የአሰልጣኞች አስተያየት፡ ኢትዮጵያ 4-3 ጅቡቲ

በቻን 2020 ማጣርያ ኢትዮጵያ ድሬዳዋ ላይ በዝግ ስታዲየም ጅቡቲን ገጥማ 4-3 አሸንፋ ወደ ቀጣዩ የማጣርያ ዙር አልፋለች። ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ጥሩ ያልተጫወትነው በተጫዋቾቻችን ትኩረት ማጣት በተፈጠረ ችግር ነው” አብርሃም መብራቱ

ስለ ጨዋታው

ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እንቅስቃሴ ባለደረጉበት ጎሎች የተቆጠሩበት ጨዋታ ነው። ይሄም ቢሆን በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸንፈን ወደ ቀጣዩ ማጣርያ ጨዋታ ማለፋችን እንደ አንድ ጥንካሬ ሆኖ በማሸነፍ ውስጥ የተፈጠሩ ስህተቶች ግን አሉ። በሀገራችን ላይ የሜዳ ተጠቃሚነትን የምንወስድበት መንገድ ላይ እንዲሁም በቀጣይ ጥሩ ዝግጅትም አድርገን ወደ ቻን 2020 የምንገባበትን ዕድል እንፈጥራለን።

ጥሩ ያልተጫወቱበት ምክንያት

በተለይ ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ጥሩ አልተጫወትንም። አንደኛው የተጫዋቾቻችን ትኩረት ማጣት የተፈጠረ ችግር ነው። በተለይ ተከላካይ ስፍራ አካባቢ የጅቡቲን አጥቂዎችን የመቆጣጠር ችግር እና በራስ መተማመናቸው መውረድ ዋጋ አስከፍሎናል። ሌላው ሜዳውን ገብታችሁ እንዳያችሁት ለኳስ ቁጥጥር የሚመች አይደለም። ለእነርሱ አጨዋወት የሚያመች ነው። ያም ቢሆን ጨዋታውን በአሸናፊነት መወጣታችን ለተጫዋቾቻችን ትልቅ ሞራል ነው የሚሆናቸው።

“እስከ ጨዋታው መጨረሻ ድረስ ውጤት ይዞ ለመውጣት ከፍተኛ ትግል አድርገናል” ዡልያን ሜት

ስለ ጨዋታው

ዛሬ ከኋላ ጀምሮ ኳሱን መስርተን በመጫወት ውጤት ይዘን ለመውጣት አቅደን ነው ወደ ሜዳ የገባነው። ይህን ፍላጎታችንን ለማሳካት በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ተጋድሎ ማድረግ አስፈልጎናል። ጎሎች ቀድመው እየተቆጠሩበን እስከ ጨዋታው መጨረሻ ድረስ ውጤት ይዞ ለመውጣት ከፍተኛ ትግል አድርገናል። ጥሩ ነበርን፤ ነገር ግን ውጤቱ አልተሳካም። አንዳንድ ተጫዋቾች በዋናው ብሔራዊ ቡድን ሲጫወቱ የመጀመርያቸው ነው። በተለይ የመጀመርያዎቹን ሁለት ጎል ያስቆጠሩት ተጫዋቾች የመጀመርያ ጨዋታቸው ነበር። በአጠቃላይ ይህ በወጣት ተጫዋቾች የተገነባው ቡድን ይህ ባይሳካም የዓለም ዋንጫ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች አሉ። በዛ ላይ ስኬታማ እንድንሆን ጠንክረን እንሰራለን።

ስለ ተጋጣሚያቸው

ተጋጣሚያችን በየቦታው ጥሩ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ነው። ቴክኒካሊም ጥሩ ናቸው። ግን ታክቲካሊ ዲሲፕንድ አልነበሩም። በተለይ የመጀመርያው ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ በራስ መተማመናቸው ወርዶ ነው። ያንን አጋጣሚ ለመጠቀም የሚቻለንን ለማድረግ ሞክረን ነበር፤ አልተሳካም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡