁለት ዓመት የፕሪምየር ሊግ ቆይታዬ ሁለት የሊግ ዋንጫ ማንሳት ትልቅ ታሪክ ነው ለኔ። በፕሪምየር ሊግ ክለቦች መጫወት ከጀመርኩ ገና ሁለተኛ ዓመቴ ነው። በሁለቱም ዓመታት ግን የሃገሪቱን ትልቅ ዋንጫ ማንሳት ችያለው እና ይህ ለኔ ትልቅ ስኬት ነው።

° ዋንጫ እንደምታነሳ ገምተህ ነበር?

እንደማሳካው እርግጠኛ ነበርኩ። እንደውም በአንድ የሬድዮ የበዓል ፕሮግራም ላይ ጠይቀውኝ ከመቐለ ጋር በእርግጠኛነት ዋንጫ እንደማነሳ ነግርያቸው ነበር። ወደ መቐለ 70 እንደርታ ለመምጣት ስወስንም ከክለቡ ጋር ዋንጫ እንደማነሳ እርግጠኛ ስለነበርኩ ነው።

° ባለፈው ዓመት ሳይጠበቅ ወደ መቐለ 70 እንደርታ በማምራትህ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ መሳተፍ አልቻልክም ነበር። በዚ ዓመትስ?

ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የአንድ ዓመት ውል ነው ያለኝ። ቀጣይ ምን እንድሚፈጠር አላውቅም ፤ ውሌ ስላለቀ እስካሁን ድረስ ከክለቡ ጋር የመቀጠል እና የመለያየት ነገር አልተረጋገጠም። ግን በሻምፕዮንስ ሊጉ መሳተፍ ትልቅ ታሪክ ነው።

° በአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር የመሳተፍ ዕድል በማግኘትህ ምን ተሰማህ?

ይህ ዕድል ባለፈው ዓመትም አግኝቼው ነበር። ዓምና ያልተሳተፍኩበት ምክንያት የኔ ችግር ሳይሆን የክለቡ ችግር ነው። ጅማ አባጅፋር ውሌን ለማራዘም ግዜ ስለወሰደ እኔም ቶሎ ብዬ ስለቀጣይ ግዜዬ መወሰን ስለነበረብኝ ነው በውድድሩ መሳተፍ ያልቻልኩት። መቐለ ያለው ነገርም በጣም ጥሩ ነው። ደጋፊው በጣም ድንቅ ነው። በቀጣም ዓመትም ከፈጣሪ ጋር ከቡድኑ ቆይቼ በቻምፒየንስ ሊጉ ጥሩ ጉዞ አደርጋለው ብዬ አስባለው።

“ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዋንጫ ስታነሳ የተለየ የደስታ ስሜት ነው ያለው” ኄኖክ ኢሳይያስ

° ዓመቱ እንዴት ነበር ላንተ?

ዓመቱ በጣም አሪፍ ነበር ፤ በጣም ብዙ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም በጣም ትልቅና ታሪካዊ ድል አስመዝግበናል። በግማሽ ዓመቱ ወደ ክለቡ ተቀላቅዬ ይህን ክብር ማሳካቴ ደስተኛ ነኝ።
በግሌም ሦስተኛው የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዬ ነው፤ በግል ይህንን ማሳካቴም ትልቅ ድል ነው ለኔ።

° ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት ነው የሊጉን ዋንጫ ያገኘኸው ስሜቱ እንዴት ነው?

ደስ የሚል ስሜት አለው። ዋንጫ ማንሳት የተለየ ስሜት ይፈጥርልሃል። በተለይም ደሞ ለተከታታይ ዓመት ሲሆን ስሜቱ በጣም ልዩ ነው። ብዙ ውጣው ውረድ እና ፈተናዎች አልፈህ ዋንጫ ስትበላ እና ደጋፊህ ስታስደስት የተለየ የደስታ ስሜት ነው ያለው።

°ሳይጠበቅ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ለማምራት ስትወስን ዋንጫው ለሦስተኛ ግዜ አነሳለሁ ብለህ አስበህ ነበር?

ቡድኑ ስቀላቀል ከተከታዮቻችን የነበረን ልዩነት በጣም ሰፊ ነበር እና ቡድኑ ዋንጫው እንደሚያነሳው በዛን ሰዓት የታወቀ ነበር ፤ እኔ ግን ዋንጫውን ለማንሳት አስቤ ሳይሆን ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ብዙ ግዜ ስለሰራው እና አሰልጣኙ በደምብ ስለሚያቀኝ ከሱ ስር በድጋሚ ለመስራት እና ቡድኑን ለመርዳት ነው።

° በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ መሳተፋቹህ አረጋጣቹሃል…

በአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር ላይ መሳተፍ በጣም ትልቅ ነገር ነው። በግሌም በጣም ደስ ብሎኛል።
ክለባችንም ለውድድሩ የሚመጥን ጥሩ ዝግጅት ያደርጋል ብዬ አስባለው።

° ባለፈው ዓመት ከጅማ ጋር የሊጉን ዋንጫ አንስተህ ነው ወደ ወላይታ ድቻ ያመራኸው እና ያንተ ብቻ ሳይሆን የብዙዎቻቹ ውሳኔ አነጋጋሪ ነበር በወቅቱ ያንተ ምክንያት ምን ነበር?

ከሌሎቹ የኔ የተለየ ምክንያት አልነበረም። አብዛኞቻችን ከቡድኑ የለቀቅንበት ምክንያት በወቅቱ የነበረው አመራር ምንም ዓይነት ውል የማደስ ጥያቄ አላቀረቡልንም። በዛ ምክንያት ከቡድኑ ለመለያየት ተገደናል።

“መቐለ 70 እንደርታ ለመምጣት የወሰንኩበት ምክንያት ትክክለኛ ነበር” ዮናስ ገረመው

° ዓመቱ እንዴት አለፈ?

ዓመቱ በጣም አሪፍ ነበር። ከቡድኔ ጋር አሪፍ ጊዜ አሳልፍያለው። ዋንጫው እና የውድድር ዓመቱ ጉዟችን ዓመቱ ለኛ ጥሩ እንደነበር ትልቅ ምስክር ናቸው። ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ዋንጫ በማንሳቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። የምትጫወተውን ለዋንጫ በዓመቱ መጀመርያ ያቀድከው ዋንጫ ስታሳካ ደሞ ትልቅ ደስታ ነው። ባጠቃላይ ከቡድኑ ጋር አሪፍ ዓመት ነው ያሳለፍኩት። በዚ ሰዓት በጣም ደስ የሚል ስሜት ውስጥ ነን ሁላችንም።

° ተከታታይ የሊግ ዋንጫ አንስተሃል…

በጣም ዕድለኛ ነኝ። በሁለት ተከታታይ ዓመታት ዋንጫ ማንሳቴ እና በእግር ኳስ ህይቴ ይሄን ትልቅ ስኬት ማሳካቴ በጣም ደስ ብሎኛል።

° ዋንጫ ባነሳህበት ማግስት ጅማን ለቀህ መቐለ ስትቀላቀል ዋንጫ አነሳለው ብለህ አስበህ ነበር?

እንደዛ ብለህ በርግጠኝነት ገምተህ አትገባም።
ግን ወደ ውድድር ገብተን ብዙ ስኬቶኝ ስናገኝ እና ሊጉን በሰፊ መምራት ስንጀምር በድጋሚ ዋንጫውን አነሳዋለው የሚል ስሜት ነበረኝ።
መጀመርያ ወደ ቡድኑ ስመጣ ግን በርግጠኝነት አነሳለው ብዬ አልመጣሁም ኳስም ስለሆነ።

° ቀጣይ ዓመት በትልቁ ውድድር መሳተፋችሁ አረጋጣቹሃል። በዛ ውድድር ለመሳተፍ መብቃታቹ ምን ስሜት ፈጠረብህ?

ሁሌም ተጫዋች የሚመኘው እና የሚያስበው ነገር ነው። በእግር ኳስ ሂወትህ ከሃገር ወጥቶ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ማድረግ ነው ትልቁ ምኞትህም የሚሆነው። መጀመርያውም እነዚህን አስበህ ነው ከታች ምትነሳው እና እነዚህ ነገሮች መሳካታቸው በግሌም እንደ ቡድንም በጣም ደስተኞች ነን።

° በርካታ ተጫዋቾች ከጅማ ጋር የሊጉን ዋንጫ አንስታቹ ከቡድኑ መልቀቃችሁ አስገራሚ ውሳኔ ነበር። ያንተ ምክንያት ምን ነበር?

ምክንያቴ ጥሩ ኳስ መጫወት እፈልጋለው ያ የሚሆነው ደግሞ እኔ የሚመቸኝ አጨዋወት ወዳለበት ስሄድ ነው እና ዋነኛው ምክንያቴ ይሄ ነው። ሌላው አሰልጣኝ ለቀቀ፣ ተጫዋቾች ለቀቁ እኔ ደግሞ የሚሻለኝን ውሳኔ መወሰን ነበረብኝ። ከዛ ወደ መቐለ ለመምጣት ወሰንኩ። ወደ መቐለ 70 እንደርታ ለመምጣት የወሰንኩበት ምክንያት ደሞ ትክክለኛ ነበር። ለአንተ አጨዋወት ወደሚመችህ ቦታ ስትሄድ ያለህን ነገር አውጥተህ እንድትሰጥም ያደርግሃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: